የ2017 ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ዛሬ ይጀመራል

የ2017 የካፍ ቶታል ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ዛሬ ሊበርቪል፣ ኦባያድ እና ሞኖሮቪያ ላይ በሚደረጉ ሶስት ጨዋታዎች ይጀምራል፡፡

የጋቦኑ አካንዳ የዲ.ሪ. ኮንጎው ሬኔሳንስ ዱ ኮንጎን ሲያስተናግድ የሱዳኑ ሂላል ኦባያድ የሲሸልሱን ሴንት ሚሼልን ይገጥማል፡፡ የላይቤሪያው ሞኖሮቪያ ክለብ ቤርዌሪስ አልጄሪያውን ሃያል ክለብ ጄኤስ ካቤሌን ያስተናግዳል፡፡ የኢትዮጵያው ተወካይ መከላከያ እሁድ አዲስ አበባ ላይ የካሜሮኑን ዮንግ ስፖርትስ አካዳሚን ያስተናግዳል።

የአፍሪካ ዋንጫ ከተጠናቀቀ ከቀናጥ በኃላ የጋቦኑ ተወካይ አካንዳ በሜዳው እና ደጋፊው ፊት ሬኔሳንስ ዱ ኮንጎን ያስተናግዳል፡፡ የጋቦን ዋንጫ አሸናፊው አካንዳ በኮንፌድሬሽን ዋንጫ የሚጠቀስ ታሪክ የለውም፡፡ ተጋጣሚው ሬኔሳንስ ምስረታውን ያደረገው በ2014 ነበር፡፡ የጋቦን ብሄራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ ከምድብ መሰናበቱን ተከትሎ ሃገሪቱን የሚወክሉ ክለቦች ላይ ያለው ተስፋ እየመነመ መጥቷል፡፡ ሃያሉ ክለብ ሞናና በ2016 ጥሩ ግስጋሴን ያሳየ ቢሆንም የአካንዳ ጉዞ ላይ ግን ብዙ ጥያቄዎች ይነሳሉ፡ የዲ.ሪ. ኮንጎው ሬኔሳንስ በውድድሩ ላይ ለመጀመሪያ ግዜ ነው የሚሳተፈው፡፡ ከጫና ነፃ ሆኖ ለሚጫወተው ክለቡ የተሻለ እንቅስቃሴን እንደሚያሳይ ተገምቷል፡፡

በሱዳን እግርኳስ የሁለቱ ሃያላን አል ሂላል እና ኤል-ሜሪክን የበላይነት ለመስበር በጥሩ መልኩ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው አል ሂላል አቦያድ የሲሸልሱን ሴንት ሚሼልን ይገጥማል፡፡ ሂላል ኦባያድ ወደ ሱዳን ሊግ ካደገ ወዲህ ዘመናዊ ስታዲየም የሰራ ሲሆን ከፍተኛ ፋይናንስ በማውጣት ክለቡን ስያጠናክር ከርሟል፡፡ ከቅድመ ማጣሪያው እምብዛም ፈቀቅ ያለ ውጤት የሌለው የቪክቶሪያው ክለብ ሴንት ሚሼል በሱዳን ከሂላል ኦባያድ ውጤት ማግኘት መቻሉ ያጠራጥራል፡፡ የማሸነፍ ቅድመ ግምቱን ሂላል ኦባያድ ወስዷል፡፡

ሞኖሮቪያ ክለብ ቤርዌሪስ በሜዳው ጄኤስ ካቤሌን ይገጥማል፡፡ የሞኖሮቪያው ክለብ ከተጋጣሚው ያነሰ የአፍሪካ ክለቦች ውድድር ልምድ አንፃር ዝቅተኛ ግምት ተሰጥቶታል፡፡ ምንም እንኳን ቤርዌሪስ በአፍሪካ እግርኳስ የካበተ ልምድ ናይኖረውም ተጋጣሚው ጄኤስ ካቤሌ በአልጄሪያ ሊግ 1 በመጥፎ ውጤት ቀውስ ውስጥ መገኘቱ የላይቤሪያውን ክለብ ተጠቃሚ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ጄኤስ ካቤሌ ወደ ሞኖሮቪያ ያቀናው ቱኒዚያዊውን የክለቡ ዋና አሰልጣኝ ሶፉያን ሂዶሲን በማሰናበት ነው፡፡ ቡድኑ በዘንድሮው የውድድር ዓመት ማሸነፍ የቻለው ሶስት ጨዋታዎችን ብቻ ነው፡፡ ካቤሌ በ2014 የካሜሮናዊውን የክለቡ አጥቂ አልበርት ኦቦሳ ከደጋፊዎች በተወረወረ ቁስ ህይወቱን ማጣቱን ተከትሎ ሰፊ መነጋገሪያ ሆኖ መሰንበቱ ይታወሳል፡፡

 

ዓርብ የካቲት 3

17፡30 – አል ሂላል ኦባያድ (ሱዳን) ከ ሴንት ሚሸል (ሲሸልስ) (አል ኦባያድ ስታዲየም)

16፡00 – አካንዳ ኤፍሲ (ጋቦን) ከ ሬኔሳንስ ዱ ኮንጎ (ዲ.ሪ. ኮንጎ) (ሰታደ ደ አንጎንጄ)

17፡00 – ሞኖሮቪያ ክለብ ቤርዌሪስ (ላይቤሪያ) ከ ዩነስ ስፖርቲቭ ደ ካቤሌ (አልጄሪያ) (አንቶኔት ቱብማን ስታዲየም)

Leave a Reply