ቅዱስ ጊዮርጊስ 1-1 ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፡ ታክቲካዊ ትንታኔ

በሚልኪያስ አበራ

እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር በ2008 ዓ.ም በታዋቂው የታክቲክ ፀኃፊ ጆናታን ዊልሰን የተደረሰውና የአለምን የእግርኳስ የታክቲክ ታሪክ በሚያወሳው መፅሃፍ (Inverting The Pyramid) መቅድም ላይ እንዲህ የሚል አጭር አንቀፅ ይገኛል፡፡

‹‹ Football is not about the players , its about the shape and about space, about the intelligent deployment of players and their movement with in that deployment ››

ዘመናዊ እግርኳስ በቡድን ቅርፅ ፣ በሜዳ ላይ በሚፈጠሩ የመጫወቻ ክፍተቶች ፣ በተጫዋቾች ብልሃታዊ የቦታ አጠቃቀም እንዲሁም በእንቅስቃሴያቸው ላይ እንደሚመሰረት የሚያስገነዝብ ሃሳብ ይሰጠናል፡፡

የእግርኳስ ፎርሜሽኖች ደግሞ ተጫዋቾች በሜዳ ውስጥ እንደመነሻ በሚኖራቸው የቦታ አያያዝ እና ከተጫዋቾች መሰረታዊ ባህርያቸው ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ይኖራቸዋል፡፡

በሶከር ኢትዮጵያ ላይ የሚሰሩ ታክቲካዊ ትንታኔዎችም በሜዳ ውስጥ በሚታዩ የቡድኖች ቅርፅ ላይ ጥገኛ ይሆናል፡፡ እንደተለመደው ተጋጣሚዎቹ የገቡበትን መነሻ ቅርፅ ፣ በተጫዋቾች እንቅስቃሴ ፣ በአስጣኞች ታክቲካዊ ውሳኔዎች እና የተጫዋቾች ለውጥ ያስከተሏቸውን ፎርሜሽኖች እናቀርባለን፡፡

በትላንትናው እለትም የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ 3ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ከንግድ ባንክ ጋር የአዲስ አበባ ስታድየም የ10፡00 መርሃ ግብር ጨዋታ ላይ 3 አንኳር ታክቲካዊ ክስተቶች ተስተውለዋል፡፡

ሁለቱም ቡድኖች በሙሉ የጨዋታው ክፍለጊዜ ከፈረንጆቹ ሚሌንየም አንስቶ በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ የሚገኘውና በስፔናዊው አሰልጣኝ ሁዋንማ ሊሎ አማካኝነት ለመጀመርያ ጊዜ ስራ ላይ እንደዋለ የሚነገርለት 4-2-3-1 ነው፡፡

(ምስል 1)

የፊሊፕ ዳውዚ ፍጥነት እና የተጋጣሚን high-line defending የሚሰብርበት መንገድ

የንግድ ባንኩ 9 ቁጥር high – line defending system (ተከላካዮች ወደ መሃለኛው የሜዳ ክፍል ተጠግተው የሚከላከሉበት የአጨዋወት ስልት) ሰርተው የሚጠቀሙ ቡድኖችን እንዴት መቅጣት እንዳለበት የሚረዳበት ታክቲካዊ ግንዛቤንና ከተከላካዮች ጀርባ ያለውን ሰፊ ክፍተት የሚጠቀምበት ፍጥነትን ታድሏል፡፡

