የጨዋታ ሪፖርት | አአ ከተማ ከ ወልድያ አቻ ተለያይተዋል

በ15ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመርያ ጨዋታ አዲስ አበባ ከተማ ወልድያን አስተናግዶ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይተዋል፡፡

በአስከፊው የትራፊክ አደጋ ምክንያት ህይወታቸውን ለሚያጡ ሰዎችን በህሊና ፀሎት በማሰብ የተጀመረው የአዲስ አበባ ስታድየም የ9:00 ጨዋታ በ9 ነጥቦች መጨረሻ ደረጃ ላይ የነበረው አዲስ አበባ ከተማን ወቅታዊ አቋሙ ጥሩ የሆነውን እና በ18 ነጥቦች 9ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ወልድያን ያገናኘ ነበር ።

የመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ እንደሚጠበቀው ሁሉ አዲስ አበባ ከተማዎች በኳስ ቁጥጥሩ የበላይነቱን የወሰዱበት ሆኖ ታይቷል። ያም ቢሆን የወልድያው አንጋፋ አጥቂ አንዱአለም ንጉሴ ነበር የመጀመሪያ የግብ ሙከራ ያደረገው። በ3ኛው ደቂቃ ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመምታት የሞከረው ኳስ በመጠኑ ወደላይ ተነስቶበት ወደ ውጪ ወጥቷል። ከዚህ በኃላ እስከ 45ኛው ደቂቃ የጫላ ድሪባ ጎል ድረስ ጨዋታው በአብዛኛው በአዲስ አበባዎች የኳስ ቁጥጥር የበላይነት በወልድያዎች ሜዳ ላይ አመዝኖ የቀጠለ ነበር።

ባለሜዳዎቹ ምንም እንኳን በብዛት በተጋጣሚያቸው ሜዳ ላይ ኳስ የማንሸራሸር እድል ቢያገኙም ወደኋላ ያፈገፈገውን የወልድያ የአማካይ መስመር እና ከአማካይ ክፍሉ ጀርባ እምብዛም የማይርቀውን የተከላካይ መስመር ማለፍ ተስኗቸው ታይቷል ። በ11ኛው ደቂቃ ላይ ሙሃጅር መኪ ከወልድያዎች ሳጥን ውስጥ በቅርብ ርቀት መቶት ወደላይ ከወጣው ኳስ ውጪ አዲስ አበቤዎቹ ኤሚክሪል ቤሊንጌን ብዙ ሲያስጨንቁት አልታዩም ። በተለይ ቡድኑ በሚያጠቃበት ወቅት ሁለት ቦታ በመከፈል ሶስቱ የማጥቃት አማካዮች እና ሁለቱ አጥቂዎች ብቻ በሁለት የአራት ተጨዋቾች መስመር ከተገነባው የወልድያ የመከላከል መስመር ጋር እየተጋፈጡ በሚወሰድባቸው የቁጥር ብልጫ ጥቃታቸው አቅም ሲያጣ ተስተውሏል ።

በ35ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር ከታዬ አስማረ የተነሳችው ኳስ በአለማየው ሙለታ በእጅ ተነክታለች እና የፍፁም ቅጣት ምት ይገባናል ቢሉም በአልቢትር በዝምታ የታለፉት ወልድያዎች በበኩላቸው ሰፊውን የሜዳ ክፍል ለአዲስ አበባዎች በመተው እና ያለኳስ ወደኋላ በማፈግፈግ በመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን ለመፍጠር ሞክረዋል ።  ከዚህ አጨዋወት አልፎ አልፎ ከርቀት ከተደረጉ ሙከራዎች በቀር ብዛት ያላቸውን አጋጣሚዎች መፍጠር ባይችሉም የመጀመሪያውን አጋማሽ ግን መርተው ነበር ወደመልበሻ ክፍል ያመሩት። ጫላ ድሪባ በ45ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት የተሻገረውን እና በደረጄ የተመለሰውን ኳስ ከ አዲስ አበባዎች ሳጥን ውስጥ ተረጋግቶ በግሩም ሁኔታ በመምታት ነበር ቡድኑን ቀዳሚ ያደረገው።

ሁለተኛው አጋማሽ ከጨዋታ እንቅስቃሴ አንፃር ከመጀመሪያው ጋር በተመሳሳይ መልኩ ሲጀምር አዲስ አበባ ከተማዎች የአቻነት ግብ ፍለጋ ጫና ፈጥረው በመጫወት ነበር የጀመሩት። በዚህም ጥረታቸው በፈጠሩት አጋጣሚ በ53ኛው ደቂቃ ከግቡ ጥቂት ሜትሮች ላይ ፍቃዱ አለሙ ጥሩ አጋጣሚ አግኝቶ ቢሞክርም ኤሚክሪል ቤሊንጌ ለጥቂት አድኖበታል ። ነገር ግን ከ 3 ደቂቃዎች በኋላ የአዲስ አበባዎች የማጥቃት ጨዋታ ከወልድያዎች የተከላካይ ክፍል የአቋቋም ስህተት ታክሎበት በግራ መስመር ያገኘውን እድል የቤሊንጌን መውጣት በመመልከት ዳዊት ማሞ በትሩ አጨራረስ ቡድኑን አቻ አድርጓል። 

ከዚህ በኃላም አዲስ አበባዎች በመነቃቃት አጥቅተው የተጫወቱ ሲሆን በ71ኛው ደቂቃ ኃይሌ እሸቱ በደረቱ አብርዶ ከርቀት  በመምታት ያደረገው ድንቅ ሙከራ እና በ82ኛው ደቂቃ ይሄው ተጨዋች በቀኝ መስመር በሙሃጅር መኪ በቀጥታ የተሞከረችውን ኳስ ወደውጪ ከመውጣቷ በፊት በሸርተቴ ለማስቆጠር ይሞከረበት አጋጣሚ ቡድኑ ለጎል የቀረበባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ።
እንግዳዎቹ ወልድያዎች በበኩላቸው ጨዋታው ወደመገባደጃው በተቃረበ ቁጥር ሁለተኛ ጎል ፍለጋ ከራሳቸው ሜዳ በመነሳት እና ፈጣን የማጥቃት ሽግግር በማድረግ ወደ አዲስ አበባዎች የግብ ክልል ለመቅረብ ቢሞክሩም ስኬታማ ለመሆን ግን አልቻሉም። በዚህም መሰረት ጨዋታው በ1- 1 ውጤት የተጠናቀቀ ሲሆን ወልድያዎች ባገኙት አንድ ነጥብ በመታገዝ በጊዚያዊነት መከላከያን በግብ ክፍያ በመብለጥ ደረጃቸውን ወደ 8ኛነት ከፍ ሲያደርጉ አዲስ አበባ ከተማም ነገ ጨዋታ የሚያደርገው ጅማ አባ ቡናን በመብለጥ 15ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡


Leave a Reply