​በሴቶች ፕሪምየር ሊግ የዛሬ ተስተካካይ ጨዋታዎች ሲዳማ ቡና እና ጌዲኦ ዲላ አሸነፉ 

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ 1ኛው ዙር መደበኛ መርሃ ግብር ተጠናቆ በሲዳማ ቡና እና አአ ከተማ ዘግይተው ወደ ውድድር መግባት ምክንያት ያልተደረጉ ጨዋታዎች እየተካሄዱ ይገኛሉ፡፡ 
እሁድ ወደ አርባምንጭ ያቀናው አዲስ አበባ ከተማ አርባምንጭ ከተማን 1-0 ማሸነፍ ችሏል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማን የድል ግብ በፍፁም ቅጣት ምት ያስቆጠረችው አምበሏ ቱቱ በላይ ናት፡፡

ዛሬ 09:00 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም ሲዳማ ቡናን ያስተናገደው አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ 1-0 ተሸንፏል፡፡ በአሰልጣኝ ፍሬው የሚመሩት ሲዳማ ቡናዎች በመጀመርያው አጋማሽ ብልጫ ወስደው የተጫወቱ ሲሆን 42ኛው ደቂቃ ላይ ረድኤት አለኸኝ ባስቆጠረችው ጎል እረፍት ወጥተዋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማዎች በኳስ ቁጥጥሩ የተሻለ ሆነው በመቅረብ ግብ ለማስቆጠር ቢጥሩም የተደራጀውን የሲዳማ ቡና የተከላካይ መስመር ሰብረው መግባት ሳይችሉ ጨዋታው በሲዳማ ቡና 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ለሲዳማ ቡና ውጤት ማማር የአማካይዋ ዘነበች አርጎ እና ግብ አስቆጣሪዋ ረድኤት አለኸኝ  ሚና ተጠቃሽ ነበር።

11:30 ላይ በቀጠለው ሁለተኛ ጨዋታ አዲስ አበባ ከተማ ከ ጌዲኦ ዲላ ተጫውተው በእንግዶቹ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ዘንድሮ ፕሪምየር ሊጉን በመቀላቀል አስደናቂ አቋማቸውን በማሳየት ክስተት የሆኑት ጌዲዮ ዲላዎች በመጀመርያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩም ሆነ ለጎል የቀረበ ሙከራ በማድረግ ተሽለው ቀርበዋል፡፡ በ35ኛው ደቂቃ በዕለቱ ጥሩ ስትንቀሳቀስ የነበረችው ፋሲካ ንጉሴ ግሩም ጎል አስቆጥራ ጌዲኦ ዲላን ቀዳሚ በማድረግ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ዲላዎች በተመሳሳይ ብልጫ የወሰዱ ሲሆን ባሳዩት አስገራሚ እንቅስቃሴ በስታድየሙ የነበረውን ተመልካች ቀልብ መግዛት ችለው ነበር፡፡ 88ኛው ደቂቃ ላይ አዲስ አበባዎች የአቻነት ጎል ፍለጋ ከግብ ክልላቸው ነቅለው በወጡበት አጋጣሚ 88ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይራ የገባችው የኔነሽ መኩሪያ ሁለተኛ ጎል አስቆጥራ ጨዋታው በጌዲዮ ዲላ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

በጨዋታው ላይ ድንቅ እንቅስቃሴ ያሳየችው 10 ቁጥር ለባሿ ቤተል ጥባ ለጌዲዮ ዲላ አሸናፊነት ትልቁን ሚና ተጫውታለች፡፡

የሴቶች ፕሪምየር ሊግ 1ኛ ዙር ሊጠናቀቅ የምድብ ለ2 ተስተካካይ ጨዋታዎች ይቀራሉ፡፡

ተስተካካይ ጨዋታዎች

ሰኞ ጥር 29 ቀን 2009

09:00 ሲዳማ ቡና ከ አዲስ አበባ ከተማ (ይርጋለም)

ቅዳሜ የካቲት 4 ቀን 2009

09:00 ሲዳማ ቡና ከ ሀዋሳ ከተማ (ይርጋለም)

የጌዲዮ ባህላዊ አለባበስ በመልበስ በስታድየሙ የሚገኘውን ተመልካች ሲያዝናና ያመሸው የጊዲዮ ዲላ ደጋፊ

Leave a Reply