በሊጉ ካስቆጠራቸው ግቦች በንፅፅር አመዛኙን ያስቆጠረው ፍጥነቱን እና የተጋጣሚ ተከላካዮች (በተለይ የመሃል ተከላካዮች) ከጀርባቸው የሚተዉትን ክፍተት እየተጠቀመ ነው፡፡ ከሳምንታት በፊት ኤሌክትሪክ ላይ አንዲሁም ባለፈው ሳምንት ንግድ ባንክ ላይ ያስቆጠራቸው ግቦች ይህን አመልካች ናቸው፡፡ በትላንትናው እለትም ጊዮርጊስ ላይ ጨዋታው በተጀመረ በ2ኛው ደቂቃ ቡድኑን መሪ ያደረገው በተመሳሳይ መንገድ ነው፡፡ ከግራ መስመር በረጅሙ የተላከለትን ኳስ ከተቆጣጠረ በኋላ ከጀርባቸው ሰፊ ክፍተትን እና ረጅም ርቀት ትተው ወደ መሃል የተጠጉትን የጊዮርጊስ ሁለቱን የመሃል ተከላካዮች (ደጉ እና ኢዜንዴ) አልፎ 14ኛ የሊግ ግቡን አስቆጥሯል፡፡

High – line defending system ከፍተኛ ቅንጅትን (organization) እና ትኩረትን (concentration) ይፈልጋል፡፡ የመሃል ተከላካዮች ፈጣን እና ቀልጣፋ እንዲሆኑ እና ጥሩ የቦታ አያያዝ (positioning) እውቀት እንዲኖራቸው ይጠበቃል፡፡ስኬታማ የመዋሃድ መስመር (coherent – line) ያለው እና ከጨዋታ ውጭ ወጥመድን (offside trap) በትክክል መተግበር የሚችል ሙሉ የተከላካይ መስመር ከማስፈለጉም በላይ ኳስን መጫወት የሚችል ግብ ጠባቂም ለአጨዋወቱ ግብአት መሆን ይኖርበታል፡፡ ግብ ጠባቂው በራቀው የተከላካይ መስመር እና በራሱ የግብ ክልል መካከል ያለውን ሰፊ ክፍተት እና ረዘም ያለ ርቀት መሸፈን የሚያስችለውን በእግር የመጫወት ብቃት ቢታደል ሲስተሙን በጥሩ ሁኔታ ለመተግበር ያስችላል፡፡

በተጋጣሚ ሜዳ ተጫዋቾች በሜዳው ቁመት በሚኖራቸው የአግድሞሽ መስመሮች (bands) መካከል በቅርብ ርቀት የሚገኙበትን መንገድ የሚፈጥርበት አዎንታዊ ጎኑ በተጋጣሚ ሜዳ በርከት ያሉ ተጫዋቾችን በማስገኘትና የ counter pressing አጨዋወትን ለመተግበር ቢያስችልም ለፈጣን የተጋጣሚ አጥቂዎች እና ላልታሰበበት የተጋጣሚ መልሶ ማጥቃት (counter attacking) አጨዋወት ተጋላጭ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ፈረሰኞቹ በመጀመርያው አጋማሽ የተደረጉባቸው የግብ ሙከራዎች ከስልቱ አተገባበር የመጡ ህፀፆች ነበሩ፡፡

(ምስል 2)

1bbbb

የአዳነ 10 ቁጥር ሚና

10 ቁጥሮች ከሌሎች ፎርሜሽኖች በተሸለ በ4-2-3-1 ፎርሜሽን ተመራጭ ናቸው፡፡ ከብቸኛው አጥቂ ጀርባ በመሆንም የ attacking play makers ሚና መወጣት ይችላሉ፡፡ የቡድናቸውን የማጥቃት አጨዋወት ፍሰት (fluidity) ለመቆጣጠርም ኳስን በትክክል የማቀበል (passing accuracy) ፣ የኳስ ቁጥጥር (ball control) ፣ ፈጠራ (creativity) ፣ እይታ (vision) እና ቴክኒክ የቦታው ተሰላፊዎች በዋነኝነት ሊያሟላቸው የሚገቡ ችሎታዎች ናቸው፡፡

