የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | የሶከር ኢትዮጵያ የጥር ወር ምርጦች 

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመርያ ዙር ሙሉ ለሙሉ ሊጠናቀቅ ነገ የሚደረጉ 2 ተስተካካይ ጨዋታዎች ብቻ ይቀራሉ፡፡ በጥር ወር እያንዳንዱ ቡድን 6 ጨዋታዎች ያደረገ ሲሆን ሶከር ኢትዮጵያ በየመጫወቻ ቦታቸው ላይ የተሻለ እንቅስቃሴ ያደረጉ ተጫዋቾች እና ውጤታማ የሆነ አሰልጣኝ መርጣለች፡፡

ማስታወሻ

*ይህ ምርጫ ተጫዋቾቹ እና አሰልጣኙ የተመረጡት በጥር ወር በተደረጉ ጨዋታዎች ላይ ብቻ መሰረት ያደረገ ነው፡፡

ግብ ጠባቂ

ሀሪሰን ሄሱ : ኢትዮጵያ ቡና

በጥር ወር በተደረጉት 6 ጨዋታዎች ላይ በሙሉ የተሰለፈው ሀሪሰን ወጥ አቋም በማሳየት ለቡና መሻሻል ቁልፉን ሚና ተወጥቷል፡፡ ከ6 ጨዋታዎች በ4ቱ ላይ መረቡን ሳያስደፍር መውጣቱም በድንቅ አቋም ላይ መሆኑን ይነግረናል፡፡

ተከላካዮች

እንየው ካሳሁን ፡ አዲስ  አበባ ከተማ

አዲስ አበባ ከተማ በአንደኛው ዙር የመጨረሻዎቹ ሳምንታት የተሻለ እንስቃሴ ማድረግ ችሏል፡፡ ለዚህ ደግሞ ቁልፍ ግልጋሎት ያበረከተው እንየው ነው፡፡ የመስመር ተከላካዩ 1 ጎል ከማስቆጠሩ በተጨማሪ በቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ ያለው ተሳትፎ ድንቅ ነው፡፡

ኤፍሬም ወንድወሰን ፡ ኢትዮጵያ ቡና

እንደ ሀሪሰን ሁሉ ኤፍሬም የቡና የተከላካይ ክፍል የተረጋጋ እንዲሆን እና በ4 ጨዋታዎች ግብ እንዳይቆጠርበት ማድረግ ችሏል፡፡ ቡድኑ በተከላካዮች ጉዳት ሲቸገር ወጥ አቋም በማሳየት የታደገው ኤፍሬም ነው፡፡ ከተለያዩ ተጫዋቾች ጋር ቢጣመርም ወጥ አቋም ከማሳየት ያገደው የለም፡፡

ምንተስኖት አዳነ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

የውድድር አመቱ ከተጀመረ ጀምሮ እንደ ምንተስኖት በወጥ አቋም የዘለቀ ተጫዋች ማግኘት ያስቸግራል፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች በወሩ የሚዋዥቅ የተናጠል ብቃት ቢያሳዩም ምንተስኖት በተከላካይም ሆነ በአማካይ ሰፍራ ድንቅ ግልጋሎት ማበርከት ችሏል፡፡ 1 ጎል ማስቆጠርም ችሏል፡፡ ምንተስኖት በዚህ ዝርዝር ሲካተት ይህ ለ2ኛ ጊዜ ነው፡፡

ደስታ ዮሃንስ ፡ ሀዋሳ ከተማ

ሀዋሳ ከተማ መጥፎ አመት እያሳለፈ ቢገኝም ደስታ በግሉ ዘንድሮም ጥሩ አቋም እያሳየ ይገኛል፡፡ በጥር ወር 5 ጨዋታ ያደረገው የግራ መስመር ተከላካዩ ሁለት ለጎሉ የሆኑ ኳሶች አቀብሎ አንድ ጎል አስቆጥሯል፡፡

አማካዮች

ሙሉአለም መስፍን ፡ ሲዳማ ቡና

ሲዳማ ቡና በጥር ወር በተሻለ ሁኔታ በርካታ ነጥቦችን መሰብሰብ እንዲችል ከፍተኛውን አስዋፅኦ ከተወጡት መካከል ሙሉአለም ግንባሬ ቀደሙን ስፍራ ይይዛል፡፡ ለቡድኑ የተከላካይ ክፍል ሽፋን በመስጠት ጥቂት ግቦች ብቻ እንዲያስተናግድ ረድቷል፡፡

ዳዊት እስጢፋኖስ ፡ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

ዳዊት በጨዋታዎች ላይ ያለው ተነሳሽነት እና ትኩረት ማጣት ደካማ ጎኑ ቢሆንም ሜዳ ውስጥ ካለ ተፅእኖ ፈጣሪነቱ ሁሌም አብሮት ይኖራል፡፡ በጥር ወር ባደረጋቸው 5 ጨዋታዎች 4 ጎል የሆኑ ኳሶች ማቀበል መቻሉ ለዚህ በቂ ማስረጃ ነው፡፡ ዳዊት በዚህ ዝርዝር ሲካተት ይህ ለ2ኛ ጊዜ ነው፡፡

ወንድሜነህ ዘሪሁን ፡ አርባምንጭ ከተማ

ለሁለተኛ ተከታታይ ወራት በዚህ ዝርዝር ወስጥ ተገኝቷል፡፡ ከውድድር አመቱ መጀመርያ ጀምሮ ወጥ አቋም በማሳየት የቀጠለው የአጥቂ አማካዩ በጥር ወር ብቻ በ6 ጨዋታዎች ተሰልፎ 4 ጎል የሆኑ ኳሶች አመቻችቶ ማቀበል ችሏል፡፡

