የፕሪሚየር ሊጉ 2ኛ ዙር ተጀምሯል፡፡ ከድሎች እና የደረጃ ለውጦች ባሻገር ምን ምን ተመለከትን ሶከር ኢትዮጵያ በ14ኛው ሳምንት ዙርያ 5 ጉዳዮችን በማንሳት በመጠኑ ትዳስሳለች፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊገዳደሩት የማይችሉት ክለብ ሆኗል
ሙገር ሲሚንቶ በኢትዮጵያ ዋንጫ ኢትዮጵያ ቡናን ውድድር አስወጥቶ ግማሽ ፍፃሜውን ሲቀላቀል አብዛኛው የስፖርት ቤተሰብ በውጤቱ ተደንቆ ነበር፡፡ ከ5 ቀናት በኋላ ግን ቅዱስ ጊዮርጊስ ፍፁም የበላይነት አሳይቶ 4-0 አሸንፏል፡፡ ከጨዋታው በኋላ የሙገሩ አሰልጣኝ ግርማ ኃ/ዮሃንስ ‹‹ በስነ-ልቡናው ተሸንፈን ገብተናል ›› ብለው የሰጡት አስተያየት የዘንድሮውን ቅዱስ ጊዮርጊስ አስፈሪነት በግልፅ ያሳያል፡፡ በስብስብ ትልቀት ብቻ ሳይሆን በተጫዋቾች ጥራት ፣ በሁለገብ ተጫዋቾች እና በተሰጥኦ የተትረፈረፈ ስብስብን ለመግጠም ወደ ሜዳ የሚገባ ቡድን በስነ-ልቡናው ተሸንፎ ቢገባ የሚያስገርም አይሆንም፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ግቦች ለማዝነብ አይቸገርም ፤ አንድ ግብ አስቆጥረው አስጠብቀው ጨዋታውን ለመጨረስም እንደዛው፡፡ ፈረሰኞች ጨዋታ ቢከብዳቸው እንኳን የአሸናፊነት ስነ-ልቡናውቸው ጨዋታ አሸንፎላቸው ይወጣል፡፡ ቀሪዎቹን ጨዋታዎች በተጠባባቂዎች ቢጫወት እንኳን ይኸው የአሸናፊነት አእምሯቸው ከተሰላፊዎቹ በበለጠ ወሳኝ ተጫዋቻቸው ነው፡፡
ኢትዮጵያ ቡና በወጥ አቋሙ ዘልቋል
አደገኞቹ ጨዋታውን በጋለ የማሸነፍ ስሜት ተጫውተው አሸንፈዋል፡፡ በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች የትኩረት ማጣት እና ደካማ የመከላከል ውህደት የታየበት ቡናን ደደቢቶች በግቦች አለመቅጣታቸው እድለኛ ቢያሰኛቸውም የጨዋታውን 2/3ኛ በሚገባ ተቆጣጥረው አሸንፈዋል፡፡ ኢትዮጵያ ቡናን በተለይም በአማካይ ክፍል ልቆ መገኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ ትላንት ጋብሬል ሻይቡ እና ሳምሶን ጥላሁን ላይ የታየውም ይኸው ነበር፡፡ ጨዋታ ሲቆጣጠር አስደናቂ የሆነው ፋሲካ አስፋው የሜዳ ላይ መሪ ነበር፡፡ የመስኡድ መሃመድ አንድ ሁለት ቅብብል እና ጨዋታውን የሚያፈጥንበት መንገድ ድንቅ ነበር፡፡ ከጉዳት የተመለሰው ዳዊት እስጢፋኖስ ደግሞ ትላንት ‹‹ CLASSIC >> ነበር:: ሁለት ግሩም ግቦች ሲያስቆጥር የመጀመርያዋ በፕሪሚየር ሊጉ ያልተለመደች አይነት ነበረች፡፡
ሲዳማ ቡናን በሜዳው የሚደፍረው ጠፍቷል
