በትናንትናው ዕለት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በይፋ የተለያየው የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቹ በዛሬው ዕለት አዲስ ክለብ መቀላቀሉን ሶከር አትዮጵያ አረጋግጣለች፡፡
የቀድሞው የደቡብ ፖሊስ፣ ደደቢት እና የደቡብ አፍሪካው ክለብ ቢድቬስት ዊትስ የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቹ ከደቡብ አፍሪካ በመመለስ ደደቢትን በድጋሚ ተቀላቅሎ ከተጫወተ በኋላ ነበር በ2010 ክረምት ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስን ተቀላቅሎ እስከተጠናቀቀው የውድድር ዓመት አጋማሽ የቆየው። ተጫዋቹ ከ20ኛው ሳምንት በኋላ በዲሲፕሊን ቅጣት በክለቡ ታግዶ ቆይቶ የአንድ ዓመት ቀሪ ውል እየቀረው በትላንትናው ዕለት በስምምነት በይፋ ከክለቡ ጋር መለያየቱ የሚታወስ ነው።
ጌታነህ ከአስር ቀናት በፊት ወደ ሲዳማ ቡና ለማምራት በድርድር ላይ የነበረ ቢሆንም መሳካት ባለመቻሉ ለጊዜው ከሰበታ ጋር ልምምድ ሲሰራ መታየቱ ይታወሳል፡፡ ይህን ተከትሎ የተጫዋቹ ቀጣይ ማረፊያ የት ይሆን በሚል መነጋገሪያ ሆኖ የሰነብተው አጥቂ በዝውውር መስኮቱ የመጨረሻ ቀን በሁለት ዓመት ኮንትራት ወልቂጤን መቀላቀሉን የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ታምራት ለሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጠዋል።
ጌታነህ ከበደ ከዚህ ቀደም በሦስት የተለያዩ ጊዜያት የፕሪምየር ሊጉ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ እና ሁለት ጊዜያት ኮከብ ተጫዋች ሆኖ ማጠናቀቁ ይታወቃል።