ኢትዮጵያ ቡና 4-1 ደደቢት፡ ቡና ወደ መሪው የሚያደርገውን ግስጋሴ ቀጥሎበታል

ታክቲካዊ ትንታኔ፡ በአዲስ ወርቁ

ሁለቱ ቡድኖች ከጥቂት ሳምንታት በፊት ካደረጉት ጨዋታ በተሻለ መልኩ ይሄኛው ለተመልካች እጅግ አስደሳች ፣ ፈጣን እንቅስቃሴ እና ከፍተኛ ፊክክር ታይቶበታል፡፡ ቡና ደደቢትን የረታበት ውጤት ግን የፍልሚያውን ሂደት ሙሉ ለሙሉ ይገልፃል ማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ ተቀራራቢ ትንቅንቅ በታየበት ጨዋታ ቡና ያገኛቸውን የጎል ማግባት እድሎችን በጥሩ ሁኔታ ወደ ጎልነት መቀየሩ እና የዳዊት እስጢፋኖስ ሁለት ግሩም ጎሎች ውጤቱን አስፍተውታል፡፡

አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው ተጎድተው የነበሩትን ዳዊት ፣ጀማል ጣሰው እና ኤፍሬም አሻሞን በተጠባቂው 4-3-3 የአጨዋወት ቅርፅ በቋሚ አሰላለፉ ውስጥ ሲያካትቷቸው በአንፃሩ ተጋጣሚያቸው ደደቢት በ4-4-2 ሲስተም መስፍን ኪዳኔን ከዳዊት ፍቃዱ ጋር በፊት መስመር ሲያጣምር፣ ታደለ መንገሻ ከግራ መስመር እየተነሳ ተጫውቷል፡፡



የመጀመሪያው 45

አሰልጣኝ ንጉሴ ከ4-2-3-1 ይልቅ 4-4-2ን መጠቀማቸው ያልተጠበቀ ነበር፡፡ የደደቢት የጨዋታ ስትራቴጂ ባለፈው አመት ቡናን 4-1 ካሸነፈው ቡድን ጋር ተመሳሳይነት አለው፡፡ (የAddis Football Tactics የመጀመሪያ ታክቲካዊ ትንታኔን ተመልከቱ)፡፡ በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ ሹአይብ ጅብሪል እና ሳምሶን ጥላሁን(አምና አዲስ ህንፃ እና ታደለ) በከፍተኛ ፍጥነት የቡና አማካዮችን ፕሬስ ከማድረጋቸው ባሻገር የክንፍ አማካዮቹ ታደለ እና ሽመክት ጉግሳም(ባለፈው አመት ምንያህል ተሾመ እና በኃይሉ አሰፋ) ወደ መሀል በመግባት ለሁለቱ የቡድን አጋሮቻቸው እገዛ አድርገዋል፡፡ የሁለቱ የመሀል ሜዳ አማካዮች አግሬሲቭ የሆነ የቦታ አያያዝ(በደንብ ወደ ፊት መጠጋት) ኳሱን በቡና ሜዳ ክልል መልሰው ለመንጠቅም ረድቷቸዋል፡፡ በጨዋታው የመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ላይ የቡና አማካዮችም እንደለመዱት ተረጋግተው መቀባበል ተስኗቸዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የደደቢት አማካዮች ኳሱን በፍጥነት ቶሎ ቶሎ ፊት ለሚገኙት ተጫዋቾች በማድረስም በኩል የተሻሉ ነበሩ፡፡

