ዝውውር | ደደቢት 3 የውጪ ተጫዋቾች ማስፈረሙን ይፋ አደረገ

ደደቢት በተከላካይ፣ አማካይ እና አጥቂ መስመር ላይ የቡድኑን ጥንካሬ ይጨምራሉ ያላቸውን ሶስት ተጫዋቾች ዝውውር ማጠናቀቁን አስታውቋል። 

ሰማያዊዎቹ ጦረኞች ሶስቱን ተጫዋቾች ያስፈረሙት የኢንተርናሽናል ተጫዋቾች ዝውውር ከመጠናቀቁ (ጃንወሪ 31) በፊት ሲሆን ሁለቱ የጋና እና አንዱ ደግሞ የኢኳቶሪያል ጊኒ ዜግነት ያላቸው ናቸው።

የ25 ዓመቱ የቀድሞ የጋና ከ17 እና 20 አመት በታች ብሔራዊ ቡድኖች ተጫዋች ኤሪክ ኦፖኩ በሁለቱ የጋና ታላቅ ክለቦች አክራ ኸርትስ ኦፍ ኦክ እና አሻንቴ ኮቶኮ መጫወት የቻለ ሲሆን በተከላካይ አማካይ ወይም በመሀል ተከላካይ ቦታዎች ላይ የመጫወት ችሎታ አለው። በ2007 በደቡብ ኮሪያ አዘጋጅነት በተደረገው የዓለም ከ17 አመት በታች ዋንጫ ላይ ተሳታፊ የነበረው የጋና ቡድን አባል የነበረው ኦፖኩ ከ2011 ጀምሮ በጋና ፕሪምየር ሊግ ለአሻንቲ ጎልድ እየተጫወተ አሳልፏል። ተጫዋቹ በ2014/15 የጋና ፕሪምየር ሊግ የውድድር ዘመን ክለቡ አሻንቲ ጎልድ የሊጉን ዋንጫ ሲያነሳ ትልቅ ሚና የነበረው ሲሆን የአመቱ የጋና ፕሪምየር ሊግ ምርጥ ተጫዋችነት ክብርንም ማግኘት ችሎ ነበር። በታህሳስ ወር መጀመሪያ ላይ ተጫዋቹ ለክዌቱ ክለብ አልናስር እንደፈረመ ቢነገርም ከክለቡ ጋር የነበረው ቆይታ በአጭሩ ተገትቷል። ኦፖኩ በደደቢት 29 ቁጥር ማልያ የሚለብስ ይሆናል።

ኤሪክ ኦፖኩ

የቀድሞው የአክራ ኸርትስ ኦፍ ኦክ ተከላካይ ክዌኩ አንዶህ በዝውውር መስኮቱ ደደቢትን የተቀላቀለ ሁለተኛው ተጫዋች ነው። አንዶህ በጋና ኸርትስ ኦፍ ላየንስ እና ቤሬኩም ቼልሲ የተጫወተ ሲሆን ያለፉትን 3 የውድድር ዓመታት በኸርትስ ኦፍ ኦክ አሳልፏል። በደደቢት 5 ቁጥር ማሊያ የተሰጠው አንዶህ በቀኝ መስመር ተከላካይ እና በመስመር አማካይ ቦታዎች ላይ ይጫወታል።

 ክዌኩ አንዶህ

የኢኳቶሪያል ጊኒ ዜጋ የሆነው አጥቂ ሮበን ኦባማ ኑሴ (በቅፅል ስሙ ሮበን ዳርዮ) በኢኳቶሪያል ጊኒ ሊግ ለአትሌቲኮ ማላቦ፣ ፓንተርስ፣ በመጨረሻም አትሌቲኮ ሴሙ ክለቦች ተጫውቶ ያሳለፈ ሲሆን ሃገሩ ባዘጋጀችው የ2015ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ላይም በብሔራዊ ቡድኑ ተካትቶ አንድ ጨዋታ ማድረግ ችሏል። የ2012ቱ የኢኳቶሪያል ጊኒ ፕሪምየር ሊግ ኮከብ ግብ አግቢ የነበረው ሮበን በደደቢት 12 ቁጥር ማሊያ ተሰጥቶታል።

በ27 ነጥብ መሪው ቅዱስ ጊዮርጊስን በመከተል በ2ኛ ደረጃ ላይ ግማሽ የውድድር ዘመኑን ማጠናቀቅ የቻለው ደደቢት ጋናዊው ክሌመንት አዞንቶ እና አይቮርያዊው ኩሊባሊ ካድርን ጨምሮ በቡድኑ የሚገኙ የውጭ ዜጎችን ቁጥር 5 አድርሷል፡፡ እነዚህን ተጫዋቾች ማስፈረሙም ለዋንጫ በሚያደርገው ፉክክር ይጠቅመዋል ተብሎ ይጠበቃል።

Leave a Reply