በአሠልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ የሚመሩት መከላከያዎች የዝውውር መስኮቱ ከመዘጋቱ በፊት ሁለት ተጫዋቾችን አስፈርመዋል።
አዲሱ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ክለብ መከላከያ ሊጉ ከመጀመሩ በፊት በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ውድድር እየተሳተፈ እንደሆነ ይታወቃል። በርካታ ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ በመቀላቀል ለዋናው ውድድር እየተዘጋጀ የሚገኘው ክለቡም በዛሬው ዕለት የሁለት ተጫዋቾችን ዝውውር ማገባደዱን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።
የመጀመሪያው ተጫዋች አኩዌር ቻም ነው። ባለፈው የውድድር ዓመት የደሴ ከተማ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ የነበረው አኩዌር ከደደቢት ተስፋ ቡድን አድጎ በዋናው ቡድን እስከ 2011 የቆየ ሲሆን በመቀጠል ለደሴ ከተማ ሲጫወት ቆይቷል። አሁን ደግሞ በጦሩ ቤት የእግርኳስ ህይወቱን ለመቀጠል ፊርማውን አኑሯል።
ሁለተኛው ተጫዋች ደግሞ ኪም ላም ነው። ኪም ከሳምንታት በፊት ሀዋሳ ላይ በተካሄደው የክልል ክለቦች ሻምፒዮና ውድድር ላይ ጋምቤላን ወክሎ የተጫወተ ሲሆን በውድድሩ ላይም መከላከያዎች ተመልክተውት ወደ ስብስባቸው ቀላቅለውታል። ሁለቱም ተጫዋቾች በዛሬው ዕለት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ተገኝተው የአንድ ዓመት ውል ፈርመዋል።