ዝውውር፡ መሃመድ ሳፋሪ ወደ ሀዋሳ ከተማ አይመጣም

የሁለት ግዜ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊው ሀዋሳ ከተማ ከሳምንት በፊት ሁለት ተከላካዮችን ከአሃሊ ሸንዲ ማስፈርም መቻሉ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ከፈረሙት መካከል ሱዳናዊው መሃመድ አሊ ኤል-ከድሪ (በቅፅል ስሙ – መሃመድ ሳፋሪ ወደ ክለቡ ሊያደርገው የነበረው ዝውውር እውን መሆን እንዳማይችል የክለቡ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡

ሳፋሪ ወርሃዊ 3750 የአሜሪካ ዶላር ደሞዝ እና በስድስት ወር የውሰት ውል ከሀዋሳ ጋር ተስማምቶ የነበረ ቢሆንም በሃገሩ ሊግን መቆየት የኃላ ኃላ መርጧል፡፡ በአሃሊ ሸንዲ ከአሰልጣኝ ውበቱ ጋር መስራት የቻለው የ32 ዓመቱ ተከላካይ ከሱዳን በሚወጡ መረጃዎች ከሆኑ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መምጣት ያልቻለው ከቤተሰቡ ጋር ተራርቆ መኖርን አለመፈለጉ ተጠቅሷል፡፡ ሶከር ኢትዮጵያ ያናገረችው ሱዳናዊው ጋዜጠኛ አብዱል ሙሳ የሳፋሪ ውሳኔ አግራሞትን እንደፈጠረበት ገልጿል፡፡ ሳይፍ ማሳዊን ያስፈረመው ሸንዲ ለሳፋሪ ቀጣይ የክለቡ ቆይታ ላይ ተፅእኖ አለው በማለት ሙሳ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

ሌላኛው የሀዋሳ ከተማ ፈራሚ ኮትዲቯሯዊው ተከላካይ መሃመድ ሲላ አርብ ምሽት አዲስ አበባ የደረሰ ሲሆን በቅርቡ ክለቡን ተቀላቅሎ ልምምድ የሚጀምር ይሆናል፡፡ ሀዋሳ ከተማ የማጥቃት እና የመከላከል አማራጮቹን ለማስፋት በዝውውር ገበያው ላይ እየተሳተፈ ይገኛል፡፡

Leave a Reply