ሳምሶን አሰፋ ስለ ወቅታዊ ድንቅ አቋሙ እና ግብ ጠባቂነት ይናገራል 

ሳምሶን አሰፋ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮው የውድድር ዘመን ጥሩ አቋም እያሳዩ ከሚገኙ ተጫዋቾች አንዱ ነው፡፡ ዘንድሮ ለድሬዳዋ ከተማ በእያንዳንዱ ደቂቃ ላይ መሰለፍ የቻለው ሳምሶን ቡድኑ ደካማ የውድድር ዘመን ቢያሳልፍም በግሉ በ6 ጨዋታዎች ላይ ግብ ሳይቆጠርበት በመውጣት ቡድኑ ቢያንስ ያለ ግብ በአቻ ውጤት እንዲያጠናቀቅ ረድቷል፡፡

ሳምሶን ትላንት ድሬዳዋ ከተማ ፋሲል ከተማን 1-0 ካሸነፈበት ጨዋታ በኋላ ከሶከር ኢትዮጵያው ዳንኤል መስፍን ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል፡፡

የግብ ጠባቂነት ህይወትህን እና የተጓዝከውን መንገድ ንገረን…

በግብ ጠባቂነት ስኬታማ የእግርኳስ ህይወት አሳልፌአለው፡፡ በመተሃራ ስኳር ጀምሬ በአየር ኃይል ፣ ኤሌክትሪክ ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሐረር ሲቲ አሳልፌያለሁ፡፡ በተለይ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በክለቡ ሪከርድ የነበሩ ውጤቶች በአፍሪካና በሀገር ውስጥ ውድድሮች ላይ ሲመዘገቡ በዋና ግብ ጠባቂነት አገልግያለው፡፡ በኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድንም ሰፊ አገልግሎት በተለያዩ ጊዜዎች ሰጥቻለው፡፡  አሁንም ቢሆን ሁሌም በትውልድ ስፍራዬ ድሬዳዋ የመጫወት ህልሜ ተሳክቶልኝ ቡድኑን በሚገባ እያገለገልኩ እገኛለው፡፡ በአጠቃላይ በግብ ጠባቂነት ህይወቴ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡

ድሬዳዋ ከተማን በዘንድሮ የውድድር ዘመን እንዴት ትመለከተዋለህ?

ቡድናችን ውስጥ በአብዛኛው ወጣቶች ናቸው የሚገኙት፡፡ ጥሩ አቅም አላቸው፡፡  በቡድን ውስጥ ከፍተኛ ሀላፊነት አለብኝ፡፡ ልምዴንም እያካፈልኩ ነው፡፡ በአንዳንድ ጥቃቅን ስህተቶች ነጥቦች ጥለናል፡፡ ሆኖም ቡድኑ ከዕለት ወደ ዕለት እየተሻሻለ የሚሄድ ነው፡፡ አንዳንድ ችግሮች ነበሩ ፤ እየተስተካከሉ ናቸው፡፡ በሁለተኛው ዙር የክለቡ አመራሮች እና አሰልጣኙ ያስቀመጡት ግብ አለ፡፡ ያንን ግብ በእርግጠኝነት እናሳካለን ብዬ አስባለው፡፡

በሊጉ የኢትዮዽያውያን ግብ ጠባቂዎች በረኞች ቁጥር ከአመት አመት እየቀነሰ ይገኛል፡፡ በዚህ ላይ ያለህ አስተያየት ምንድን ነው? የውጭ እና የሀገር ውስጥ ግብ ጠባቂዎችን አቅምስ እንዴት ትገልፀዋለህ?

