ፕሪሚየር ሊግ ፡ ደደቢት ኢትዮጵያ ቡናን አሸነፈ

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 20ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ በተደረገ ብቸኛ ጨዋታ ደደቢት ኢትዮጵያ ቡናን 3-0 በሆነ ሰፊ ውጤት በማሸነፍ ደረጃውን አሻሽሏል፡፡

ደደቢቴ ጨዋታው በተጀመረ ገና በ9ኛው ደቂቃ ሳሙኤል ሳኑሚ ባስቆጠረው ግብ 1-0 መምራት ጀምሯል፡፡ በ39ኛው ደቂቃ ናይጄርያዊው አጥቂ በድጋሚ ከመረብ ያሳረፋት ግብ ደደቢትን በ2-0 መሪነት እረፍት እንዲወጡ ሲያደርግ ዳዊት ፍቃዱ በሁለተኛው አጋማሽ የመጨረሻዎቹ ደቂዎች ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው በደደቢት 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ከጨዋው በኋላ አስተያየታቸውን የሰጡት የደደቢቱ አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ የቡና ተከላካዮች ላይ ጫና መፍጠራቸው ውጤት እንዳስገኘላቸው ተናግረዋል ‹‹ ጥንካሬያችን የተዘጋጀንበትን ሜዳ ላይ ተግባራዊ ማድረጋችን ነው፡፡ በማጥቃት አጨዋወት በነሱ የግብ ክልል አካባቢ ጫና ፈጥረን በመጫወት ተከላካዮች እንዲሳሳቱና የግብ እድል ለመፍጠር አስበን ነበር ይህም ተሳክቶልናል፡፡ ›› ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

የቡናው አንዋር ያሲን በበኩላቸው የተከላካዮች ስህተት ዋጋ እንዳስከፈላቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹ ግቦች የተቆጠሩብን በተከላካዮቻችን ስህተት ነው፡፡ ከሽንፈት ወደዚህ ጨዋታ መምጣታችን የማሸነፍ ግዴታ ውስጥ ገብተን ነበር፡፡ በፍጥነት ግቦች መቆጠራቸውም ወደ ጨዋታው እንዳንመለስ አድርጎናል፡፡ ከቀሩን ጨዋታዎች አንፃር ከዋንጫው ፉክክር ወጥተናል ›› ብለዋል፡፡

 

ያጋሩ