በ4-2-3-1 ፎርሜሽን በሁለት የተከላካይ አማካዮች ስለሚታገዙም ከፍተኛ የመከላከል ኃላፊነት ላይጠበቅባቸው ይችላል፡፡ ከመሃለኛው ክፍል የሚነሳን ኳስ (midfield build-up) የማስጀመር እና በነፃ ሚና በሜዳው ቁመት እና አግድሞሽ በሁለገብነት ሊንቀሳቀሱም ይችላሉ፡፡ አጥቂውን ከጀርባ ካሉ የተከላካይ አማካዮችጋር የማገናኘት ሃላፊነትን ሊወጡም ይችላሉ፡፡ በመስመሮች ከመስመር አማካዮች እና ፉልባኮች ጋር በመሆንም የሶት ማእዘናት የመቀባበያ አማራጮችን መፍጠር እና ተጋጣሚን overload ለማድረግ የሚያስችል እንቅስቃሴ ሌላው የ10 ቁጥሮች ተጠባቂ ሚና ነው፡፡

አዳነ ከተጠቀሱት ሃላፊነቶች አንፃር ሚናው የሚፈልገውን የታክቲክ ስርአት (discipline) የሚያሟላ ተጫዋች አይደለም፡፡ በ10 ቁጥር ሚና በሚሰለፍባቸው ጨዋታዎች የቦታውን ትክክለኛ ግልጋሎት የሚያበረክትባቸው አጋጣሚዎች እጅግ ውስን ናቸው፡፡

በትናንትናውም እለት ወደ ግራው መስመር ባደላው እንቅስቃሴ ከዘካርያስ እና በኃይሉ ጋር መጠነኛ overload ሲፈጥር ከመታየቱ ውጪ ያን ያህል ስኬታማ አልነበረም፡፡ በጨዋታው ወደ ሁለቱም መስመሮች እየወጣ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል የሚልካቸው ተሻጋሪ ኳሶች ወደ መስመር ያደላ እንቅስቃሴ ማድረጉን አመላካች ሆኗል፡፡

የመስመር አጥቂዎቹ ዳዋ እና በኃይሉ በተለይ በመጀመርያው አጋማሽ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በተደጋጋሚ የሚልኳቸው ረጃጅም የአግድሞሽ ኳሶች (long diagonal passes) ብሪያን እና አዳነን ታሳቢ ያደረጉ ቢሆንም ልኬታቸውን እና ኢላማቸውን የጠበቁ አልነበሩም፡፡ የአዳነ – – – ስርአትም ለዚህ እደምክንያት ሊቀርብ ይችላል፡፡በጠንካራው እና በተደራጀው የንግድ ባንክ የመከላከል ሂደት ውስጥ የአዳነ የቦታ አያያዝ ጥያቄን የሚያጭር ነበር፡፡ በጠበበው የተከላካይ እና የተከላካይ አማካይ መሃል ከአጥቂው ብሪያን ጋር በአግድሞሽ ትይዩ (lateral line) የሚገኝባቸው አጋጣሚዎች በርካታ ናቸው፡፡ አጥቂው ከ10 ቁጥሩ ማግኘት የነበረበትን ድጋፍ ማግኘት ያልቻለውም በመሰል የአዳነ የቦታ አያያዝ ህፀፅ ምክንያት ነው፡፡ በእርግጥ የተጋጣሚው ንግድ ባንክ የተጠቀጠቀ የመከላከል ስልት (compact defending system) ከፍተኛውን አስተዋፅኦ ይወስዳል፡፡ ሆኖም ፈረሰኞቹ ከ play maker ሊያገኙ የሚገባቸው ክፍተቶችን የመጠቀም ፣ ተከላካይ ሰንጣቂ ኳሶችን ለአጥቂው ማድረስ እና የጨዋታ ፍሰትን የመቆጣጠር ጥቅሞችን ከአዳነ ሊያገኙ አልቻሉም፡፡

(ምስል – 3)