እኔ በእርግጠኝነት የምነግርህ ከውጭ መጥተው የሚጫወቱትን ግብ ጠባቂዎች በሙሉ አይቻቸዋለው፡፡ ከኢትዮዽያ ግብ ጠባቂዎች የተሻለ ደረጃ አላቸው ብዬ የምናገረው የቅዱስ ጊዮርጊሱ ሮበርት ኦዶንካራ እና የኢትዮዽያ ቡናው ሀሪሰን ሄሱ ብቻ ናቸው፡፡ ሌሎቹ በስነ-ልቡና እና ክለቦች የውጭ ግብ ጠባቂ ይዘዋል ለማለት ካልሆነ በስተቀር ከኢትዮዽያ ግብ ጠባቂዎች የሚባል ብቃት የላቸውም። እኔ ከሮበርት ጋር ስለሰራው ብዙ ልምዶችን ከሱ አግኝቻለው ፤ ብዙ የሚያሳምኑ ብቃቶች አሉት፡፡ ለእኛ ትምህርት የምንወስድባቸው ግብ ጠባቂዎች ቢመጡ ትቀበላለህ፡፡ ከዛ ውጭ ግን አብዛኛዎቹ ለሊጉ የማይመጥኑ ናቸው። ኢትዮዽያውያን ግብ ጠባቂዎች አቅም አላቸው፡፡ ብዙዎች በምርጥ ብቃታቸው ሲጫወቱባት የነበረባት ሀገር ናት፡፡ በአሁን ሰአት ግን የመሰለፍ እድል ካለማግኘት የተነሳ ብዙ ግብ ጠባቂዎች እየጠፉ ነው፡፡ የሚመለከታቸው አካለት ፣ ክለቦች ፣ የፌዴሬሽን አመራሮች ህግ ሊያወጡ ይገባል፡፡ ሚዲያውም ቢሆን ሊያግዘን ይገባል ፤ አለበለዚያ ነገሮች በዚህ ከቀጠሉ ከባድ ነው የሚሆነው፡፡

ዘንድሮ በግልህ ድቅ አመት እያሳለፍክ ትገኛለህ፡፡ የጥንካሬህ ሚስጢር ምድነው ?

የጥንካሬዬ ሚስጥር ሁሌም ጠንክሮ መስራት ነው፡፡ በአጠገቤ ጠንካራ ተፎካካሪ ግብ ጠባቂዎች አሉ ከተዘናጋሁና ለየጨዋታዎቹ ትኩረት ሰጥቼ ካልተዘጋጀሁ የቋሚነትን እድል አጣለሁ፡፡ በመሆኑም በየጨዋታው ስራዬን በአግባቡ መስራቴ ጥሩ እንቅስቃሴ እንዳሳይ ረድቶኛል፡፡

ግብ ጠባቂ ለመሆን ለሚያስቡ ታዳጊዎች ምን ማስተላለፍ ትፈልጋለህ?

ኢትዮዽያ ውስጥ ጥሩ ግብ ጠባቂ ሆኖ ለመውጣት የሚያስችሉ ያልተሟሉ ብዙ ነገሮች ቢኖሩም በዚህ ተስፋ ሳይቆርጡ ጠንክረው እንዲሰሩ መልዕክቴን አስተላልፈለው፡፡

1 Comment

  1. ሳምሶንን አንድ ጨዋታ የማየት እድል አግኝቺያለሁ ፡ ከሰዉነቱ ሙሉነት ጀምሮ የተሻለ game የማንበብ ስጦታ አለዉ ፡ እሱም እንደጠቀሰዉ ጥሩ በረኛ ለመሆን ሁሌም game ዉስጥ መሆን አለበት 1 በረኛ በ አንድ ጨዋታ ከ3 ያላነሱ ስህተቶችን ይማራል ። always he need to be in the game . ሌላዉ ትልቁ ነገር ጠንክሮ መስራት አለበት ፡ በጣም አሰልቺ እና አድካሚ sport ቢኖር የ ግብ ጠባቂ training ነዉና ፦ የስራህ ዉጤት ምንጊዜም ለ ኩራት ያበቃሃል ።
    Ethiopian football federation must do something to avoid the Shortage of Goalkeepers in the Country ; I belive Ethiopia is the best place to produce very good Goalkeepers . we have to look for long plan .

Leave a Reply