ዝውውር : አቢኮይ ሻኪሩ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፈርሟል

በትውልድ ናይጄሪያዊ በዜግነት ቤኒናዊ የሆነው የፊት መስመር ተሰላፊው አቢኮይ ሻኪሩ አላዴ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የስድስት ወር ውል መፈረሙ ታውቋል፡፡

አጥቂው በአዳማ ከተማ በ2008 መጨረሻ ከተለቀቀ በኃላ ክለብ ሳይኖረው ያለፉትን ረጅም ወራት ቆይቷል፡፡ ዝውውሩ ከፈረንጆቹ ጥር 31 በፊት በመጠናቀቁ ሻኪሩ በሁለተኛው ዙር የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለንግድ ባንክ ተሰልፎ መጫወት ይችላል፡፡

በ2007 ከኦማን መልስ ለኢትዮጵያ ቡና መፈረም የቻለው ሻኪሩ እንደተጠበቀው መልካም እንቅስቃሴ ሳያሳይ አደገኞቹን ከአንድ ዓመት በኃላ ሊለቅ ችሏል፡፡ 2008 የውድድር ዘመነን በአዳማ ከተማ ቢያሳልፍም ይህ ነው የሚባል እንቅስቃሴን ሳያደርግ ከክለቡ ጋር ተለያይቷል፡፡ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በክረምቱ የዝውውር መስኮት ናይጄሪያዊውን ፒተር ንዋድኬን ያሰፈረመ ሲሆን የፈት መስመሩን በማጠናከር ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት አለማውን አድርጓል፡፡

በጥር የዝውውር መስኮት አብዛኞቹ የፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ የሆኑት ክለቦች ያስፈረሟቸው ተጫዋቸች የውጪ ሃገራት ተጫዋቾች ናቸው፡፡ በተያያዘ ዜና ንግድ ባንክ በ2008 መጨረሻ ለቆ ወደ ክዌት ሊግ ያመራው ሌለኛው ናይጄሪያው አጥቂ ፍሊፕ ዳውዝ አል ናስርን ለቆ ለሌላኛው የሃገሪቱ ክለብ አል ሻባብ የ6 ወር ውል ፈርሟል፡፡

ፊሊፕ ከ6 ወር ቆይታ በኃላ የተሻለ ውል ካገኘ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመመለስ ፍላጎት እንዳለው ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጿል፡፡

Leave a Reply