​የጨዋታ ሪፖርት | ደደቢት ደረጃውን ያሻሻለበትን ድል አስመዝግቧል

በ15ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ወላይታ ድቻን አበበ ቢቂላ ስታድየም ላይ ያስተናገደው ወላይታ ድቻ 3-0 በማሸነፍ ወደ ድል ተመልሷል፡፡ 

እንደ ሌሎች ጨዋታዎች ሁሉ የአለም የትራፊክ አደጋ ቀንን በማስመልከት በትራፊክ አደጋ ህይወታቸውን ለሚያጡ ሰዎች የህሊና ጸሎት በማድረግ የተጀመረው ጨዋታ ፈጣን እንቅስቃሴ እና የተመልካች ድባብ የደመቀ እንቅስቃሴ ታይቶበታል፡፡

የጨዋታው የመጀመርያ 20 ደቂቃዎች በሁለቱም በኩል ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ተስተውሎበታል፡፡ ደደቢት በሽመክት ጉግሳ እና በጌታነህ ከበደ አማካኝነት የግብ ሙከራ ሲያደርግ ወላይታ ድቻ በአላዛር ፋሲካ አማካኝነት ለግብ እጅግ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ችሎ ነበር፡፡ 

በ20ኛው ደቂቃ በድቻ ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ የተሰጠውን ሁለተኛ ቅጣት ምት ጌታነህ ከበደ መትቶ ግብ ጠባቂው ወንድወሰን ሲመልሰው አቤል እንዳለ አግኝቶት ወደ ግብነት በመቀየር ሰማያዊዎቹን ቀዳሚ አድርጓል፡፡ 

ከ2 ደቂቃዎች በኋላ ጌታነህ ከበደ ግብ ጠባቂው ወንድወሰንን በማለፍ ደደቢት 2-0 መምራት የቻለበትን ግብ አስቆጥሯል፡፡ ጌታነህ የግብ መጠኑን 11 በማድረስ የሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት መምራቱንም ቀጥሏል፡፡

ከግቦቹ በኋላ በሙከራዎች ባይታጀብም በሁለቱም በኩል ወደ ግብ ለመቅረብ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ መልካም ነበር፡፡ የመጀመርያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የተጠናቀቀውም በደደቢት 2-0 መሪነት ነበር፡፡

ሁለተኛው አጋማሽ ወላይታ ድቻ ኳስ ተቆጣጥሮ በፍጥነት ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን ግብ ለማግኘት ጥረት ቢያደርጉም ጥሩ ጥምረት ያሳዩት አክሊሉ እና አይናለምን ማለፍ አልቻሉም፡፡ 

ደደቢቶች በአንጻሩ በመልሶ ማጥቃት በቀላሉ ወደ ወላይታ ድቻ የግብ ክልል ሲደርሱ ተስተውሏል፡፡ በ62ኛው ደቂቃ ላይም ሽመክት ጉግሳ በመልሶ ማጥቃት የመጣውን ኳስ በጥሩ ሁኔታ በግራ እግሩ አክርሮ በመምታት የደደቢትን 3ኛ ግብ አስቆጥሯል፡፡ ሽመክት ጉግሳ በቀድሞ ክለቡ ላይ ግብ ማስቆጠሩን ተከትሎ ደስታውን ከመግለጽ ተቆጥቧል፡፡

ወላይታ ድቻዎች በ66ኛው ደቂቃ ውጤቱን ሊያያጠቡበት የሚችሉበት የፍጹም ቅጣት ምት ቢያገኙም ተቀይሮ የገባው መሳይ አንጪሶ መትቶ ክሌመንት አዞንቶ መልሶበታል፡፡ የተመለሰውን ኳስ ዳግም ንጉሴ አግኝቶ ቢሞክርም የግቡን አግዳሚ ለትሞ ተመልሷል፡፡

ደደቢት ጨዋታውን 4-0 ለማሸነፍ የሚያስችለውን ግልጽ የግብ እድል ጌታነህ በራሱ ጥረት ፈጥሮ ቢሞክርም ወንድወሰን አሸናፊ አድኖበት ጨዋታው በደደቢት 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

Leave a Reply