የካፍ አፍሪካ ዋንጫ ምርጥ 11

የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌድሬሽን (ካፍ) ጋቦን ባዘጋጀችው የቶታል የአፍሪካ ዋንጫ የተሻለ የተንቀሳቀሱ ተጫዋቾችን በምርጥ 11 ውስጥ አካቷል፡፡ ዕሁድ ምሽት ሊበርቪል ላይ የአፍሪካ ዋንጫው ፍፃሜውን ሲያገኝ ካሜሮን ግብፅን በመርታት ለአምስተኛ ግዜ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ መሆኗ ይታወሳል፡፡

ቻምፒዮኗ ካሜሮን ሶስት ተጫዋቾችን በምርፅ 11 ውስጥ ማስመረጥ ስትችል ጋና፣ ግብፅ እና ቡርኪናፋሶ እያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት ተጫዋቾችን ማስመረጥ ችለዋል፡፡ ሴኔጋል እና ዲ.ሪ. ኮንጎ አንድ ተጫዋች በምርጥ 11 ውስጥ ማካተት የቻሉ ሃገራት ናቸው፡፡ አፍሪካ ዋንጫው ኮከብ ተጫዋች ተብሎ የተመረጠው የ22 ዓመቱ የካሜሮን አጥቂ ክሪስቲያን ባሶጎግ በፊት መሰምር ተሰላፊነት ተመርጧል፡፡ ባሶጎግ ለሃገሩ ብሄራዊ ቡድን የተጠራው በቅርቡ ነው፡፡ ፈጣኑ አጥቂ ለሃገሩ የዋንጫ የተሳካ ጉዞ ቁልፍ ሚና ነበረው፡፡ ያለው ጉልበት እና ፍጥነት የተጋጣሚ ተከላካዮችን የሚረብሸው ባሶጎግ በፍፃሜው ጨዋታ የግብፁን አንጋፋ የመስመር ተከላካይ አህመድ ፋቲን ሲያስቸግር አምሽቷል፡፡ ምንም እንኳን ያስቆጠረው የግብ መጠን አንድ ብቻ ቢሆንም ያሳየው ድንቅ እንቅስቃሴ የብዙዎችን ቀልብ ስቧል፡፡

የማይበገሩት አንበሶቹ የተቆጠረባቸው የግብ መጠን ሶስት ብቻ ነው፡፡ ለዚህም ቁልፍ ሚናን የተወጡት ግብ ጠባቂው ፋብሪስ ኦንዶ እና ሚካኤል ንጋጅዌ ናቸው፡፡ የቡርኪናፋሶዎቹ በርትራንድ ትራኦሬ እና ቻርለስ ካቦሬ በስብስቡ ውስጥ መካተት የቻሉ ሌሎች ተጫዋቾች ናቸው፡፡ ትራኦሬ ፈረሰኞቹ እስከፍፃሜ ግማሽ ባደረጉት ያልተጠበቀ ግስጋሴ ቁልፍ ነበር፡፡ አንጋፋው አማካይ ካቦሬ ለፓውሎ ዱራቴው ቡድን ጥንካሬን ሲፈጥር አስፈላጊ የሆነውን የመሪነት ግዴታውን በብቃት መወጣት ችሏል፡፡

ጋና ምንም እንኳን የ35 ዓመት የመታትን አፍሪካ ዋንጫ ድርቅ ባታስቆምም ዳንኤል አማርቴ እና ክሪስቲያን አትሱ በግላቸው መልካም እንቅስቃሴ አሳይተዋል፡፡ አማርቴ ለአቭራም ግራንት ቡድን የተከላካይ ክፍል የተሻለ ግልጋሎትን ሲሰጥ ፈጣኑ አትሱ በመስመር ያደርግ የነበረው እንቅስቃሴ ጥሩ ነበር፡፡ ጋና በመከላከሉ ረገድ እንደጆናታን ሜንሳህ እና ጆን ቦይ ያሉት ተጫዋቾችን ብትይዝም አንዳቸውም የአማርቴ ያህል አልጠቀሟትም፡፡ ጆን ቦይ ይባስ በአፍሪካ ዋንጫው ብቃቱ ከመቼውም ግዜ በላይ ወርዶ ታይቷል፡፡

የግብፆቹ አህመድ ሄጋዚ እና መሃመድ ሳላህ ፈርኦኖቹን በሚገባ ያገለገሉ ተጫዋቾች ናቸው፡፡ ሄጋዚ ወደ አል አሃሊ ከተመለሰ ወዲህ በድንቅ አቋሙ ፀንቷል፡፡ ቡድኑ በእዱ ዙሪያ የተገነባ እንደሆነ የሚነገርለት ሳላህ ግብ ከማስቆጠር ባለፈ የግብፅ የመልሶ ማጥቃት ዋነኛ መሳሪያ ነበር፡፡ ሳላህ ግብ የሆኑ ሁለት ኳሶችን አመቻችቶ ማቀበል ችሏል፡፡

የዲ.ሪ. ኮንጎው ጁኒየር ካባናንጋ ካሎንጂ የአፍሪካ ዋንጫው ኮከብ ግብ አግቢ ሆኗ ተመርጧል፡፡ ሶስት ግቦችን በአራት ጨዋታዎች ያስቆጠረው ካባናንጋ በምርጥ 11 ውስጥ ሊካተት ችሏል፡፡ የነብሮቹ የአፍሪካ ዋንጫ ጉዞ በጋና ሩብ ፍፃሜ ላይ ቢሰናከልም የካባናንጋን ያህል ግብ ያስቆጠር ተጫዋች በአፍሪካ ዋንጫው የለም፡፡ ካባናንጋ ግብ ማስቆጠሩ በተረፈ ከቡድን አጋሮቹ ጋር ያሳዩት የነበረው የደስታ አገላለፅ ጭፈራ በብዙዎች ተወዷል፡፡ (የኮንጎ ተጫዋቾች ፊምቡ የተባለውን ጭፈራ በተደጋጋሚ በምድብ ጨዋታዎች ላይ አስመልክተውናል፡፡)

ብዙዎች ለዋንጫው ገምተዋት ሳይጠበቅ በካሜሮን ተሸንፋ ከውድድር የወጣችው ሴኔጋል ተከላካዩን ሞዶ ካራ ምቦጂ በምርጥ 11 ውስጥ ማካታት ችላለች፡፡ ካራ የተከላካይ ክፍሉን በሚገባ ከመምራቱ ባሻገር ቱኒዚያ ላይ ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡

 

ኮከብ ተጫዋች፡ ክሪስቲያን ባሶጎግ (ካሜሮን)

ኮከብ ግብ አግቢ፡ ጁኒየር ካባናንጋ (ዲ.ሪ. ኮንጎ) በ3 ግቦች

የፀባይ ዋንጫ አሸናፊ፡ ግብፅ

የካፍ የአፍሪካ ዋንጫ ምርጥ 11

 

ፋብሪስ ኦንዶ (ካሜሮን)

ሞዶ ካራ ምቦጂ (ሴኔጋል) አህመድ ሄጋዚ (ግብፅ) ሚካኤል ንጋጅዌ (ካሜሮን)

 

በርትራንድ ትራኦሬ (ቡርኪናፋሶ) ዳንኤል አማርቴ (ጋና) ቻርለስ ካቦሬ (ቡርኪናፋሶ) መሃመድ ሳላህ(ግብፅ) ክሪስቲያን አትሱ (ጋና)

 

ክሪስቲያን ባሶጎግ (ካሜሮን) ጁኒየር ካባናንጋ (ዲ.ሪ. ኮንጎ)

Leave a Reply