1ccc

በጊዮርጊስ የተከላካይ አማካዮች እና የአጥቂ አማካዮች መካከል የነበረው ክፍተት

ሁለቱ የጊዮርጊስ የተከላካይ አማካዮች (ተስፋዬ እና ምንተስኖት) እጅግ ወደኋላ ባፈገፈገው ሚናቸው እና በጨዋታው በነበራቸው ቦታ እንዲሁም ይበልጥ የአጥቂውን መስመር ተጠግቶ በነበረው የማጥቃት አማካዮች (ዳዋ ፣ አዳነ ፣ በኃይሉ) መካከል ሰፊ ክፍተት እና ረጅም ርቀት (በሜዳው ቁመት – vertical distance ) ነበር፡፡ ዳዋ እና ቱሳ የኳስ አቅጣጫን ባማከለው እንቅስቀሴያቸው (ball oriented movement) መስመራቸውን ወደ ጎን እና ወደላይ በመለጠጥ ለቡድናቸው ስፋት እና ጥልቅት ለማስገኘት ሲሞክሩ ታይቷል፡፡

አዳነም ለብሪያን በአግድሞሽ መስመር ቀርቦ በመጫወቱ በጊዮርጊሶች 4-2-3-1 በ2ኛው እና በ3ኛው መስመር መካከል ያለው ርቀት ሊሰፋ ችሏል፡፡ አልፎ አልፎ ምንተስኖት ከአግድሞሽ የተከላካይ አማካይነት እየወጣና ወደፊት እየተጠጋ ያንን ክፍተት በመጠኑ ሊሸፍን ቢሞክርም በአብዛኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ክፍተቱ ግልፅ ሆኖ ይታይ ነበር፡፡

በእርግጥ በሁለተኛው አጋማሽ ምንተስኖት በተሸለ ወደፊት ቀርቦ መጫወት ችሏል፡፡ በእረፍት ሰአት አሰልጣኞቹ በዚህ ላይ መጠነኛ ማስተካከያ ያደረጉ በሚመስል መልኩ በ57ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር በቱሳ አማካኝነት በረጅሙ ወደ ባንክ የግብ ክልል (በግራ) የተላከችን ኳስ ተመልሳ ወደ ቀኙ የግብ ክልል ስትመጣ ምንተስኖት አስቆጥሮ ቡድኑን አቻ ለማድረግ ችሏል፡፡

ለግቡ መቆጠር የጊዮርጊሶች ወሳኝ ተጫዋች የሆነው በኃይሉ ጥረት ከፍተኛውን ድርሻ ቢወስድም የንግድ ባንኩ ሲሳይ ቶሊ ደካማ የመከላከል እና የቦታ አጠባበቅ አይነተኛ አስተዋፅኦ ነበረው፡፡ ሲሳይ በcit inside እንቅስቃሴ በተደጋጋሚ ወደ ውስጥ ሲገባ ኳላ የነበረው የግራ መስመር ፉልባክ (አለምነህ) በቀላሉ ተጋላጭ ሲሆን ይታይ ነበር፡፡ ለግቧ መቆጠር ምክንያ የሆነችው የቱሳ ተሸጋሪ ኳስም ከዚህ ስፍራ ከተገኘ ነፃ ክፍተት የመጣ ነው፡፡ ቱሳ በረጅሙ ወደ ባንክ የግብ ክልል ሲልካት ሰፊ ጊዜ እና ነፃ ቦታ ነበረው፡፡

ሆኖም ጊዮርጊስ በ2ኛው አጋማሽ aggressive ሆኖ ከመቅረቡ ውጪ የነበረውን ክፍተት በጥሩ ሁኔታ የማጥበብ አማራጭ አለመውሰዱ ንግድ ባንኮች በመሃል ሜዳ ላይ መጠነኛ የሆነ ብልጫ እንዲያሳዩ አድርጓቸዋል፡፡ በሰፊው ክፍተት ባይጠቀሙም በቁጥር ከጊዮርጊስ የተሸሉ ተጫዋቾችን በመሃል ሜዳው ላይ የሚያገኙበትን ሂደት ሲፈጥሩ ነበር፡፡ ይህም የበዙ interceptions እንዲያገኙ አድርጓቸዋል፡፡

(ምስል – 4)

1dddddddddd

ያጋሩ