ጋቦን 2017፡ ካሜሮን የአፍሪካ ቻምፒዮን ሆነች

በጋቦን አስተናጋጅነት ሲደረግ የነበረው የ31ኛው የቶታል የአፍሪካ ዋንጫ ዕሁድ ምሽት በሊበርቪል በሚገኘው ስታደ አሚቴ ፍፃሜውን ሲያገኝ ካሜሮን ከ15 ዓመታት በኃላ ለመጀመሪያ ግዜ የአፍሪካ ዋንጫን ማሸነፍ ችላለች፡፡ የማይበገሩት አንበሶቹ ግብፅን ከኃላ ተነስተው 2-1 በመርታት ለአምስተኛ ግዜ አፍሪካ ዋንጫን ማሸነፍ ችለዋል፡፡

የቦነስ ክፍያ ጉዳዮች እና የከዋክብት ተጫዋቾች ጥሪ አለመቀበል ካሜሮንን ቢፈትኗትም በስተመጨረሻም በቤልጄማዊው አሰልጣኝ ሁጎ ብሮስ እየተመራች ዋንጫን አንስታለች፡፡ በፍፃሜው ጨዋታ ከአንድ ግብ በላይ ሲቆጠር ይህ ከ2004 ወዲህ ለመጀመሪያ ግዜ ነው፡፡

የግብፅ በጥብቅ መከላከል እንዲሁም የካሜሮን ሰፊ የሆነ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በታየበት ጨዋታ በጉዳት ምክንያት ሁለት ጨዋታ ያለፈው የፈርኦኖቹ አማካይ መሃመድ ኤል-ኒኒ በጥሩ መልኩ ከመሃመድ ሳላህ የተቀበለውን ኳስ ከጠበበ ቦታ ላይ አስቆጥሮ ግብፅን በመጀመሪያው አጋማሽ መሪ ማድረግ ችሏል፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ የማይበገሩት አንበሶቹ ሙሉ ለሙሉ ተጭነው ሲጫወቱ ፈርኦኖቹ በመከላከል ላይ ተጠምደው አምሽተዋል፡፡

በ58ኛው ደቂቃ በጉዳት ምክንያት ተቀይሮ የወጣውን አዶልፍ ቴኩን ተክቶ የገባው ተከላካዩ ኒኮላስ ንኮሉ በግንባሩ በመግጨት ካሜሮንን አቻ አድርጓል፡፡ መደበኛው ደቂቃ ሊጠናቀቅ ሶስት ደቂቃዎች ሲቀሩት ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ቪንሶን አቡበከር በግሩም ሁኔታ ኳስን በደረቱ ካበረደ በኃላ አሊ ጋብርን በማለፍ ካሜሮኖችን በደስታ ያስፈነደቀች ግብ በኤሳም ኤል ሃዳሪ መረብ ላይ አሳርፏል፡፡ በተለይ በሁለተኛው 45 የግብፅ የኃላ መስመር ፈጣኖቹን የካሜሮንን የመስመር ተጫዋቾች ለመቆጣጠር ሲከብዳቸው ተስተውሏል፡፡ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ የተመረጠው የካሜሮኑ ቤንጃሚን ሙካንጆ ነው፡፡

ግብፅ በአፍሪካ ዋንጫ ፍፃሜ ስትሸነፍ ይህ ለሁለተኛ ግዜ ነው፡፡ በ1962 በኢትዮጵያ 4-2 የተሸነፈችበት የፍፃሜ ጨዋታ የመጀመሪያው እና ብቸኛው ሆኖ ለረጅም ዘመናት ቆይቷል፡፡ ካሜሮን በ2002 ሴኔጋልን በመለያ ምት የአፍሪካ ዋንጫውን ካሸነፈች በኃላ በ2008 በግብፅ ተሸንፋ ዋንጫው ማጣቷ ይታወሳል፡፡ ወጣት እና ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች ስብጥር የሆነው ቡድኑ እንደሴኔጋል እና ጋና ያሉ ሃገራትን ከውድድር ማስወጣት ችሏል፡፡ ግብፅ ለመጨረሻ ግዜ የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ የተሸነፈችው በ2004 ቱኒዚያ ባስተናገደችው የአፍሪካ ዋንጫ በምድብ ጨዋታ በአልጄሪያ 2-1 ነበር፡፡ የግብፁ አሰልጣኝ ሆክቶር ኩፐር በአውሮፓ እግርኳስ የነበራቸው የፍፃሜ እድለቢስነት አሁንም ወደ አፍሪካ ተከትሏቸው መጥቷል፡፡

የካሜሮኑ አጥቂ ክሪስቲያን ባሶጎግ የውድድሩ ኮከብ ተጫዋች ተብሎ ተመርጧል፡፡ አሸናፊዋ ካሜሮን የ4 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በሽልማት መልክ ታገኛለች፡፡

 

የፎቶ ምንጮች፡ AFP, Reuters

1 Comment

  1. Yes, bravo Cameroon , they deserve it. EFF should take a lesson from this how focusing on youth player makes a deference.

Leave a Reply