​ፋሲል ከተማዎች በተፎካካሪነት ለመቀጠል በዝውውር ገበያው ይሳተፋሉ

የከፍተኛ ሊግ ቻምፒዮን በመሆን ወደ ፕሪምየር ሊግ ያደገው ፋሲል ከተማ በመጀመርያዎቹ 2 ወራትን ባልተጠበቀ ሁኔታ ትልልቆቹን ቡድኖች በማሸነፍ ጭምር የደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ እስከመፎካከር ደርሰው ነበር፡፡ ክለቡ የጥር ወር ከገባ ወዲህ ግን እየተቸገረ የሚገኝ ሲሆን በተደጋጋሚ በጣላቸው ነጥቦችም ወደ ደረጃ ሰንጠረዡ ወገብ ወርዷል፡፡ 

በወቅታዊ የክለቡ ሁኔታ ሶከር ኢትዮጵያ የቡድን መሪው አቶ ሀብታሙ ዘዋለን አናግራለች፡፡ አቶ ሀብታሙ ፋሲል በውድድር ዘመኑ የታዩባቸውን ክፍተቶች እንደለዩ በመግለፅ ክፍተቶቻውን በመሙላት ላይ እንደሚያተኩሩ ተናግረዋል፡፡ 

“ፋሲል ከተማ በዘንድሮ የውድድር አመት በሊጉ ተቀላቅሎ ጠንካራ ፉክክር በማሳየት ጥሩ ቡድን መሆኑን አሳይቷል፡፡ ሆኖም አንደኛ ዙር ሊገባደድ ከመቃረቡ ጋር ተያይዞ ክለቡ ችግሮች አሉብኝ ባላቸው ቦታዎች በተለይ የተከላካይ አማካይ ፣ የመስመር ተጫዋች እንዲሁም የአጥቂ  መስመር ላይ ክፍተቶችን ለመድፈን ተጨዋቾችን ከውጭ ለማስመጣት ጥረት ቢያደርግም በተፈለገው ደረጃ ሊያገኝ አልቻለም፡፡ የውጭ ተጨዋቾች ለማስፈረም ደግሞ የዝውውር መስኮቱ በመዘጋቱ አሁን ሙሉ ትኩረታችንን በሀገር ውስጥ ተጨዋቾች ላይ ብቻ አድርገን እየተንቀሳቀስን እገኛለን” ብለዋል፡፡

አቶ ሀብታሙ አያይዘውም ለአሰልጣኙ አጨዋወት የሚመቹ ተጫዋቾችን ፍለጋ ገበያ እንደሚወጡ ገልጸዋል፡፡

“አሰልጣኙ ለሚከተለው የአጨዋወት ፍልስፍና ይረዳሉ ፤ ይጠቅማሉ ብለን ያሰብናቸውን ተጨዋቾች በፊርማ አልያም  በውሰት ውል ወደ ክለባችን በማምጣት ክለቡን ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ እንዲቀጥል ወደ ገበያው የምናመራ ይሆናል፡፡ ” ብለዋል፡፡

Leave a Reply