የአሰልጣኞች አስተያየት | ኢትዮ-ኤሌክትሪክ 2-0 ሃዋሳ ከተማ

ሃዋሳ ከተማን በአዲስ አበባ ስታድየም ያስተናገደው ኢትዮ-ኤሌክትሪክ በፍፁም ገብረማሪያም የመጀመሪያ አጋማሽ ሁለት ግቦች ታግዞ 2-0 አሸንፎ ወጥቷል፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የሁለቱም ክለብ አሰልጣኞች ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

የኢትዮ-ኤሌክትሪክ አሰልጣኝ ብርሃኑ ባዩ

ስለጨዋታው

“ጨዋታው ጥሩ ነው፡፡ ሚዛናዊ ጨዋታ ነው፡፡ ያገኘነውን ኳሶች ማግባት ችለናል፡፡ በተረፈ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ነበር፡፡ ሁለታችንም ኳስን እንጫወታለን፡፡”

በሁለተኛው አጋማሽ የተፈጠሩ እድሎችን አለመጠቀም

“ይህ ቋሚ ችግር ነው፡፡ አጥቂዎቻችንም ከመጀመሪያ ጀምሮ የነበሩ ልጆች ናቸው፡፡ በራስ መተማመኑ ላይ አሁንም ችግር አለ፡፡ እድዛም ሆኖ ግን ካለፉት ግዜያት ይሻላል፡፡ የተገኙት ድሎች ይጠቅሙናል፡፡”

ስለኤሌክትሪክ የአንደኛ ዙር ጉዞ

“በየትኛውም ጨዋታ እኛ በጨዋታ እንቅስቃሴ ተበልጠን ወጥተን አናውቅም፡፡ በአምስት ጨዋታዎች እየመራን ሁለቱን ተሸንፈንበታል ሶስቱን አቻ ወጥተል፡፡ በጥቃቅን ስህተቶች ግብ ይቆጠርብናል፡፡ ያገኘናቸውን በርካታ ኳሶች መጠቀም አልቻልንም፡፡”

የሃዋሳ ከተማ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ

ስለጨዋታው

“ጨዋታው ከጠበቅነው ውጪ ነው፡፡ ነጥብ ይዘን ለመሄድ ነበር አመጣጣችን፡፡ ግን ከእረፍት በፊት በፍፁም ጨዋታውን መቆጣጠር አልቻልንም ነበር፡፡ በተለይ መከላከሉ ላይ፡፡ በጣም ክፍት ነበርን ማለት ይቻላል፡፡ እነሱ ያገኙነትን ሁለት አጋጣሚ በቀላሉ ግብ ማስቆጠር ችለዋል፡፡ ከዛ በኃላ ከባድ ነበር፡፡ ከእረፍት በኃላ ሙሉ በሙሉ ጫና ፈጥረን ለመጫወት ሞክረናል፡፡ እነሱም ከምራታቸው አንፃር ያንን ለማስጠበቅ ብዙም ወደፊት የመምጣት ነገር አልነበራቸውም፡፡ ያገኘናቸውንም እድሎች ወደጎል መቀየሩ ላይ አልተሳካልንም፡፡”

ስለሁለተኛው ዙር

“ለሁለተኛው ዙር የተወሰኑ ተጫዋቾችን ለማዛወር ጥረት እያደረግን ነው፡፡ በመከላከሉ በኩል ያሉትን ክፍተቶች ለመድፈን ጥረት እናደርጋለን፡፡ ምክንያቱም የፈለግከውን ያህል ስትጫወት ብትቆይ ቀኑን ሙሉ ኳስ ከአንተ ጋር አይቆይም፡፡ ያው በተነጠቅክ ሰዓት ደግሞ ቀጥታ ጎልህ ክፍት ከሆነ የመሸነፍ እድልህን ሰፊ ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ክፍተታችንን ለመድፈን እንሰራለን ብዬ ነው ማስበው፡፡”

“የአጥቂ መስመር ላይም እንደዚሁ ተጫዋቾችን ለማስፈረም ጥረት እያደረግን ነው፡፡ ይሳካልናልን ብለን እናስባለን፡፡ ካለንበት ዞን ለመውጣት በየአቅጣጫው የተሻሉ ልጆች ያስፈልጉናል፡፡ ስለዚህ ካሉት ጋር የበለጠ ሊያግዙን የሚችሉ ተጫዋቾች ለመቀላቀል እንሞክራለን፡፡ ይህንን እየሰራንበት ነው፡፡”

Leave a Reply