ጅማ አባ ጅፋር ሁለት ተጫዋቾችን አስፈርሟል

የምዕራብ ኢትዮጵያው ክለብ በዝውውሩ መዝጊያ ቀን በስብስቡ ላይ ሁለት ተጫዋቾችን ጨምሯል።

ከአዲሱ የውድድር ዓመት መጀመር አስቀድሞ በርከት ያሉ ተጫዋቾችን በማስፈረም ቡድኑን እየገነባ ያለው ጅማ አባ ጅፋር በዝውውር መስኮቱ የመጨረሻ ቀን ላይ አንድ የሀገር ውስጥ እና አንድ የውጪ ተጫዋቾችን በእጁ አስገብቷል። ኢትዮጵያዊው አዲሱ የጅማ አባ ጅፋር ተጫዋች ከባህር ዳር ከተማ ጋር ቀሪ የአንድ ዓመት ውል ቢኖረውም በስምምነት የተለያየው ሚኪያስ ግርማ ነው። በቀኝ መስመር ተከላካይነት እና አማካይነት በመሰለፍ የሚታወቀው ተጫዋቹ መነሻውን ከቅዱስ ጊዮርጊስ አድርጎ በድሬዳዋ ከተማ እና በባህር ዳር ከተማ ተጫውቶ ማሳለፉ ሲታወስ በ2014ቱ የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ደግሞ በጅማ አባ ጅፋር መለያ የምንመለከተው ይሆናል።

ሌላኛው የክለቡ አዲስ ፈራሚ ካሜሩናዊው ሮጀር ማላ ነው። በአማካይ ቦታ ላይ የሚጫወተው ሮጀር ንጃላ ክዋን እና ለሞዛምቢኩ ዩፒ ዲ ማንሲያ የተጫወተ ሲሆን ከ2012 ጀምሮ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ለሀላባ ከተማ ሲጫወት ቆይቷል።