የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሁለተኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታዎች ዛሬ ጎንደር እና አዲስ አበባ ላይ ተደርገዋል፡፡ ፋሲል ከተማ ወደ መሪዎቹ የተጠጋበትን ድል ወላይታ ድቻ ላይ ሲያስመዘግብ ሐዋሳ ከተማ በበኩሉ ከወራጅ ቀጣናው የወጣበትን ወሳኝ ነጥብ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በማሸነፍ ማሳካት ችሏል፡፡
ከወራጅ ቀጣናው ለመውጣት አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ሐዋሳ ከተማን የገጠመው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 2-0 ተሸንፏል፡፡ በተከታታይ ሽንፈቶችን ያስተናገደው ባንክ በመጀመሪያው አጋማሽ ከሐዋሳ የሚሰነዘሩበትን ጥቃቶች በመመለስ ጥሩ ነበር፡፡ ንግድ ባንክ በፒተር ንዋድኬ እንዲሁም ሐዋሳ በዳንኤል ደርቤ አማካኝነት ለግብነት የቀረቡ ሙከራዎች አድርገዋል፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ የእንግዶቹ የመሃል ክፍል ወደፊት ተጠግቶ መጫወቱ ፍሬ አፍርቶ ታፈሰ ሰለሞን ከቀኝ መስመር ወደ አደጋ ክልሉ የላከውን ኳስ የንግድ ባንኩ የመሃል ተከላካይ ቢኒያም ሲራጅ በራሱ ግብ ላይ አስቆጥሯል፡፡ ከ12 ደቂቃዎች በኃላ ቶጎዋዊው አረፋት ጃኮ ሁለተኛውን ግብ አሁንም ከታፈሰ ሰለሞን የተቀበለውን ኳስ ተጠቅሞ አስመዝግቧል፡፡ ውጤቱን ተከትሎ ሐዋሳ ከተማ በ14 ነጥብ ከወራጅ ቀጠናው በአንድ ደረጃ ከፍ ብሎ 13ተኛ ሲሆን ጅማ አባ ቡና እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በእኩል 13 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው 14ኛ እና 15ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡
we <> never walk alone……keep it up Atsewochh
Viva fasil