​ከክለቦች ተቃውሞ የገጠመው የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊዎችን ቁጥር የመገደብ ሀሳብ

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ 1ኛ ዙር ግምገማ ትላንት በአዳማ የባ ሆቴል ተካሂዷል፡፡ በውይይቱ ላይ ሰፊውን ሰአት የወሰደው ደግሞ በዘንድሮው አመት ተግባራዊ ይሆናል የተባለው ከሴቶች ፕሪምየር ሊግ በታች አንድ ሊግ በማቋቋም በሊጉ እየተሳተፉ ካሉ 20 ቡድኖቸች 10 ቡድኖች እንዲወርዱና ከአዳዲሶቹ  ቡድኖች ጋር በማጣመር እንዲካሄድ የወጣው ደንብ ነው፡፡ 

ፌዴሬሽኑ ደንቡን ለማውጣት በከፍተኛ ሊጉ ያስመዘገበው ስኬት መነሳሻ እንደሆነው በመግለፅ የውድድር ጥራት ያመጣል በሚል እንደወጣ የውድድር እና ስነስርአት ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ አበበ ገላጋይ በትላንቱ ግምገማ ላይ ተናግረዋል፡፡ 

“ከዚህ ቀደም ከወንዶች ፕሪምየር ሊግ ቀጥሎ ይገኝ በነበረው ብሄራዊ ሊግ ከ80 በላይ ክለቦች ተወዳድረው የሚያልፉት ሁለት ቡድኖች በፕሪምየር ሊግ ጠንካራ ተፎካካሪ መሆኑ  ባለመቻላቸው አምና የከፍተኛ ሊግ በ32 ቡድኖች ተቋቁሞ ከተካሄደው ውድድር ያለፉት ክለቦች በዘንድሮው ፕሪምየር ሊግ ተፎካካሪ መሆናቸው በሴቶች ፕሪምየር ሊግ ላይም ቢተገበር በተመሳሳይ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል” ሲሉ አቶ አበበ ተናግረዋል፡፡ 

ከክለብ ተወካዮች በተነሳው ሀሳብ ደግሞ ደንቡ የሴቶች እግርኳስን የሚያዳክም እንደሆነ ተገልጿል፡፡ የክለብ አመራሮች ለሴቶች እግርኳስ በሚሰጡት ደካማ ትኩረት ምክንያት ወደ ታችኛው ሊግ መውረድ የሚኖር ከሆነ ቡድኖች እንደሚፈርሱ ስጋታቸውነ ገልጸዋል፡፡ በሁሉም አካባቢ እየተስፋፋ ያለውን የሴቶች እግርኳስ ተሳትፎ ይገድባል ፣ የፉክክር ሚዛኑን ከዚህም የባሰ ያዛባዋል ፣ ደንቡ አስፈላጊ ቢሆንም ጊዜው አሁን አይደለም የሚሉና ሌሎች አስተያየቶች ከግምገማው ተሳታፊዎች ተሰንዝረዋል፡፡  ከአስተያዮቶቹ መካከል አንኳር አንኳሩን እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡-

አቶ ኪሩቤል ከሲዳማ ቡና

መውረድ ይኑር የሚለውን ሀሳብ እንደ ሲዳማ ቡና እንቃወማለን፡፡ እግርኳስ ከማይታወቅባቸው ገጠራማ አካባቢዎች የሚወጡ ተጫዋቾችን እድል የሚዘጋም ነው፡፡ ምናልባት ደንቡ ከጸና ለሲዳማ ቡና በልዩ ሁኔታ የ1 አመት ጊዜ ሊሰጥ ይገባል፡፡ ምክንያቱም ሲዳማ ገና እንደአዲስ እየተገነባ ያለ ቡድን ነው፡፡

አቶ ማስረሻ ከ ጌዲኦ ዲላ

መውረድ እንደሚኖር የሰማነው አሁን ነው፡፡ ቀደም ብሎ ቢነገረን ጥሩ ነበር፡፡ ይህ ደንብ የውድድሩን ፉክክር የሚያዛባ ነው የሚሆነው፡፡ ምክንያቱም አቅም ያላቸው ክለቦች ላለመውረድ ተጫዋቾችን በመግዛት ትንንሾቹን ቡድኖች ያዳክማሉ፡፡

አሰልጣኝ ብዙአየሁ ከልደታ ክፍለከተማ

መውረድ የሚለው ደንብ ቢታሰብበት የተሻለ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ክለቦች የሚወርዱ ከሆነ አንዳንዶቹ የሴት ቡድናቸውን ለማፍረስ ዳር ዳር እያሉ ነው፡፡ የውድድሩ ጥራት እንዲመጣ በቅድሚያ ተሳታፊዎችን መጨመር ነው ያለብን፡፡

አሰልጣኝ ዮናስ ከቅድስት ማርያም

ይህ ደንብ ከመዘጋጀቱ በፊት ክለቦች ያሉበትን ሁኔታ መረዳት ይገባል፡፡ ውድድሩ ሊጀመር እጣ በሚወጣበት ወቅት ነው ይህ ነገር የተነገረው፡፡ ይህ ደንብ ተግባራዊ መደረግ ያለበት ውድድር ሊጀምር ሲል ሳይሆን በረጅም ጊዜ ሒደት ነው መሆን ያለበት፡፡ መውረድ የሚኖር ከሆነ አዳዲስ የሴት ቡድኖችን እድል የሚዘጋ ነው የሚሆነው፡፡ የተሳታፊ ቁጥር በመቀነስ ብቻ ደግሞ የሊግ ጥራት ይመጣል የሚል እምነትም የለንም፡፡

