የአሰልጣኞች አስተያየት | መከላከያ 0-0 ሲዳማ ቡና

በአዲስ አበባ ስታድየም ሲዳማ ቡናን ያስተናገደው መከላከያ ያለ ግብ አቻ ተለያይቷል፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የሁለቱም ክለቦች አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

የመከላከያ አሰልጣኝ ሻለቃ በለጠ ገብረኪዳን

ስለጨዋታው

“ያጋጠመንን እድል ባለመጠቀማችን ነጥብ ጥለን ልንወጣ ችለናል፡፡ ከነሱ የተሻለ ጥሩ እድሎች አጋጥመውናል፡፡ እነሱም ብዙም የሞከሩት ሙከራ አልነበረም፡፡ ግን በአጠቃቀም ችግር ምክንያት አቻ ልንወጣ ችለናል፡፡”

“የአጨራረስ ችግር አለብን፡፡ እዚህ ላይ ጠንክረን እየሰራን ነው፡፡ እንጂ የአጥቂዎች ክፍተት አይደለም፡፡ ምክንያቱም ተከላካዩም ያገባል፡፡ የግድ ከአጥቂ አይደለም መጠበቅ ያለብን፡፡ እግርኳስ ጨዋታ መከላከልን እና ማጥቃት እስከሆነ ድረስ ጥሩ እድሎችን ፈጥረናል፡፡ የአጠቃቀም ችግር ግን አለብን፡፡ ጨዋታው ላይ ግን የተሻልን ነበርን፡፡ ውጤት ይዘን ልንወጣ ይገባን ነበር ሆኖም ግን አልተሳካም፡፡”

ስለሁለተኛ ዙር

“በሁለተኛው ዙር ከአሁኑ ተሽለን እንመጣለን ብዬ አስባለው፡፡ ጉዳት ላይ የነበሩ ልጆችም ድነውልን ይመጣሉ፡፡ ጥሩ ነገር ይዘን እንመጣለን ብዬ አስባለው፡፡”

“አዳዲስ ተጫዋች የማምጣት ሃሳብ የለንም፡፡ ምክንያቱም ጉዳት ላይ የነበሩ ተጫዋቾች ነበሩ ፤ እንደነ ባዬ አይነት፡፡ ስለዚህ እነዚህ ተጫዋቾች ከጉዳት ሲመለሱ ጥሩ ግልጋሎት እናገኛለን ብዬ አስባለው፡፡ አዲስ ተጫዋች የማምጣት እቅድ የለንም፡፡”

የሲዳማ ቡና አሰልጣኝ አለማየሁ አባይነህ

ስለጨዋታው

“በዛሬው ጨዋታ ከነበረው ሂደት ያለንን ነገር አለማጣት ነበር እቅዳችን፡፡ ምክንያቱም ከሜዳችን ውጪ እንደመጫወታችን መጠን ተጋጣሚያችን ጠንከራ ነው፡፡ ይዘነው የገባነው የጨዋታ ስልት በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ነው፡፡ ይህንን ስርዓት እንድንጠቀም ያደረገን መሃል ሜዳ ላይ ጥሩ ይንቀሳቀስ የነበረው ሙሉ አለም በጉዳት ስለወጣ ነው፡፡ በቦታው ወጣት እና አዲስ ልጅ ነው የተጠቀምነው፡፡ በመልሶ ማጥቃት ሂደት ውስጥ አጋጣሚዎችን ፈጥረናል፡፡ መጠቀም አልቻልንም፡፡ እነዚህ አጋጣሚዎችን መጠቀም ብንችል አሸንፈን እንወጣ ነበር፡፡ በእንቅስቃሴ ደረጃ ይዘነው የገባነውን ነገር ልጆቼ ተግብረውታል ብዬ አስባለው፡:”

ከሜዳ ውጪ የሲዳማ ቡና የዘንድሮ አቋም

“ከሜዳ ውጪ ያለን ሪከርድ በተወሰነ መልኩ ጥሩ አይደለም፡፡ በአንደኛው ዙር በሜዳችን ምንም ዓይነት ጨዋታ አልተሸነፍንም፡፡ ስለዚህ ይህንንም ስናረግ የነበረው ጥንቃቄ አጥቅተን እንጫወታለን ብለን በምንፈጥራቸው ስህተቶች ግቦች የተቆጠሩብን እና ከሜዳችን ውጪ ልንሸነፍ የቻልነው፡፡ ጥንቃቄ ያለበት ጨዋታ ተጫውተን ባገኘነው አጋጣሚ በመልሶ ማጥቃት ነው ልንጫወት የመጣነው፡፡ ይህም ከሜዳ ውጪ የተጫወትንበት የአጨዋወት ስርዓት ነው፡፡ ውጤታማ አድርጎናል፤ አንድ ነጥብ ቀላል አይደለም፡፡ ስለዚህ ይህንን ደግሞ በሁለተኛው ዙር በተሻለ መልኩ ሰርተን ከሜዳ ውጪ ያለንን ሪከርድ ማስተካከል ከቻልን ተፎካካሪ ሆነን የማንጨርስበት ምንም ምክንያት የለም፡፡”

Leave a Reply