የሴካፋ ሀገራት ከ17 ዓመት በታች ዋንጫ በሰኔ ወር ዩጋንዳ ላይ ይዘጋጃል

የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ሀገራት የእግርኳስ ካውንስል (ሴካፋ) ከ10 አመታት በኋላ በአዲስ መልክ ከ17 ዓመት በታች ዋንጫ በዩጋንዳ እንደሚያዘጋጅ አስታውቋል፡፡

ከ20 ዓመት በታች እና የታዳጊ ውድድሮች ከዚህ ቀደም ሲዘጋጁ የነበረ ቢሆንም ክፍለ አሃጉሩ በተደጋጋሚ ጠንካራ የሆነ የታዳጊዎች ውድድርን ለማዘጋጀት ሲቸገር ይስተዋላል፡፡ የሲኒየር ቻሌንጅ ዋንጫውን እና የክለብ ዋንጫውን በ2016 መጨረሻ ያደርጋል ተብሎ ቢጠበቅም ሳይደረጉ መቅረታቸውም ይህ ውድድር እንዳይሰረዝ ስጋት የሚያጭር ነው፡፡

ውድድሩ በሰኔ ወር እንዲዘጋጅ ቀነ ቀጠሮ ሲያዝለት ሴካፋ የተሳታፊ ሀገራትን ግንቦት ላይ ይፋ እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡ የዩጋንዳው Chimp Reports ድረ-ገፅ ዘጋቢ የሆነው ፍሬድ ሞአምባ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፀው ከሆነ ውድድሩ በሰሜን ዩጋንዳ በምትገኘው ጂንጃ የፉፋ ንጅሩ ቴክኒካል ማዕከል ይካሄዳል፡፡  የሰው-ሰራሽ ሳር ንጣፍ ያለው ንጅሩ የቴክኒክ ማዕከል በመስከረም ወር የሴቶችን የሴካፋ ዋንጫ ተካሂዶበታል፡፡

ከክፍለ አህጉሩ ማህበር አባላት አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ በውድድሩ ላይ ትሳተፍ አትሳተፍ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም፡፡ የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን በቶታል የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች ዋንጫ ለማለፍ በተደረገው የመጨረሻ ማጣሪያ ዙር በማሊ 4-1 በሆነ የአጠቃላይ ውጤት ተሸንፎ ከውድድር መውጣቱ ይታወሳል፡፡ ከማጣሪያው ጨዋታ በኃላም ቡድኑ ተበትኗል፡፡

የደከመ የእግርኳስ ደረጃን ይዘዋል ተብሎ ከሚጠቀሱት ክፍለ አሃጉሮች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሰው ምስራቅ አፍሪካ በ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ላይ አንድም ተወካይ የለውም፡፡

Leave a Reply