ቡና በመሀል ሜዳ ሶስት አማካዮች ቢኖሩትም ጨዋታውን በተረጋጋ ሁኔታ መቆጣጠር አልቻሉም፡፡ የተከላካይ ክፍሉም እጅግ ተጋላጭ ነበር፡፡ በአምስት ደቂቃ ውስጥ ብቻ ሁለት አስደንጋጭ ሙከራዎች ተደርገውበታል፡፡ መስፍን ለጥቂት ከጨዋታ ውጪ ተብሎ የተሻረበት እና ሽመክት ወደ ግብ አክርሮ መትቷት ወደ ጎን የወጣችው አጋጣሚን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የቡና የተከላካይ ክፍል እምብዛም መረጋጋትን ያልተስተዋለበት ምናልባትም ሁለቱ የመሀል ተከላካዮች ከሁለት የፊት አጥቂዎች ጋር በመፋጠጣቻውም ሊሆን ይችላል፡፡ በፕሪምየር ሊጉ ውድድር በርካታ ተጋጣሚዎች አንድ የፊት አጥቂ ስለሚጠቀሙ አንዱ የቡና የመሀል ተከላካይ አጥቂውን ሲይዝ ሌላኛው ደግሞ ትንሽ ወደኃላ ቀረት በማለት የቡድን ጓደኛው ቢታለፍ እንኳን ሽፋን ይሰጣል፡፡ በዚህ ጨዋታ ግን 2ለ2 በመጋፈጣቸው እንደተለመደው መረዳዳት አልቻሉም፡፡(ምስሉን ተመልከቱ) ደቂቃዎች እየገፊ ሲሄዱ ግን በተሻለ መንገድ ለመከላከል ሞክረዋል፡፡

ታደለ ወደ መሀል አጥብቦ ስለሚጫወት ደደቢት በአማካይ ክፍል በቀላሉ የቁጥር ብልጫ እንዳይወሰድበት እገዛ አድርጓል፡፡ የክንፍ አማካዩ ከመስመር በአግድሞሽ ወደ መሀል ሰብሮ የሚገባበት እንቅስቃሴም ለቡና አማካዮች ፈታኝ ነበር፡፡ በፓሰሮች የተሞላው የቡና የአማካይ ክፍል ጠንካራ አማካይ ከገጠመው ሊፈተን እንደሚችል ከዚህ በፊት ጠቁሜ ነበር፡፡ ጋቾት ፓኖም የሚያስፈልገውም በእነኚህ ደቂቃዎች ነበር(ስለ ጋቾት በኃላ እመለሳለሁ)፡፡ መረጋጋት ያልቻለው የቡና የኃላ መስመር ጎል ለማስተናገድ የተገደደው ገና በዘጠነኛው ደቂቃ ሲሆን ዳዊት ከተከላካዮች ጀርባ(የአጥቂው ብቃት እነኚህ ሩጫዎች መሆናቸውን ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ገልጫለሁ) የተጣለለትን ምርጥ ኳስ በተረጋጋ ሁኔታ ጀማልን በማለፍ ከመረብ ጋር አገናኝቷታል፡፡

የደደቢት የአማካይ ክፍል ወደፊት በመጠጋቱ ምክንያት የተከላካይ ክፍሉም በመስመሮች መካከል ያለውን ክፍተት ለማጥበብ ወደ ፊት ተጠግቶ ተጫውቷል፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሳያ መሆን የሚችለው የቡና አጥቂዎች በተደጋጋሚ ከጨዋታ ውጪ ለመባል መገደዳቸው ነበር፡፡ ቡና ጨዋታውን እምባዛም መቆጣጠር ሳይችል 25ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት ከቅጣት ምት ወደ ግብ ሞክሯት የተመለሰችውን ኳስ ቢኒያም አሰፋ ወደ ጎልነት ቀይሯታል፡፡ የዚህች ጎል መቆጠር በቡና ደጋፊዎች ዘንድም ሆነ በተጫዋቾቹ ላይ ከፍተኛ መነቃቃትን ፈጥሯል፡፡

