በራሪው ፍቅሩ ዳግም ወደ ህንድ?

ኢትዮጵያዊው አጥቂ ፍቅሩ ተፈራ ስሙ ዳግም በስፋት ለዝውውር ተነስቷል፡፡ በ15 በላይ ክለቦችን በእግርኳስ ህይወቱ የተጫወተው ቀድሞ የአዳማ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ አጥቂ በህንድ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ከሚወዳደረው መሃመዳን ስፖርቲንግ ክለብ ጋር ስሙ ለዝውውር ተያይዟል፡፡

ፍቅሩ ለሰባት ወራት ቆይታ ያደረገበትን የባንግላዴሹን ሼይክ ሩሴልን ከለቀቀ በኃላ ክለብ አልባ ሆኖ ቆይቷል፡፡ በታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን የህንድ ሂሮ ሊግ ግብ ያስቀጠረው ፍቅሩ እስከጥር 2017 መጀመሪያ ድረስ የአሰልጣኝነት ኮርሶችን ለመከታተል እንደሚፈልግ ከዚህ ቀደም ገልፆ ነበር፡፡ ተጫዋቹ እና የመሃመዳን ክለብ ባለስልጣናት በዝውውር ጉዳይ ላይ በቃል ደረጃ መስማማታቸውን ተቀማጭነቱን በህንድ ያደረገው የእግር ኳስ ድህረ-ገጽ feverpitch.in ከሳምንታት በፊት ዘግቧል፡፡

የfeverpitch.in ዘጋቢ የሆነው ባቡዋ ቢስዋስ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጠው አስተያየት ከሆነ በቃል ደረጃ ሁለቱም ወገኖች ቢስማሙም የተፈረመ ውል ግን እስካሁን የለም፡፡ “እኛ ከክለቡ ባገኘነው መረጃ መሰረት መሃመዳን ለፍቅሩ የውል ሰነዶችን ልኳል፡፡ ቢሆንም ነገሮችን እንደታቀዱት እየሄዱ አይደለም፡፡ እስካሁን ድረስ ፍቅሩ ክለቡን አልተቀላቀለም፡፡” ሲል ሃሳቡን ሰጥቷል፡፡

የህንድ የዝውውር መስኮት እንደቻይና ሁሏ እስከሚቀጥለው ሳምንት ድረስ ክፍት በመሆኑ የፍቅሩ ዝውውር እውን ሊሆን ይችላል፡፡ ፍቅሩ በህንድ ለአትሌቲኮ ኮልካታ እና ቼናይ ክለቦች መጫወት ችሏል፡፡ በአትሌቲኮ ኮልካታ ቆይታው በ12 ጨዋታዎች አምስት ግቦችን በማስቆጠር ክለቡ የመጀመሪያውን የሂሮ ህንድ ሱፐር ሊግ አሸናፊ እንዲሆን አስችሏል፡፡ ከአሰልጣኝ አንቶኒዮ ሃባስ ጋር ባለመስማማቱ ወደ ቼናይ ያመራው ፍቅሩ አንድ ግብ ብቻ ነው ከመረብ ማዋሃድ የቻለው፡፡

በሁለተኛ ግዜ የህንድ ቆይታውም የሊጉን ክብር ማግኘት ችሏል፡፡ ፍቅሩ ከዚህ ቀደም ሃገራት እና እግርኳሳቸውን መናቅ መቆም አለበት ሲል መናገሩ ይታወሳል፡፡ ፍቅሩ አያይዞ “ከጥቂት ዓመታት በፊት ወደ ህንድ ሄዶ እግርኳስ መጫወት በብዙዎች ዘንድ የማይታሰብ ነበር። አሁን ግን በርካታ ተጫዋቾች ወደዚያ ሄደው ለመጫወት በማሰብ ምክር ፈልገው ይደውሉልኛል። ሃገራትን እና እግርኳሳቸውን የመናቅ አስተሳሰብ መቆም ያለበት ነገር ነው። እኔ በተጫወትኩባቸው ሃገራት ሁሉ ሄዶ መጫወት የሚፈልግ ተጫዋች ካለ ጥሩ ኮንትራት ከቀረበላቸው እንዲሄዱ እመክራለሁ።” ሲል በመስከረም ወር አስተያየቱን መስጠቱ ይታወቃል፡፡ ፍቅሩ በህንድ ሂሮ ሊግ ግብ ካስቆጠረ በኃላ በመገለባበጥ ደስታውን የሚገልፅ በመሆኑ ‘በራሪው ፍቅሩ’ የሚል ተቀፅላ ስም ወጥቶለታል፡፡

መሃመዳን ስፖርቲንግ ክለብ የኮልካታ ክለብ ነው፡፡ ቡድኑ በአሁኑ ወቅት በሁለተኛ ዲቪዚዮን ላይ በመወዳደር ይገኛል፡፡

Leave a Reply