ጋቦን 2017፡ የአሊያን ትራኦሬ ድንቅ የቅጣት ምት ግብ ቡርኪናፋሶን አሸናፊ አድርጓል

በጋቦን አስተናጋጅነት ሲደረግ የነበረው የቶታል የአፍሪካ ዋንጫ ቅዳመ ምሽት በደረጃ ጨዋታ ጋና እና ቡርኪናፋሶን አገናኝቷል፡፡ ፈረሰኞቹን በመጨረሻ ደቂቃ የተቆጠረች ግብ የሶስተኛ ደረጃነት እንዲያገኙ አስችላለች፡፡ የደረጃ ጨዋታው የተካሄደው በፖር ዠንቲል ነው፡፡

እንደቀደምት የደረጃ ጨዋታዎች በግብ ሙከራ ባልታጀበው ጨዋታ ጋና ካሜሮንን ከገጠመው ቡድኗ የተወሰነ ቅያሪ ስታደርግ ቡርኪናፋሶ እምብዛም በአሰላለፏ ላይ ለውጥ አላደረገችም፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ ጥቂት የግብ ማግባት ሙከራዎች ብቻ ታይተዋል፡፡ ቶማስ ፓርቴ ጥቋቁር ከዋክብቶቹ በመጀመሪያው 45 ቀዳሚ መሆን የሚችሉበትን እድል አግኝቶ የግቡ አግዳሚ መልሶበታል፡፡ በተቃራኒው ግብ ክልል ፕሪጁስ ናኮልማ ያገኘውን እድል አምክኗል፡፡ ጋና በሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ የግብ ሙከራዎችን ብታደርግም የአጨራረስ ድክመት ዋጋ አስከፍሏታል፡፡ በ88ኛው ደቂቃ በቀኝ መስመር በኩል የተሰጠውን የቅጣት ምት አማካዩ አሊያን ትራኦሬ በቀጥታ በመምታት በግሩም ሁኔታ በሪቻርድ ኦፎሪ መረብ ላይ አሳርፏል፡፡ የትራኦሬ ግብ ቡርኪናፋሶን በአፍሪካ ዋንጫው ታሪክ ያስመዘገበችው ሁለተኛዋ ትልቅ ውጤት እንዲሆን አድርጓል፡፡ ቡርኪናፋሶ በ2013 ለፍፃሜ ከበቃችት ውጤቷ ቀጥሎ የ2017ቱ ሶስተኛ ደረጃነት ትልቁ ውጤቷ ነው፡፡ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ በካፍ የተመረጠው የቡርኪናፋሶው ቱሬ ነው፡፡

የአራት ግዜ የአፍሪካ ቻምፒዮኗ ጋና እና እስራኤላዊው አሰልጣኝ አቭራም ግራንት በጥቋቁር ከዋክብቶቹ አፍሪካ ዋንጫ ያልተሳካ ጉዞ በኃላ አብሮ መቀጠል ጉዳይ አጠራጣሪ አድርጓታል፡፡ ጫና ውስጥ የሚገኙት ግራንት በስራ ገበታቸው ይለቃሉ የሚሉ መረጃዎች በጋና መናፈሳቸውን ቀጥለዋል፡፡ ከአፍሪካ ዋንጫው ጉዞቸው በምድብ እና በሩብ ፍፃሜ ላይ የተገተው ዚምባቡዌ፣ አልጄሪያ፣ ኮትዲቯር እና ቱኒዚያ ከዋና አሰልጣኞቻቸው ጋር ተለያይተዋል፡፡ የዚምባቡዌው ካሊስቶ ፓስዋ፣ አልጄሪያው ጆርጅ ሊከንስ፣ የኮትዲቯሩ ሚሸል ዱሰየር እና የቱኒዚያው ሄነሪ ካስፐርዛክ በገዛ ፍቃዳቸው ከስራ ገበታቸው ተነስተዋል፡፡

የፍፃሜ ጨዋታው ሊበርቪል ላይ በሚገኘው ስታደ ደ አሚቴ ምሽት 4፡00 ላይ በካሜሮን እና ግብፅ መካከል ይደረጋል፡፡

 

የፎቶ ምንጭ: AFP, Getty Images

 

Leave a Reply