ውድድር አመቱ መጀመርያ ሲዳማ ቡና የነበረበትን ደረጃ ለተመለከተ አሁን ያሳየው መሻሻል አስገራሚ ነው፡፡ የተደራጀ ቡድን መገንባት የሚችሉበት ቆፍጣናው አሰልጣኝ ቀስ በቀስ የራሳቸውን ቡድን እየሰሩ ነው፡፡ በቅርብ ጊዜያት የተመዘገቡት ጨዋዎችን ብንመለከት እነኳን በቅዱስ ጊዮርጊስ በጥሎ ማለፉ የተሸነፉት በመጨረሻው ደቂቃ ነው፡፡ ደደቢት ፣ ሙገር እና መድንን አሸንፎ ሽቅብ መውጣቱን ቀጥሏል፡፡ ዘላለም ሽፈራው በተለይ በሜዳቸው ውጤት የማግኘት ቀመሩን አግኝተውታል፡፡ እስካሁን ካገኙት 19 ነጥቦች 18 ነጥቦች የሰበሰቡት በሜዳቸው ነው፡፡ በዚህ ሳምንት በይርጋለም የተሰዋው ደግሞ መከላከያ ነው፡፡
ያለመውረድ ትግሉ ዘንድሮ ብዙ ክለቦችን ያሳትፋል
ሁለተኛው ዙር ከሻምፒዮንነቱ በተሻለ ላለመውረድ የሚደረገው ትግል አጓጊ ይሆናል ተብሎ ይታሰባል፡፡ እስካሁን 14 ሳምንታት በተካሄዱበት ፕሪሚየር ሊግ በደረጃ ሰንጠረዡ ወገብ (7ኛ) ላይ በሚገኘው መከላከያ እና በመጨረሻ ደረጃ ላይ በሚገኘው ኢትዮጵያ መድን መሃከል ያለው የነጥብ ልዩነት 10 ብቻ ነው፡፡ ቁጥሩ ለበርካቶች ብዙ ቢሆንም ተገማች ባልሆነው ፕሪሚየር ሊግ 10 ነጥብ እጅግ ጠባብ ርቀት ነው፡፡ አስገራሚው ነገር በ4ኝነት የተቀመጠው ደደቢት ከመሪው ጋር ካለው ርቀት ይልቅ ከመጨረሻው ጋር ያለው ርቀት ጠባብ ነው፡፡ ከቅዱስ ጊዮርጊስ በ18 ነጥቦች አንሶ 4ኛ ላይ የተቀመጠው ደደቢት ከኢትዮጵያ መድን የራቀው ግን በ13 ነጥቦች ነው፡፡ የ14ኛው ሳምንት ጨዋታዎች ውጤትም ሐዋሳ ከነማን እና ሙገር ሲሚንቶን ላለመውረድ ወደሚደረገው ፉክክር ጋብዟቸዋል፡፡
መብራት ኃይል በመጠኑ እየተነሳ ነው
ዮርዳን ስቶይኮቭ የለቀቁትን መንበር በድጋሚ ከተረከቡ በኋላ ማንሰራራት ጀምሯል፡፡ ታክቲክ አዋቂነታቸው እና የአሰልጣኝነት ብቃታቸው በፕሪሚየር ሊግ ተከታታዮች ዘንድ ጭቅችቅ የሚፈጥሩት ዮርዳን ቡድኑን ለማሻሻል የወሰዱት እርምጃ ቡድኑን እያነሳሳው ነው፡፡ በተለይም አብዱልከሪም ሀሰንን ወደ ቋሚ አሰላለፍ የመለሱበት ውሳኔ ውጤት እያስገኘላቸው ነው፡፡ የቀድሞው የቅዱስ ጊዮርጊስ አማካይ ባለፉት 4 ጨዋዎች ሶስት ግቦች ከመረብ ሲያሳርፍ የማጥቃት እንቅስቃሴው ዋነኛ ተዋናይ ሆኗል፡፡ ቡድኑም ካለፉት 4 ጨዋታዎች ያገኘው ነጥብን ያህል በሙሉው የውድድር ዘመን እንዳላሳካ ስናስብ የታሪካዊው ክለብ ያለመውረድ ትግል መልካም ዜና ነው፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከስታስቲክሶች በተቃራኒው የቆመ የማይገመት ሊግ ነው፡፡