አሰልጣኝ አስራት አባተ ከ አአ ከተማ

ፌዴሬሽኑ ይህን ደንብ ተግባራዊ ለማድረግ ያሰበው በከፍተኛ ሊግ ባመጣው ስኬት ነው፡፡ ነገር ግን በወንዶች እና በሴቶች እግርኳስ ላየይ ያለው ሁኔታ ተመሳሳይ ባለመሆኑ የከፍተኛ ሊጉን አሰራር በቀጥታ ወደ ሴቶች ማውረድ ከባድ ነው፡፡

ደንብ ላይ እስከተቀመጠ ድረስ በደንቡ መመራት ይኖርብናል፡፡ ነገር ግን ፌዴሬሽኑ ከወዲሁ ቁርጥ ያለ ውሳኔ መወሰን ይኖርበታል፡፡ ውድድሩ ከገፋ በኋላ ቢወስን ጭቅጭቅ ሊፈጥር ይችላል፡፡ 

አሰልጣኝ ቶሎሳ ከንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለከተማ

ይህ ደንብ ክለቦችን የሚያዳክም ነው፡፡ በዚህ አመት ከወረድን ተጫዋቾቻችን በሌሎች ይወሰዳሉ በቀጣዩ ለመምጣትም ያስቸግራል፡፡ ሴቶች ላይ የሚደረገው ድጋፍ አነስተኛ በመሆኑም የመፍረስ እጣ ነው የሚደርስብን፡፡

አሰልጣኝ እየሩሳሌም ከኢትዮጵያ ቡና

በደንቡ ላይ ጥያቄ የለኝም፡፡ ነገር ግን የሚወርዱ ቡድኖች ህልውናቸው ቀጣይ መሆኑን እንዴት ማረጋገጥ ይቻላል የሚለው መታሰብ አለበት፡፡ እስከመቼ የሴቶች ክለቦች በልመና ህልውናቸውን እያቆዩ ይቀጥላሉ? በኢትዮጵያ የትምህርት ፖሊሲ እንኳን ጥራት ሳይሆን ሽፋን ነው ቅድሚያ የሚሰጠው፡፡ የሴቶች እግርኳስም አሁን የሚያስፈልገው ሽፋን ነው፡፡ በቅድሚያ በሁሉም ቦታ መዳረስ አለበት፡፡ ከዛ በኋላ ነው ተሳታፊዎችን ስለመገደብ እና ስለ ጥራት ማንሳት ያለብን፡፡

አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ከ ሲዳማ ቡና

በዚህ ግምገማ ላይ የተጋበዝነው የክለብ አሰልጣኞች እና ቡድን መሪዎች ነን፡፡ እኛ ለክለቡ አመራሮች እዚህ የተባለውን ሪፖርት ከማቅረብ ውጪ ስልጣን የለንም፡፡ በክለቦች ህልውና ላይ ፈላጭ ቆራጭ የሆኑት አመራሮችን ፌዴሬሽኑ በዚህ ግምገማ ላይ እንዲገኙ ማድረግ ነበረበት፡፡ በእነሱ ፊት ይህ ደንብ ላይ ውይይት ካልተደረገ ትርጉም የለውም፡፡ 

ደንቡን አሁን ይፈጸም ተብሎ ዱብ እዳ ከማድረግ ይልቅ ቢያንስ የአመት ቢበዛ የ3 አመት ጊዜ ተሰጥቶ ክለቦች እንዲዘጋጁበት መደረግ ያለበት፡፡ 

የሴቶች እግርኳስ ተጠቃሚ እያደገ ያለው ተጫዋቾቹን ብቻ አይደለም፡፡ ቤተሰቦቻቸውነም ጭምር ነው፡፡ አቅም ያላቸውን ተጫዋቾች ከገጠር ወረዳዎች ለማምጣት ብዙ እንለፋለን፡፡ ከዛ በኋላ ግን እስከ ብሄራዊ ቡድን ምርጫ ደርሰው ቤተሰባቸውን ሲረዱ እንመለከታለን፡፡ በደንቡ ምክንያት መውረድ የሚኖር ከሆነ ለእነዚህም እድል መዝጋት ነው የሚሆነው፡፡

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የሊግ ኮሚቴ የስራ ሒደት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ገብረስላሴ አስተያየቶቹን በቀናነት እንደሚመለከቱ ጠቁመው ፌዴሬሽኑ በሴቶች እግርኳስ ላይ ካስቀመጠው የመካከለኛ ጊዜ እቅድ መካከል በሊግ እርከን ከፋፍሎ ማወዳደር ዋነኛው መሆኑን እና ክለቦች እንደ ክለብ ብቻ ሳይሆን እንደሀገር በማሰብ ተግባራዊ ለማድረግ መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ገልፀዋል፡፡ 

አቶ አበበ ገላጋይም የተቀመጠውን ደንብ ማክበር እንደሚገባ ገልጸው በጉዳዩ ላይ ግን ፌዴሬሽኑ ግትር አቋም እንደማይኖረውና በቀጣይ የሚታይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

Leave a Reply