የአሰልጣኞች አስተያየት፡ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 0-2 ሀዋሳ ከተማ

​ሀዋሳ ከተማ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት ቀሪ ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በመርታት ከወራጅ ቀጣው ወጥቷል፡፡ የሁለቱም ክለብ አሰልጣኞች ለጨዋታው በኃላ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡


የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምክትል አሰልጣኝ ሲሳይ ከበደ

ስለጨዋታው

“በመጀመሪያው 45 ጨዋታው የቀዘቀዘ ነበር፡፡ በሁለተኛው 45 ቡድናችን ያገኛቸውን የግብ እድሎች ባለመጠቀሙ ግብ ተቆጥሮብን ልንወጣ ችለናል፡፡” 

“አሁንም የኃላ መስመራችን ሊስተካከል አልቻለም፡፡ በግንኙነት እና ማርኪንግ ስህተቶች ናቸው ግቦች የተቆጠሩብን፡፡ ቀሪ ብዙ ጨዋታዎች አለን፡፡ አሁን ባለንበት ደረጃ አንቀጥልም፡፡ በሁለተኛው ዙር የተሻለ አቋም ይዘን በሊጉ ላይ የተሻለ ተፎካካሪ ሆነን እንጨርሳለን ብዬ አስባለው፡፡”

የንግድ ባንክ ቀጣይ ጉዞ

“ወደ ቡድናችን ያካተትነው ተጫዋች አለ፡፡ በተጨማሪ በጤና ምክንያት እየተጫወቱ የሌሉ ተጫዋቾች አሉ፡፡ ባሉን የእረፍት ሰዓቶች ከህመማቸው ካገገሙልን ወደ ጨዋታ ከተመለሱልን የተሻለ ውጤት እናመጣለን ብለን እናስባለን፡፡”
የሀዋሳ ከተማ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ
ስለጨዋታው

“ለሁለታችንም ከባድ እና ወሳኝ ጨዋታ ነበር፡፡ ያለንበት ደረጀም እታች ነው ስለዚህም ከዚህ ለመውጣት እና አንደኛውን ዙር በጥሩ ነገር ለመጨረስ ሁለታችንም ጥንቃቄ የተሞላበት ጨዋታ እንደተጫወትን ነው ያየሁት፡፡ በጣም ጥሩ ነገር ማሸነፋችን ነው ብዬ ማስበው፡፡ በአጠቃላይ ለእኛ ጥሩ ቀን ነበር፡፡” 

“መጀመሪያ ላይ ባልተለመደ መልኩ ከኃላ ከመሃል ተከላካዮች በቀጥታ ወደፊት የሚላኩ ኳሶች ነበሩ፡፡ ብዙም እንድንጫወት ያልጋበዙን እና መሃል ላይ የነበሩ ልጆችን በጣም ተይዘው ነበር እና በምንፈልገው መንገድ አልተንቀሳቀስንም፡፡ ሁለተኛው አጋማሽ ላይ እሱን በማረማችን እና ፊት ላለለው አረፋት በቅርበት በመጫወታችን ይመስለኛል የተሻለ መንቀሳቀስ የቻልነው፡፡”

ግብ ሲያስቆጥሩ የነበረው የተጫዋቾች እና አሰልጣኙ ደስታ አገላለፅ

“ሁላችንም ጠንክረን ሰርተን ከዚህ ነገር ለመውጣት ጥረት እያደረግን ነው፡፡ እንደሚታወቀው ውጤት ካጣህ መጀመሪያ የሚባረረው አሰልጣኝ ነው፡፡ ምንአልባት ለእኔ ያላቸው ቅርበት ይመስለኛል እንዳልባረረ ሰግተው ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህ የተለየ ነገር ግን የለውም፡፡ ደስታቸውን ለመግለፅ የመጡበት መንገድ ጭንቀት ውስጥ እንዳሉ ነው የሚያሳየው፡፡ ከራሳቸው አልፎ ለእኔም እየተጨነቁ እንዳሉ ነው የተሰማኝ፡፡ አንድ መሆን ከቻልን ከዚህም በላይ መሄድ እንችላለን ብዬ ነው ማስበው፡፡” 
ስለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነት

“እንግዲህ ላለፉት አምስት እና አራት ዓመታት ስሜ ከብሄራዊ ቡድኑ ጋር በተደጋጋሚ ይነሳል፡፡ አሁንም እሰማለው፤ እኔም እራሴ ማስረጃዬን አስገብቻለው፡፡ እግዚአብሄር ከፈቀደ ይሆናል፡፡ ካልሆነም ማንኛውም ሰው ቢይዘው ደስተኛ ነኝ፡፡”     

Leave a Reply