የአሰልጣኞች አስተያየት፡ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1-4 ቅዱስ ጊዮርጊስ

ቅዱስ ጊዮርጊስ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን 4-1 በሆነ ሰፊ ውጤት በመርታት ሊጉን እየመራ አንደኛውን ዙር አጠናቋል፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የሁለቱም ክለቦች ምክትል አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

“ከመጀመሪያውም አጥቅተን ግቦችን ለማግኘት ነበር እቅዳችን” የቅዱስ ጊዮርጊስ ምክትል አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ

ስለጨዋታው

“በጣም ጥሩ ነው፡፡ በመጀመሪያ 45 በተለይ በምንፈልገው መንገድ ተጫውተናል፡፡ ከመጀመሪያውም አጥቅተን ግቦችን ለማግኘት ነበር እቅዳችን፡፡ ተሳክቶልናል፡፡ በሁለተኛው 45 ትንሽ ቀዝቀዝ ያለ ይመስላል፡፡ ግን ተጫዋቾቻችን በብልጠት ውጤቱን ይዘው ለመውጣት ሞክረዋል፡፡ ተሳክቷል፡፡”

“በአዲስ አበባ ከተማ ጨዋታ ብቻ ሳይሆን ባለፉት ሶስት አራት ጨዋታዎች ጥሩ አልተጫወትንም፡፡ ደጋፊዎቻችንን አላስደሰትንም፡፡ ሁልጊዜም ስህተቶቻችን ላይ ጠንክረን ለመስራት ሞክረናል፡፡ ካለፈውም ጨዋታ ተነስተን አንዳንድ ማስተካከያዎችን ለማድረግ ሞክረናል፡፡ ተጫዋቾቻችን በአዕምሮ ለማዘጋጀት ነው ብዙ የሰራነው፡፡ እንደሚያታየው ሜዳ ላይ ተነሳሽነታቸው ጥሩ ነበር፡፡ ልንጫወተው የምንፈልገውን የጨዋታ ዘዴ እየተገበሩ ነው፡፡ ቢሆንም ስህተቶች አሉብን ፤ እነዚህን ስህተቶች አርመን ለወደፊቱ እንመጣለን፡፡”

“የመስመር ተጫዋቾቻቸውን ልንቆጣጠር አልቻንም” የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምክትል አሰልጣኝ ሲሳይ ከበደ

ስለጨዋታው

“ቅዱስ ጊዮርጊስ ተጭኖ ነው የተጫወተው፡፡ ከዕረፍት በፊት ባገባቸው ግቦችም ጨዋታውን በአሸናፊነት ሊወጣ ችሏል፡፡ እኛም ከእረፍት በፊት በሰራናቸው ስህተቶች ጨዋታው ልንሸነፍ ችለናል፡፡”

“እንዳያችሁት የተከላካይ ክፍላችን በሁለቱምጨዋታዎች (ከኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በተደረገው) ስህተቶችን እየሰራ ነው፡፡ አጠቃላይ ቡድናችንን ፈትሸንና ራሳችንን ተመልክተን የመከላከል ችግራችንን ቀንሰን ወደፊት ያሉትን ጨዋታዎች በማሸነፍ ሊጉ ላይ ለመቆየት እንሰራለን፡፡”

“ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከሜዳቸው ወጥተው እኛ ሜዳ ላይ ተጭነው ለመጫወት ነው የፈለጉት፡፡ እኛ ይህንን ጨዋታቸውን ልንቆጣጠረው አልቻልንም፡፡ ተጨማሪ ደግሞ የመስመር ተጫዋቾቻቸውን ልንቆጣጠር አልቻንም፡፡ በእነዛ ነገሮች ነው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቅድሚያ ሊወስድብን የቻለው፡፡ ግን በአጠቃላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ በጥንካሬው ብቻ ሳይሆን የመጀመሪያዎቹ ሁለት ግቦች በእኛ ስህተቶች የተገኙ ግቦች ናቸው ዋጋ ያስከፈሉን፡፡”

Leave a Reply