ወልቂጤ ከተማ 2 ጨዋታ በሜዳው እንዳያደርግ ቅጣት ተጣለበት

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የከፍተኛ ሊጉ ክለብ ወልቂጤ ከተማ ደጋፊዎች የስፖርታዊ ጨዋነት ጥሰት በመፈፀማቸው በክለቡ ላይ የገንዘብ እና የጨዋታ ቅጣት አስተላልፏል፡፡

ወልቂጤ ከተማ ታህሳስ 23 ከሀድያ ሆሳዕና ጋር ባደረጉት የ6ኛ ሳምንት ጨዋታ የቡድኑ ደጋፊዎች በፈፀሙት ያልተገባና ከስፖርታዊ ጨዋነት የራቀ ተግባር በሜዳው የሚያደርጋቸው ሁለት ጨዋታዎችን በሌላ ሜዳ እንዲያደርግ ተወስኖበታል፡፡ ፌዴሬሽኑ በቅጣቱ  ውሳኔው እንዳብራራው ከሀድያ ሆሳዕና ጋር በተደረገው ጨዋታ ላይ ደጋፊዎች ወደ መጫወቻ ሜዳው ድንጋይ በመወርወር ጨዋታው ለ5 ደቂቃ እንዲቋረጥ በማድረጋቸው ፣ የሜዳውን አጥር አልፈው በመግባታቸው ፣ ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላም በተጫዋቾች ፣ ዳኞች እና የፀጥታ ሃይሎች ላይ ድንጋይ በመወርወር የውድድሩን መንፈስ በማወካቸው በሜዳው የሚያደርጋቸው ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎችን ከወልቂጤ 100 ኪሎሜትር ርቀት በላይ በሆነ ሜዳ እንዲጫወት እና 30,000 ብር ቅጣት እንዲከፍል ተወስኖበታል፡፡ ጨዋታዎቹ የሚደረጉባቸው ቀናት እና ቦታዎች ፌዴሬሽኑ ወደፊት እንደሚገልፅም አስታውቋል

የወልቂጤ ደጋፊዎች ከዚህ ቀደም በብሄራዊ ሊግ የዙር እና የማጠቃለያ ውድድሮች ላይ ተደጋጋሚ የስፖርታዊ ጨዋነትን የሚጥሱ ተግባራት መፈፀማቸውንና ክለቡ ይህን ለማስተካከል ጥረት አለማድረጉን ፌዴሬሽኑ አስታውሷል፡፡

ወልቀጤ በከፍተኛ ሊጉ ምድብ ለ 15 ነጥብ ይዞ 4ኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ በቀጣይ በሜዳው የሚያደርጋቸው ጨዋታዎች በ12ኛው ሳምንት ከድሬዳዋ ፖሊስ እና በ15ኛው ሳምንት ከጅማ ከተማ ጋር ነበር፡፡

1 Comment

Leave a Reply