የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተስተካካይ ጨዋታዎች ነገ ይደረጋሉ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 2ኛ ሳምንት ሊደረጉ ፕሮግራም ወጥቶላቸው ያልተካሄዱት 2 ተስተካካይ ጨዋታዎች ነገ አዲስ አበባ እና ጎንደር ላይ ይደረጋሉ፡፡

ፋሲል ከተማ ከ ወላይታ ድቻ (09:00 ፋሲለደስ ስታድየም)

ፋሲለደስ ስታድየም ላይ ፋሲል ከተማ በተከታታይ ድል አስመዝግቦ በ3ኛ ደረጃ 1ኛውን ዙር ለማጠናቀቅ በማለም ወላይታ ድቻን ያስተናግዳል፡፡ ከ5 ተከታታይ ጨዋታዎች ምንም ድል ያላሳካው ወላይታ ድቻም 3 ነጥብ ለመሰብሰብ ጠንካራ ፉክክር እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡

በጨዋታው ዙርያ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየታቸውን የሰጡት የፋሲሉ አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ ከቡድናቸው ትኩስ ጉልበት ለማግኘተ በማሰብ ከእሁዱ ጨዋታ ሶስት እና ከዛ በላይ ለውጦች አድርገው እንደሚገቡ ተናግረዋል፡፡ የወላይታ ድቻው መሳይ ተፈሪም የተጫዋቾችን ሚና በማሸጋሸግ ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ገልጸዋል፡፡

በነገው የ09:00 ጨዋታ በፋሲል ከተማ በኩል ግብ ጠባቂው ዮሃንስ ሽኩር አሁንም ከጉዳት ያላገገመ ሲሆን ወላይታ ድቻ የአጥቂዎቹ አላዛር ፋሲካ (5 ቢጫ) እና ዳግም በቀለ (ጉዳት) ግልጋሎት የማያገኝ ይሆናል፡፡

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ሀዋሳ ከተማ (11:30 አአ ስታድየም)

ሁለት ከደረጃ ሰንጠረዡ ወገብ በታች የሚገኙ ቡድኖችን በሚያገናኘው ጨዋታ አሸናፊው ቡድን ከወራጅ ቀጠናው የሚያመልጥ በመሆኑ ትኩረት የሚሰጠው ጨዋታ ነው፡፡

አሰልጣኙ ጸጋዬ ኪዳነማርያም በፌዴሬሽኑ በመቀጣታቸው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ  በምክትል አሰልጣኙ ሲሳይ ከበደ መሪነት ወደ ሜዳ የሚገባ ይሆናል፡፡ ቡድኑ በጉዳት እየታመሰ ሲሆን ግብ ጠባቂው ኢማኑኤል ፌቮ ፣ አጥቂው ዳኛቸው በቀለ እና አምበሉ ታዲዮስ ወልዴ ከነገው ጨዋታ ውጪ ሆነዋል፡፡ ጂብሪል አህመድ እና ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን የመሰለፍ እድላቸውም 50/50 ሆኗል፡፡

በሀዋሳ ከተማ በኩል በጉዳት ጨዋታው የሚያልፈው ተጫዋች የሌለ ሲሆን በኤሌክትሪክ በተሸነፉበት ጨዋታ ቀይ ካርድ የተመለከተው አዲስአለም ተስፋዬ በቅጣት ጨዋታው ያመልጠዋል፡፡ በጉዳት 1 ጨዋታ ያለፈው አምበሉ ደስታ ዮሃንስ ደግሞ ለጨዋታው ዝግጁ ሆኗል፡፡

1 Comment

  1. ትኩረት ሰጥታቹህ የክልል ጨዋታዎችን መዘገባችሁ የሚደነቅ ነው ።

Leave a Reply