ከባለፈው ጨዋታ(ቡና ደደቢትን 2ለ1 ከረታበት ፍልሚያ) በተቃራኒ ሁኔታ ከጉዳት የተመለሰው ኤፍሬም በዚህ ፍልሚያ ጥሩ ሲንቀሳቀስ በቀኝ መስመር የተሰለፈው አስቻለው ግርማ ደግሞ እምብዛም ተፅዕኖው የጎላ አልነበረም፡፡ ኤፍሬም ጨዋታውን ወደ ጎን በመለጠጥ እና ራሱን ከስዩም ተስፋዬ ነፃ በማድረግ ጥሩ ጥሩ ኳሶችን ለመቀበል ሞክሯል፡፡ ወደ ጎል ሞክሮ በደደቢት ግብ ጠባቂ የተመለሰበት አንድ ቆንጆ አጋጣሚም ይጠቀሳል፡፡ የክንፍ አጥቂው ከዚህች ሙከራ ባሻገር 41ኛው ደቂቃ ላይ ቡና መሪነቱን ያስጨበጠውን ሁለተኛ ጎል ማስቆጠር ችሏል፡፡ ለዚህች ጎል መቆጠር የሮቤል ግርማ አስተዋፅኦ እጅግ ከፍተኛ ነበር፡፡ ፊልባኩ ኤፍሬም ጥሩ አጋጣሚ ማግኘቱን በመረዳት በአጥጋቢ የጊዜ አጠባበቅ ወደ ፊት ሄዶ ኦቨርላፕ በማድረግ ስዮምን 2ለ1 ከማጥቃቱም ባሻገር ለክንፍ አጥቂው ወደ ውጪ(Cut-Back) ጥሩ ኳስ አመቻችቶ አቀብሏል፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በትልልቅ የአውሮፓ ሊጎች በእንዲህ አይነት ሁኔታ (Cut-Back) የሚቆጠሩ ጎሎች ቁጥራቸው በእጅጉ ጨምሯል(በእኛው ሊግስ?)፡፡ ሽመክት ጉግሳ በፍጥነት ወደ ኃላ ተመልሶ ስዩምን ከመርዳት ይልቅ እጁን ወደ ላይ በማንሳት ከጨዋታ ውጪ በማለት ጊዜውን አባክኗል፡፡

ሁለተኛው 45

ሁለተኛው የጨዋታ አጋማሽ አምስት ደቂቃ ሳይሞላው ቡና ሶስተኛውን ጎል ማግባቱ ለደጋፊውም ሆነ ለተጫዋቾቹ ተጨማሪ እፎይታን ሰጥቷል፡፡ ዳዊት በአጭር ርቀት የመጣበትን የደደቢት በረኛ አንጠልጥሎ(ቺፕ) ያስቆጠረበት መንገድ እጅግ ማራኪ ነበር፡፡ አማካዩ በዚያን ጊዜ በተጋጣሚ ሳጥን ውስጥ መገኘቱ በራሱ አድናቆት ይገባዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የቢኒያም እንቅስቃሴም ወሳኝ ነበር፡፡ አጥቂው ለቡድኑ የሚያበረክተው አስተዋፅኦ እምብዛም ሲደነቅ አይስዋልም፡፡ ቢኒያም ከኳስ ውጪ የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ሁሌም ይማርኩኛል፡፡ በዚህም የተጋጣሚ የመሀል ተከላካዮችን ከቦታቸው ጎትቶ ማስወጣትም ይችልበታል፡፡ ጀርባውን ለጎል ሰጥቶ (Hold up play) የቡድን አጋሮቹ በጨዋታው ላይ እንዲሳተፉ የሚያደርገው ጥረትም ሊደነቅ ይገባል፡፡ በጥልቀት ወደ ኃላ በመመለስ በጨዋታው ላይ ሁሌም ለመሳተፍ ይጥራል፡፡

ዳዊት በደደቢት ተከላካዮች መካከል ገብቶ ይህቺን ጎል እንዲያስቆጥር ቀዳዳዎች እንዲፈጠሩለት ያደረገው እንቅስቃሴም ጥሩ ነበር፡፡ በመስመር የሚጫወቱት አስቻለው እና ኤፍሬምም ሆነ አማካዮቹ የቢንያምን እሯሯጥ በመረዳት የተፈጠረላቸው ክፍተቶችን በይበልጥ ለመጠቀም ቢሞክሩ ተመሳሳይ ጎሎችን ማግኘት ይችላሉ ብዬ እገምታለሁ፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ይሆን ዘንድ በጨዋታው መገባጀጃ አካባቢ የተፈጠረውን አንድ እንቅስቃሴ ላነሳ፡፡ ቡና አንድ ፈጣን የመልሶ ማጥቃት ይጀምራል፡፡ ይህን ያስተዋለው ቢኒያም በፍጥነት ወደ ቀኝ በመሮጥ አንዱን የደደቢት የመሀል ተከላካይ ከቦታው ያስወጣዋል፡፡ ቀዳዳውን የተመለከተው ፋሲካ በፍጥነት ወደ ክፍተቱ ይገሰግሳል፡፡ ኳስ እግሩ ስር የነበረችው ዳዊትም በጥሩ ሁኔታ ለፋሲካ አሾልኮ ያሳልፍለታል፡፡ አማካዮ ኳሷ ወደ ጎልነት ባይቀይራትም የፍፁም ቅጣት ምት ጠርዝ ላይ ተጠልፎ ይወድቃል፡፡ ይህቺን የቆመ ኳስ ነው ታዲያ ዳዊት በግሩም ሁኔታ አራተኛ ጉል ያደረጋት፡፡ ቢኒያም ያደረጋት ሩጫ ቀላል ልትመስል ትችላለች ነገር ግን ዋጋዋ ከፍተኛ ነበር፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ አጥቂው ወደፊት በአጨራረሱ ረገድ እና ወጥ አቋም በማሳየት በኩል ግን በእጅጉ መሻሻል ይገባዋል፡፡

