ሐምሌ 1 የተከፈተው የመጀመሪያ ዙር የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት በነገው ዕለት ፍፃሜውን ያገኛል።
የኢትዮጵያ እግርኳስ የበላይ አካል የሆነው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የ2014 የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ዙር የተጫዋቾች የዝውውር ጊዜ መቼ እንደሆነ ይፋ አድርጎ የመጀመሪያውም ዙር መስኮት ከ83 ቀናት በፊት ተከፍቶ ነበር። ሐምሌ 1 የጀመረው የክረምቱ የዝውውር መስኮትም እጅግ ከፍተኛ እንቅስቃሴ የታየበት ሲሆን ፍፃሜውንም በነገው ዕለት አመሻሽ ያደርጋል።
ድረ-ገፃችን እስከ አሁን ባላት መረጃ መሠረት 175 ተጫዋቾች ወደ 16ቱ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ክለቦች አዲስ ዝውውር ፈፅመው አምርተዋል። እስከ አሁን ባጠናከርነው መረጃ በዚህ የዝውውር መስኮት ጅማ አባጅፋር በርካታ ተጫዋቾችን (19) ወደ ስብስቡ በአዲስ መልክ የቀላቀለ ክለብ ነው። በተቃራኒው አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ተጫዋቾችን ያስፈረመው ክለብ ደግሞ ፋሲል ከነማ (3) ነው።
የኢትዮጵያ እግርኳስ ድምፅ የሆነችው ሶከር ኢትዮጵያ የዝውውር እንቅስቃሴውን በንቃት በመመልከት በየአፍታው ዜናዎችን ስታቅርብ እንደነበረ የሚታወቅ ሲሆን ነገ እስከሚጠናቀቅበት ደቂቃ ድረስ ያሉ አዳዲስ መረጃዎችን እንዲሁም ከዝውውሩ መጠናቀቅ በኋላ አጠቃላይ የክለቦች እንቅስቃሴ ምን እንደሚመስል በተለያዩ መሰናዶዎች ይዛ የምትቀርብ ይሆናል።