አጥቂዎች

ሽመክት ጉግሳ ፡ ደደቢት

ሽመክት የደደቢት በመስመር ላይ የተመሰረተ የማጥቃት እንቅስቃሴ ዋንኛ መሳርያ መሆኑን ቀጥሏል፡፡ ቡድኑ ግብ ለማስቆጠር ቢቸገርም ሽመክት በግሉ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ለተከላካዮች ፈታኝ ነው፡፡ በጥር ወር 2 ጎሎችን ያስቆጠረው ሽመክት በዚህ ዝርዝር ሲካተት ይህ ለ2ኛ ጊዜ ነው፡፡

ፍፁም ገብረማርያም ፡ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

ፍጹም በመጨረሻም ወደ መደበኛ ግብ አስቆጣሪነቱ ተመልሷል፡፡ በጥር ወር ከፍጹም የተሻለ ግብ ያስቆጠረ ተጫዋችም በሊጉ የለም፡፡ ኢትዮ ኤሌክትሪክ የውድድር ዘመኑን የመጀመርያ ድል እንዲያስመዘግብ ፣ ወደ ክልል ተጉዞ በሁለት ጨዋታ ነጥብ ተጋርቶ እንዲመለስ እና ከወራጅ ቀጠና እንዲወጣ የፍጹም 5 ግቦች እጅግ ወሳኝ ነበሩ፡፡

አስቻለው ግርማ ፡ ኢትዮጵያ ቡና

የአስቻለው ወደ ድንቅ አቋም መመለስ ኢትዮጵያ ቡና በከፍተኛ ሁኔታ እንዲሻሻል ረድቶታል፡፡ አስቻለው ቡድኑ 4 ጨዋታዎች አሸንፎ ድንቅ ወር እንዲያሳልፍ ያስቆጠራቸው 4 ጎሎች እና የፈጠራቸው የግብ እድሎች ወሳኝ ነበሩ፡፡

ተጠባባቂዎች

ግብ ጠባቂ

መከላከያ በጥር ወር ምንም ጨዋታ ባያሸንፍም ሁሉንም ጨዋታ ከመሸነፍ የታደገው አቤለ ማሞ ነው ብሎ በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡

ተከላካዮች

የወልድያው አዳሙ መሀመድ ቡድኑ በጠባብ ውጤት አሸንፎ ከሚወጣባቸው ምስጢሮች አንዱ ነው፡፡ የሲዳማ ቡናው ሰንዴይ ሙቱኩ የአንተነህ ተስፋዬን ጉዳት ተከትሎ በመሃል ተከላካይ ስፍራ ምርጥ ግልጋሎት አበርክቷል፡፡

አማካዮች

የኢትዮጵያ ቡናው ጋቶች ፓኖም ቡድኑ ላሳየው መሻሻል ከፍተኛውን ሚና ከተወጡ ተጫዋቾች አንዱ ነው፡፡ የሀዋሳ ከተማው ጋዲሳ መብራቴ ግብ በማስቆጠር እና አመቻችቶ በማቀበል የቡድኑ ዋነኛ የማጥቃት መሳርያ ነው፡፡

አጥቂዎች

የአአ ከተማው ኃይሌ እሸቱ ከጨዋታ ጨዋታ መሻሻል በማሳየት ውድ  ዋጋ ያላቸው ጎሎችን ለቡድኑ አበርክቷል፡፡ የአምናው የከፍተኛ ሊግ ኮከብ አብዱራህማን ሙባረክ በጥር ወር መንሸራተቱ  ባሳየው ፋሲል የተሻለ እንቅስቃሴ አሳይቷል፡፡ ሁለት ጎሎችንም በስሙ አስመዝግቧል፡፡

የጥር ወር ኮከብ ተጫዋች

አስቻለው ግርማ – ኢትዮጵያ ቡና

ኢትዮጵያ ቡና በጥር ወር ካገኛቸው 14 ነጥቦች ቢያንስ 9 ነጥቦች እንዲያሳካ የአስቻለው መኖር አስፈላጊ ነበር፡፡ መጥፎ የውድድር ዘመን ጅማሬ አድርጎ የነበረው አስቻለው በጥር ወር ከመስመር እየተነሳ 4 ጎሎች አስቆጥሮ ፍጥነት እና ቴክኒክ ተጠቅሞ በርካታ የግብ እድሎች በመፍጠር ኢትዮጵያ ቡና እንዲያንሰራራ ማድረግ ችሏል፡፡

የጥር ወር ኮከብ አሰልጣኝ – ገዛኸኝ ከተማ

በጥር ወር እንደ ኢትዮጵያ ቡና በርካታ ነጥብ የሰበሰበ የለም፡፡ በወሩ መጀመርያ ቡድኑን በጊዜያዊ አሰልጣኝነት የተረከቡት አሰልጣኝ ገዛኸኝ ከተማም ቡድኑን ከውጤት ቀውስና  አውጥተው ማግኘት ከሚገባቸው 18 ነጥቦች 14 ማሳካት ችለዋል፡፡ በጥር ወር ምንም ሽንፈትም አላስተናግደም፡፡

3 Comments

  1. This is great starting. I encourage you to proceed your good works.

  2. Media is vital for informing fans about Ethiopian football and you are doing wonderful endeavor to our football Renaissance.Thanks and Keep it up.

Leave a Reply