​ሱራፌል ጌታቸው “ከአአ ከተማ አግባብ ባልሆነ መንገድ የስንብት ደብዳቤ ደርሶኛል ” ይላል

አዲስ አበባ ከተማ እግርኳስ ክለብ በዲሲፕሊን እና ጉዳቶች ምክንያት ተጫዋቾችን እንደቀነሰ ከዚህ ቀደም ማስነበባችን ይታወሳል፡፡ ከተቀነሱት ተጫዋቾች አንዱ የሆነው አማካዩ ሱራፌል ጌታቸው ከክለቡ የተቀነሰበት መንገድ አግባብ እንዳልሆነና እንደማይቀበለው ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጿል፡፡

በክረምቱ የዝውውር መስኮት ከሙገር ሲሚንቶ አአ ከተማን የተቀላቀለው ሱራፌል በቅድመ ውድድር ዝግጅት ወቅት በደረሰበት ጉዳት ህክምና ላይ እያለ ክለቡ በ’አቋም መውረድ’ ማስጠንቀቂያ እንደሰጠው ይገልፃል፡፡ ” ዝግጅት ከምናደርግበት አዳማ ከተመለስን በኋላ ጥቅምት ወር ላይ ነበር የተጎዳሁት፡፡ ከዛም ታህሳስ 12 ላይ ቀዶ ጥገና አድርጌ በማግስቱ የ3 ሳምንት ፍቃድ ደብዳቤ በማስገባት ህክምናዬን ስከታተል ቆይቻለሁ፡፡ ሆኖም ገና በ9 ቀናት ውስጥ (ታህሳስ 21) ክለቡን ማገልገል ባለመቻልህ ወደ ብቃትህ እንድትመለስ የሚል ማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ደረሰኝ፡፡ ጥር 3 ቀን 2009 የተሰጠኝን ፍቃድ ጨርሼ ክለቡን እንደተቀላቀልኩ አሳውቄ በማግስቱ የጂምናዝየም ስራዎች መስራት ጀምሬ ነበር፡፡ ነገር ግን በድጋሚ ታህሳስ 8 ከክለቡ በደረሰኝ ደብዳቤ ከዚህ ቀደም የተላከልህን ደብዳቤ ስለላልተቀበልክ ዲሲፕሊን ጥሰሃል  በሚል የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተሰጠኝ” ይላል፡፡

ሱራፌል የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ የተሰጠበት አግባብ ላይ ያለውን ቅሬታ በደብዳቤ ማሳወቁን ይገልጻል፡፡ ” በህክምና ላይ እንዳለሁ እየታወቀ በአቋም መውረድ ተብሎ የተፃፈብኝ ደብዳቤ ያለውን ሁኔታ የማይገልፅ እንደሆነ ለክለቡ ቅሬታዬን አቅርቤያለሁ፡፡ ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽንም ግልባጭ አስገብቼ ምላሽ በመጠባበቅ ላይ ሳለሁ ክለቡ ባደረጋቸው 15 ጨዋታዎች ባለመሰለፍህ ፣ የእረፍት ጊዜህን ጨርሰህ በወቅቱ ቡድኑን ባለመቀላቀልህ እና ለ11 ቀን በመጥፋትህ ከክለቡ ተሰናብተሃል የሚል ደብዳቤ ጥር 16 ቀን 2009 ደርሶኛል” ሲል ስለ ጉዳዩ አስረድቷል፡፡

ከአዲስ አበባ ጋር የ2 አመት ኮንትራት ተፈራርሞ ክለቡን የተቀላቀለው ሱራፌል አግባብ ባልሆነ መንገድ የስንብት ደብዳቤ የደረሰው በመሆኑ ጥር 17 ቅሬታውን ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን መግለፁንና የፌዴሬሽኑን ውሳኔ እየተጠባበቀ እንደሆነ ገልጿል፡፡

ዘንድሮ በተጫዋቾች እና ክለቦች መካከል እንዲህ አይነት ውዝግቦች ሲከሰቱ ይህ የመጀመርያ አይደለም፡፡ ከ2 ሳምንት በፊት ወልድያ ከ3 ተጫዋቾት ጋር በነበረው ውዝግብ ምክንያት ከውድድር እስከመታገድ ደርሶ እንደነበር ይታወሳል፡፡

Leave a Reply