ደደቢት በመጀመሪያው አጋማሽ እና በዚህኛውም በተደጋጋሚ ወደ ቡና የግብ ክልል ለመቅረብ ቢሞክርም ፍሬአማ መሆን አልቻለም፡፡ አልፎ አልፎ ታደለ ማራኪ እንቅስቃሴዎችን ቢያሳይም የጨዋታውን ውጤት መቀየር ሳይችል ቀርቷል፡፡ አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታም የተጫዋች ቅያሬዎችን ቢያደርጉም ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸው ጎልን ማግኘት አልቻሉም፡፡

በአንፃሩ አሰልጣኝ ጳውሎስ 60ኛው ደቂቃ ላይ ብልጠት የታከለበት የተጫዋች ቅያሬ አድርገዋል፡፡ ድካም የተስተዋለበት መስኡድ መሀመድን በጋቶች ቀይረውታል፡፡ ከዚህ በፊት በነበሩ ጨዋታዎች ላይ አሰልጣኙ ቢያንስ ውጤቶችን ለማስጠበቅ ከጋምቤላ የተገኘውን ተጫዋች በተገቢው ሰአት አለመጠቀማቸው ግርምትን እንደፈጠረብኝ ገልጬ ነበር፡፡ ጋቶች በሜዳ ላይ በቆየባቸው የመጨረሻዎቹ 30 ደቂቃዎች የማያስከፋ እንቅስቃሴ አሳይቷል፡፡ ከለውጡ በኃላ አማካዩ ከተከላካዮች ፊት የሆልዲንግ ሚናን ከፋሲካ ተረክቦ ከኃላው ለሚገኙት ተጫዋቾች በቂ ሽፋን ሰጥቷል፡፡ በዚህም ምክንያት ፊሲካ ወደፊት ጠጋ (በመስኡድ ሚና) ብሎ ተጫውቷል፡፡ ጋቾት ቡና የሚከፈትበትን ፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎች ለመከላከልም ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው፡፡ 85ኛው ደቂቃ ላይ በግራ መስመር አካባቢ በፍጥነት እየገሰገሰ የመጣው ታደለን እንዴት እንደነጠቀው ማስተዋል ይቻላል፡፡ የተከላካይ አማካዩ በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ የመካተት እድልን ባያገኝ እንኳን እንዲህ ባሉ ጠንካራ ፍልሚያዎች ላይ ለጥቂት ደቂቃዎችም ይሁን ከስካሁኑ በተሻለ መልኩ በሁለተኛው ዙር ከፍተኛ ግልጋሎትን ይሰጣል ብዬ እጠብቃለሁ፡፡

ማጠቃለያ

አሰልጣኝ ጳውሎስ የጨዋታውን ውጤት ብቻ ሳይሆን በመጀመሪያው አጋማሽ በአብዛኛው ክፍለ ጊዜ የአማካይ ክፍላቸው በፍጥነት፣ በጉልበት እና በአግሬሲቭ አጨዋወት እንዴት እንደተፈተነ ማጤን አለባቸው፡፡ አሰልጣኝ ንጉሴ ይዘውት የቀረቡት ታክቲክ ውጤት ባያስገኝላቸውም መጥፎ አልነበረም፡፡ ቡድናቸው ጨዋታውን በጀመረበት መንገድ አለመቀጠሉ እና ተጋጣሚያቸው ያገኛቸውን እድሎች በአግባቡ መጠቀሙ ለሽንፈት ቢደርጋቸውም ከመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የቡድናቸው ጠንካራ ጎን ብዙ መልካም ነገር እንደሚቀስሙ አልጠራጠርም፡፡

{jcomments on}

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *