የጨዋታ ሪፖርት | ቅዱስ ጊዮርጊስ የመጀመሪያውን ዙር በመሪነት አጠናቋል 

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 15ኛ ሳምንት አአ ስታድየም ላይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን የገጠመው ቅዱስ ጊዮርጊስ 4-1 በመርታት 1ኛውን ዙር በመሪነት ጨርሷል፡፡

በመጀመሪያው ጨዋታ ላይ እንደተደረገው ሁሉ በዚህኛውም ጨዋታ በመኪና አደጋ ምክንያት ህይወታቸውን ለሚያጡ ሰዎች የህሊና ፀሎት በማድረግ ነበር ጨዋታው የተጀመረው።

በመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች ተመጣጣኝ የኳስ ፍሰት በታየበት የጨዋታ እንቅስቃሴ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ጠንካራ ሙከራዎች አልታዩም። ነገር ግን  በ11ኛው ደቂቃ ላይ የቅ/ጊዮርጊሶች የመጀመሪያ አደገኛ የማጥቃት ሙከራ ወደግብነት ተቀይሯል።  አበባው ቡታቆ ከግራ መስመር ካሻማው የእጅ ውርወራ የተነሳችውን ኳስ ሳላዲን በተረከዝ ወደ ፊት ሲያሻግረው ፈጣኑ የመስመር አጥቂ አቡበከር ሳኒ ወደ ውስጥ ይዟት በመግባት እና የሚያሻማ በመምሰል የንግድ ባንኩ ግብ ጠባቂ ሙሴ ገ/ኪዳን ባጠበበት በኩል በመምታት አስቆጥሯል።

ከአበከር ሳኒ ጎል በኋላ ጨዋታው በመጠኑ ቢቀዛቀዝም በኳስ ቁጥጥሩ ጊዮርጊሶች የተሻሉ ሆነው ታይተዋል። በሙከራውም በኩል ጊዮርጊሶች በ22ኛው ደቂቃ ላይ ጥሩ የግብ እድል ፈጥረው ነበር፡፡ ሳልሀዲን ሰይድ ምንተስኖት አዳነ በረጅሙ ከመሀል ሜዳ የላከለትን ኳስ ትጠቅሞ ከግብ ክልሉ በወጣው ግብ ጠባቂ መሴ ገ/ኪዳን አናት ላይ ቺፕ አርጎ ለማስቆጠር የሞከረበት አጋጣሚ ሲሆን ኳሷም ግብ ሳትሆን ወደላይ ተነስታለች ። ሳሀዲን ይህን ዕድል በማምከኑ በከፍተኛ ቁጭት ውስጥ ሆኖ ታይቷል ።

ከዚህች ሙከራ 1 ደቂቃ ቆይታ በኋላም ለቅዱስ ጊዮርጊሶች ሁለተኛ ግብ መቆጠር መንስኤ የሆነው አጋጣሚ ተፈጠረ ። ኢማኑኤል ፌቮን ተክቶ የንግድ ባንኮችን ግብ ሲጠብቅ የነበረው ሙሴ ገ/ኪዳን በበሀይሉ አሰፋ ላይ ጥፋት በመስራቱ አልቢትሩ ለሙሴ የቢጫ ካርድ እንዲሁም ለቅ/ጊዮርጊስ የፍፁም ቅጣት ምት ሰጥተዋል ። ፍፁም ቅጣት ምቱም በአዳነ ግርማ አማካይነት ወደ ሁለተኛ ጎልነት ተቀይሯል ።

ከዚህ በኋላ የነበረው የመጀመሪያው ግማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሙሉ ለሙሉ የቅዱስ ጊዮርጊሶች የበላይነት የታየበት ነበር። በ33ኛው ደቂቃ የቡድኑ የፊት አጥቂ ሳልሀዲን ሰይድ አቡበከር ሳኒ ከግራ መስመር ያሻማውን እና ምንተስኖት አዳነ የጨረፈውን ኳስ የንግድ ባንክን ተከላካይ በማለፍ ካመቻቸ በኋላ ከግቡ አፋፍ ላይ ሶስተኛውን ጎል ከመረብ አዋህዷል ። ሳልሀዲን የመጀመሪያው አርባ አምስት ሊጠናቀቅ ስድስት ደቂቃዎች ሲቀሩትም ሌላ ጎል በማከል የቡድኑን መሪነት ወደ 4 ከፍ ማድረግ ችሏል። ጎሏም ምንተስኖት አዳነ ከመስመር ያሻማውን ኳስ የንግድ ባንኩ የመሀል ተከላካይ ቶክ ጀምስ በግንባሩ ከጎሉ ለማራቅ ያረገው ሙከራ በተቃራኒው ወደግብ አምርቶ እና የግቡን አግዳሚ ለትሞ ሲመለስ ኳስ ወደ ሳልሀዲን ሰይድ አምርታ አጥቂው በነፃነት ያስቆጠራት ነበረች ። ይህች ጎል ለሳልሀዲን በዚህ የውድድር አመት ሰባተኛ ጎሉ ሆና ተመዝግባለች።

