ጋቦን 2017፡ ካሜሮን ከግብፅ በፍፃሜው ይፋለማሉ

የአራት ግዜ የአፍሪካ ቻምፒዮኗ ካሜሮን ጋናን 2-0 በመርታት ከ2008 በኃላ ለመጀመሪያ ግዜ ለፍፃሜ መብቋቷን አረጋግጣለች፡፡

ከጨዋታው አስቀድሞ የጋናው ግብ ጠባቂ ራዛክ ብሪማ በጋና ደጋፊዎች ላይ ያልተገባ ቃል በመሰንዘሩ የጋና ሚዲያዎች ወሬ ነበር፡፡ አብዛኞቹ ከዋክብቶቿ ፊቷን ያዞሩባት ካሜሮን ለዋንጫው ከፍተኛ ግምትን ያገኙትን ሴኔጋል እና ጋናን ከዋንጫው ውጪ በማድረግ አልቀመስ ብላለች፡፡ የማይበገሩት አናብስቶቹ ሰኞ እለት በቦነስ ክፍያ ምክንያት ከፌድሬሽኑ ጋር በገቡት ቅራኔ ምክንያት ልምምድ አልሰሩም ነበር፡፡

ፍራንስቪል ላይ በተካሄደው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ካሜሮን ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች በማድረግ የተሻለች ነበረች፡፡ ከማዕዘን የተሻገረውን ኳስ አዶልፍ ቴኩ ሞክሮ የጋናው የመስመር ተከላካይ ሃሪሰን አፉል ከመስመር ላይ አውጥቶበታል፡፡ ሮበርት ታምቤ ከርቀት የሞከረው ኳስ ብሪማ መልሶበታል፡፡ ጥቋቁር ከዋክብቶቹ በመጀመሪያው አጋማሽ ጆርዳን አዩ ካደረገው ሙከራ ውጪ ይህን ነው የሚባል ሙከራ አላደረጉም፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ የጋና የበላይነት የተፀባረቀበት ሆኗ አልፏል፡፡ ሙባረክ ዋካሶ፣ ቶማስ ፓርቴ እና ጀርዳን አዩ አሁንም ያለተሳኩ ሙከራዎች አድርገዋል፡፡ በ72ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት የተሻገረውን ኳስ የብሪማ እና የተከላካዩ ጆን ቦይስ አለመግባባት ታክሎበት ግዙፉ የካሜሮን ተጫዋች ሚካኤል ንጋዱ-ንጋድጂ የማይበገሩት አናብስቶቹን መሪ ማድረግ ችሏል፡፡ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሲል ደግሞ በመልሶ ማጥቃት የመጣውን ኳስ ከመሃል ሜዳ ይዞ በመሄድ ክሪስቲያን ባሶጎግ ወደ ግብነት ቀይሮ ካሜሮኖችን አስፈንድቋል፡፡ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ በካፍ የተመረጠው ባሶጎግ ነው፡፡

ካሜሮን ከ2008 ወዲህ ለመጀመሪያ ግዜ ለፍፀሜ መብቃት ችላለች፡፡ ካሜሮን በ2002 ሴኔጋል በመለያ ምት አሸንፋ ዋንጫውን ካነሳች ወዲህ ዋንጫውን አሸንፋ አታውቅም፡፡ የእሁድ የፍፃሜ ተጋጣሚዋ ግብፅ በሁለት የፍፃሜ ጨዋታዎች  ከካሜሮን ጋር ተገናኝታ በሁለቱም አሸናፊ እንደነበረች ይታወሳል፡፡ በ1986 በመለያ ምት 5-4 እንዲሁም በ2008 በመሃመድ አቡትሪካ ብቸኛ ግብ ግብፅ ካሜሮንን በማሸነፍ ነው ዋንጫውን ያነሳችው፡፡ ጋና በተከታታይ ለስደስት ግዜያት በአፍሪካ ዋንጫ ግማሽ ፍፃሜ ብትደርስም በሁለቱ ብቻ አሸናፊ ሆኗ ለፍፃሜ የደረሰችው፡፡ ከ1982 ወዲህም የአፍሪካ ዋንጫን አንስታ አታውቅም፡፡

የፍፃሜ ጨዋታው ዕሁድ ሊበርቪል በሚገኘው ስታደ አሚቴ ሲካሄድ ጋና እና ቡርኪናፋሶን በሚያገናኘው የደረጃ ጨዋታ ፖር ዠንቲል ላይ ቅዳሜ ይደረጋል፡፡

 

የፎቶ ምንጭ፡ AFP

 

Leave a Reply