ጋቦን 2017፡ ኤሳም ኤል-ሃዳሪ በደመቀበት ምሽት ግብፅ ለፍፃሜ አልፋለች

ግብፅ ከሰባት ዓመት በኃላ በተመለሰችበት የአፍሪካ ዋንጫ ቡርኪናፋሶን በመለያ ምት በማሸነፍ ለፍፃሜ ማለፏን አረጋግጣለች፡፡ ሊበርቪል ላይ በተካሄደው ጠንካራ ጨዋታ ሃገራቱ መደበኛው ክፍለ ግዜ እና ተጨማሪ ደቂቃውን 1-1 በሆነ የአቻ ውጤት ነበር ያጠናቀቁት፡፡ በኳስ ቁጥጥር የአጠቃላይ የበላይነት ቡርኪናፋሶ ብትወስድም በመጨረሻም ተሸንፋ ከፍፃሜው ቀርታለች፡፡

19ሺህ ተመልካች በስታዲየም ገብቶ በተከታታለው ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ ግብ ሳይቆጠርበት ተጠናቅቋል፡፡ በፈርኦኖቹ በመሃመድ ቴሬዝጌ እና መሃሙድ ካራባ እንዲሁም ፈረሰኞቹ በፕሪጁስ ንኮልማ፣ አሪስቲድ ባንሴ እና በርትራንድ ትራኦሬ አማካኝነት ለግብ የቀረቡ ያልተሳኩ ሙከራዎችን በመጀመሪያው አጋማሽ ማድረግ ችለዋል፡፡ በ65ኛው ደቂቃ ካራባ ያመቻቸለትን ኳስ ተጠቅሞ የፈርኦኖቹ ወሳኝ ተጫዋች መሃመድ ሳላህ በግሩም ሁኔታ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል፡፡ መሪነቱ የዘለቀው ግን ለሰባት ደቂቃዎች ብቻ ነበር፡፡ ግብፅ ግቧን በአፍሪካ ዋንጫው ሳታስደፍር ብትቆይም የባንሴ የ72ኛ ደቂቃ ግብ ቡርኪናፋሶን አቻ አድርጓል፡፡ አብዱራዛክ ትራኦሬ ሳጥን ውስጥ ያሸገረለትን ባንሴ በደረቱ ካበረደ በኃላ በኤሳም ኤል-ሃዳሪ መረብ ላይ አስቆጥሯል፡፡

በመደበኛው የጨዋታ ክፍለግዜ እና በጭማሪ 30 ደቂቃው ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር ሃገራቱ ወደ መለያ ምት አምርተዋል፡፡ ግብፅ የመጀመሪያ ምቷን በአብደላ ኤል-ሰዒድ አማካኝነት ብታመክንም የ44 ዓመቱ ኤል-ሃዳሪ ሁለት ምቶችን በመመለስ ሃገሩን ለፍፃሜ አብቅቷል፡፡ የቡርኪናፋሶው ግብ ጠባቂ ሄርቬ ኮፊ እና አማካዩ በርትራንድ ትራኦሮ ምቶችን ኤል ሃዳሪ አምክኗል፡፡ ለ675 ደቂቃዎች በአፍሪካ ዋንጫ ግቡን ያላስደፈረው ኤል ሃዳሪ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ በካፍ ተመርጧል፡፡

ቡርኪናፋሶ ጥቂቶች ብቻ ለግማሽ ፍፃሜ የጠበቋት ሲሆን ለግብፅም እጅግ ፈታኝ ሁና ነበር፡፡ ግብፅ በቡርኪናፋሶ ተሸንፋ የማታውቅ ሲሆን በ1998 የቡርኪናፋሶ ባስተናገደችው የአፍሪካ ዋንጫ ፈረሰኞቹ እና ፈርኦኖቹ በግማሽ ፍፃሜው ተገናኝተው ፈርኦኖቹ በሆሳም ሃሰን ሁለት ግቦች ማሸነፋቸው ይታወሳል፡፡ የ2010ን የአፍሪካ ዋንጫ ካሸነፈች በኃላ ከአህጉሪቱ ታላቅ ውድድር ርቃ የቆየችው ግብፅ ከሰባት ዓመት በኃላ በተመለሰች ውድድር ለፍፃሜ ቀርባለች፡፡ ግብፅ በ2011 ተነስቶ በነበረው አብዮት እና የፖለቲካ ውጥንቅጥ እግርኳሷን በእጅጉ ጎድቶት ነበር፡፡

ሐሙስ ጋና ከካሜሮን በሌላኛው ግማሽ ፍፃሜ ይገናኛሉ፡፡ የሁለቱ አሸናፊ ግብፅን በመጪው ዕሁድ በፍፃሜው ሊበርቪል ላይ ሲገጥም ተሸናፊው ለደረጃ ከብርኪናፋሶ ጋር ቅዳሜ ፖር ዠንቲል ላይ ይፋለማል፡፡
የፎቶ ምንጮች፡ AP, AFP, Reuters, BeIN Sports

1 Comment

 1. ታላቅ አክብሮት ለሶከር ኢትዮጵያዎች
  አንድ አስተያየት አለኝ
  እሁድ ጥር 14/2009 ዓ.ም በተካሄደዉ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሊግ ምድብ ’ሠ’
  አምበሪቾ 1-0 ጋርዱላ ከተማ
  ተብሎ በድህረገጻችሁ የተገለጸዉን ማርጋገጥ ብቻል፡፡ 1-1 አቻ እንደተጠናቀቀ ነዉ የሰማነዉ፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ የደረጃ ሠንጠረዥ ለዉጥም ይኖረዋል፡፡
  አመሰግናለሁ!
  ዘማች ነኝ

Leave a Reply