በጨዋታው በጉዳት ምክንያት በርካታ የተጨዋቾች እና የሚና ለውጥ አድርጎ ወደሜዳ የገባው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቡድን በተጋጣሚው የተወሰደበት ከፍተኛ ብልጫ ጨዋታውን እጅግ አክብዶበታል ። ያም ሆኖም በ45ኛው ደቂቃ ላይ የቅዱስ ጊዮርጊሱ የመሀል ተከላካይ አስቻለው ታመነ ከቡድኑ የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ጠርዝ ላይ ፒተር ንዋድኬ ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን የቅጣት ምት ራሱ ፒተር በመምታት ለንግድ ባንክ የውጤት ማጥበቢያ የሆነች ጎል አስቆጥሯል።

መጀመሪያው አጋማሽ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ እና የተቆጠሩት ግቦች ብዛት ሁለተኛውን አርባ አምስት ንግድ ባንኮች ግቦችን ለማግኘት እና ውጤቱን ለማጥበብ እንዲሁም ጊዮርጊሶች ውጤቱ በሚሰጣቸው ነፃነት አጥቅተው በመጫወት ተጨማሪ ጎሎችን ለማግኘት የሚጥሩበት ይሆናል ተብሎ ቢጠበቅም እንደታሰበው ሳይሆን ቀርቷል ። በተቃራኒውም ሁለተኛው አጋማሽ ጥቂት የግብ እድሎች የተፈጠሩበት እና የቀዘቀዘ የጨዋታ ፍሰት የታየበት ሆኖ አልፏል ።

ምንም እንኳን ንግድ ባንኮች ከመጀመሪያው በተሻለ ወደፊት ገፍተው ለመጫወት ጥረት ቢያረጉም የተቆጠረባቸውን ግቦች የሚያካክሱ እድሎችን መፍጠር ከብዷቸው ታይቷል ። እንደሙከራም ሊነሱ የሚችሉት አጋጣሚዎች ከፊት አጥቂው ፒተር ንዋድኬ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ግብ በጣም ርቆ ያረጋቸው የነበሩ ሙከራዎች ናቸው ። ከዛ ውጪ በ31ኛው ደቂቃ አዲሱ ሰይፉን በመተካት ወደሜዳ  ተቅይሮ የገባው ዳንኤል ለታ በ87ኛው ደቂቃ ላይ ከፒተር የተቀበለውን ኳስ በቀጥታ ለማስቆጠር ሲሞክር  ሳልሀዲን ባርጌቾ ተደርቦ ያወጣበት አጋጣሚ የሚጠቀስ ነው ።

በመጀመሪያው ግማሽ በጎል የተንበሸበሸው ቅዱስ ጊዮርጊስም እንደታሰበው ተደጋጋሚ እድሎችን እና ተጨማሪ ጎሎችን ማግኘት ሳይችል ነበር ጨዋታው ከእረፍት በፊት በነበረው የ 4-1 ውጤት የተጠናቀቀው ። ቡድኑ አምስተኛ ጎል ለማግኘት ተቃርቦ የነበረውም በ 63ኛው ደቂቃ አዳነ ግርማ ከመስመር የመጣውን እና የንግድ ባንኮች የተከላካይ መስመር ስህተት የታከለበትን ኳስ  በሙሴ አናት ላይ በመስደድ  ወደግብ ለመቀየር በሞከረበት አጋጣሚ ነበር። ነገር ግን ኳሷ የግቡን መስመር ሳታልፍ ከሰከንዶች በፊት ተቀይሮ የገባው ፍቃዱ ደነቀ ደርሶ አውጥቷታል።

የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በዚህ መልኩ ሲገባደድ በጨዋታው እንቅስቃሴ እና ውጤት በጣሙን የተደሰቱት የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ከቡድኑ ተጨዋቼች ጋር በጋራ በመሆን ድሉን በጭፈራ አክብረዋል ። ውጤቱንም ተከትሎም ቅዱስ ጊዮርጊስ የ2009ኝን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር በ29 ነጥቦች በመሪነት ያጠናቀቀበትን ነጥብ ሲያሳካ ። በሁለት ጨዋታዎች 6 የግብ እዳ የገጠመው እና አንድ ቀሪ ጨዋታ ያለው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክም እስከ ነገ የሌሎቹ ቡድኖች 15ኛ ሳምንት ጨዋታዎች 12ኛ ደረጃ ላይ ይቆይያል።

Leave a Reply