የጨዋታ ሪፖርት | አርባምንጭ ከ ኢትዮጵያ ቡና ነጥብ ተጋርተዋል

ተመስገን ማሞ | ከአርባምንጭ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 1ኛ ዙር የመጨረሻ ሳምንት አርባምንጭ ላይ አርባምንጭ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና ተጫውተው ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተለያይተዋል፡፡

በጨዋታው ለወትሮው ከተለመደው እጅግ በላቀ መልኩ ቁጥሩ የበዛ ተመልካች ወደ ሜዳ የገባ ሲሆን የቡና ደጋፊዎች ሲጨመሩ የአርባምንጭ ስታድየም በተመልካች ተጨናንቆ ነበር፡፡

በገብረሚካኤል ያዕቆብ አማካኝነት በተጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የመጀመርያዎቹ 15 ደቂቃዎች ጫና ፈጥረው ለመጫወት ሞክረዋል፡፡ የግብ ሙከራ ማድረግ የቻሉትም ገና በመጀመርያው ደቂቃ ነበር፡፡ ወንድሜነህ ዘሪሁን የቡና ተከላካዮችን ትኩረት ማጣት ተከትሎ ያገኘውን ኳስ ከፍጹም ቅጣት ምት ክልል ውጪ ሞክሮ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቶበታል፡፡

ከ15 ደቂቃዎች በኋላ ኢትዮጵያ ቡናዎች ቀስ በቀስ ጨዋታውና  መቆጣጠር ችለዋል፡፡ ለዚህም መሀል ሜዳው ላይ ጋቶች ፓኖም እና እያሱ ታምሩ ትልቁኅ ሚና ተጫውተዋል፡፡ በ23ኛው ደቂቃ እያሱ ከቀኝ መስመር ቆርጦ በመግባት መሬት ለመሬት መትቶ የሞከራት ኳስ የአርባምንጭ ደጋፊን ያስደነገጠች ሙከራ ነበረች፡፡ የተመታው ኳስ ጥንካሬ ባይኖረውም ግብ ጠባቂው ጋር ሲደርስ በሜዳው ምክንያት ነጥሮ አቅጣጫ በመቀየር አንተነህን ገጭቶ ተመልሷል፡፡

ከ23ኛው ደቂቃ በኋላ ጨዋታው እየተቀዛቀዘ መጥቶ ብዙም የግብ ሙከራ ሊታይበት አልቻለም፡፡ አርባምንጮች በመስመር ተከላካዮቻቸው በተለይም በወርቅይታደል አበበ አማካኝነት በተሻጋሪ ኳስች የግብ እድል ለመፍጠር ጥረት ቢያደርጉም ያን ያህል አስደንጋጭ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም፡፡

በ41ኛው ደቂቃ በኤልያስ ማሞ ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኘውን ቅጣት ምት ጋቶች ሞክሮ በአንተነህ የተያዘበት ኳስ በቡና በኩል በመጀመርያው አጋማሽ የሚጠቀስ ሙከራ ነበር፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ኢትዮጵያ ቡና በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ የተሻለ ተንቀሳቅሰዋል፡፡ አርባምንጮች በበኩላቸው በመስመሮች በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ በማተኮር በተሻጋሪ ኳሶች ለመጫወት ሞክረዋል፡፡ በ60ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት የተሻማውና በቡና ተከላካዮች ስህተት ግብ ለመሆን የተቃረበው ኳስ የጥረታቸው ማሳያ ነበር፡፡

እንደ መጀመርያው ሁሉ የ2ኛው አጋማሽም በሙከራ ያልታጀበ ነበር፡፡ ይልቁንም በተደጋጋሚ በዳኛ ፊሽካ እየተቆራረጠ አሰልቺ መልክን ይዞ ጨዋታው ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተፈጽሟል፡፡

በባለሜዳዎቹ አርባምንጮች በኩል የመስመር ተከላካዩ ወርቅይታደል አበበ ሚዛናዊ በሆነ የመከላከል እና የማጥቃት እንቅስቃሴው ፣ አማካዩ ምንተስኖት አበራ የቡናን የአማካይ ክፍል እንቅስቃሴ በመግታት ጥሩ ተንቀሳቅሰዋል፡፡ በኢትዮጵያ ቡና በኩል ደግሞ የኤፍሬም ወንድወሰን እና ወንድይፍራው ጌታሁን ጥምረት የተዋጣለት ነበር፡፡

1 Comment

  1. እርማት በዚህ ጨዋታ ኢኮ ፌቨር ያልተሰለፈ መሆኑን እና የቡና የመከላከል ቀጠና በኤፍሬም እና ውንዳፍራው ቦርጠና የተመራ መሆኑን በመግለፅ ነው። (ይስተካከል )

Leave a Reply