ድሬዳዋ ከተማ ለሁለተኛው ዙር ራሱን ለማጠናከር እየተንቀሳቀሰ ነው

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 14ኛ ሳምንት ፋሲል ከተማን ያስተናገደው ድሬዳዋ ከተማ 1-0 በማሸነፍ በ2 ወራት ውስጥ የመጀመርያ የሆነ ድሉን አስመዝግቧል፡፡ ከጨዋታው በኋላ አስተያየታቸውን የሰጡት የቡድኑ አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው በክፍተቶቻቸው ላይ ትኩረት አድርገው ቡድናቸውን ለማጠናከር እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

” ቡድናችን በዋናነት ያሉበትን ድክመቶች በሚገባ አይቷል፡፡ የድሬዳዋ ስፖርት ቤተሰብም ክፍተታችንን አይቷል፡፡ ክፍተት ያሉብን ቦታዎች በዋናነት የግራ መስመር ተከላካይ እና የተከላካይ አማካይ ላይ ነው፡፡ በተለይ የተከላካይ አማካይ የለንም ማለት ይቀላል፡፡ ተጨማሪም አማካይ ተጨዋቾችም ቡድናችን ያስፈልጉታል፡፡

“የግራ መስመር ተጨዋች ለማግኘት ጥረት እያደረግን ነው ፤ ይሳካል ብዬ አስባለው፡፡ ሁለት አማካዮችን ግን የተወሰኑ ነገሮች ካልሆነ በቀር አብዛኛው ነገሮች ተጠናቀዋል፡፡ በቅርቡ ከቡድኑ ጋር የሚቀላቀሉም ይሆናል” ሲሉ ሀሳባቸውን ገልጸዋል፡፡

በተያያዘ ዜና ድሬዳዋ ከተማ በጉዳት እና በተለያዩ ምክንያቶች በክለቡ ብዙ አገልግሎት ያልሰጡ ተጨዋቾችን ሊያሰናብት እንደተዘጋጀ ለክለቡ ቅርበት ያላቸው አካላት ለሶከር ኢትዮዽያ ገልፃዋል፡፡

ወደ ድሬደዋ ከተማ ከተዛወሩት ተጫዋቾች መከከል አድናን ቃሲም አንዱ መሆኑ ታረጋግጧል፡፡ አምና በሀድያ ሆሳዕና ያሳለፈው አድናን በሲዳማ ቡና አብረውት ከሰሩት አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ጋር በድጋሚ የሚገናኝ ይሆናል፡፡

ድሬደዋ ከተማን የተቀላቀሉት አዲስ ፈራሚዎች እና የሚሰናበቱት ተጨዋቾች ማንነት አጣርተን እንደደረሰን የምናቀርብ መሆኑን እንገልፃለን፡፡

Leave a Reply