“ከሲሸልሱ ቡድን ጋር ሁለት ጥሩ የሆነ ጨዋታን እንጠብቃለን” ማርት ኖይ

በ2017 ቶታል ካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ የኢትዮጵያው ተወካይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሜዳው ውጪ ኮት ዲኦርን ፕራስሊን ላይ ይገጥማል፡፡ ክለቡ ለጨዋታው ሐሙስ ወደ ሲሸልስ የተጓዘ ሲሆን ዕረቡ እለት ቦሌ በሚገኘው የልምምድ ቦታው የተገኘችው ሶከር ኢትዮጵያ የአሰልጣኝ ማርት ኖይን አስተያየት እንደሚከተለው አቅርባለች፡፡

ስለዝግጅት

“የኛ ዝግጅት በተጠናረከ መልኩ የተጀመረው በቅዳሜው ጨዋታ ከንግድ ባንክ ጋር በነበረን ጨዋታ ነው፡፡ ቡድኑ በዛ ጨዋታ ጥሩ ተንቀሳቅሷል፡፡ በዚው እንደሚቀጥሉ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ እስከምን ድረስ እንደተዘጋጀን ለመናገር ሁሌም ያስቸግራል፡፡ጥሩነታችንን ልንመለከት የምንችለው በጨዋታ ወቅት ብቻ ነው፡፡ አስቀድሜ እንደተናገርኩት ከባንክ ጋር ያደረግነው ጨዋታ ጥሩ ነበር፡፡ ስለዚህም ተጫዋቾቻችን በዚሁ እንደሚቀጥሉ እንጠብቃለን፡፡ በጨዋታው ላይ የተሰለፉት 14 ተጫዋቾች ለአሁንም ጨዋታ ዝግጁ ናቸው፡፡ ፕሪንስ እና ብሩኖ መጫወት ስለሚችሉ ጥሩ ነገር ነው፡፡ ከሲሸልሱ ቡድን ጋር ሁለት ጥሩ የሆነ ጨዋታን እንጠብቃለን፡፡ በሲሸልስም ይሁን በኢትዮጵያ በሚኖረው ጨዋታ ጥሩ መጫወት አለብን፡፡”

ስለኮት ዲ ኦር

“በተወሰነ መልኩ ስለሲሸልስ ቡድኖች መረጃው አለን፡፡ ባለፈው ዓመት ከሴንት ሚሸል ጋር ተጫውተናል፡፡ በሀዋሳ ደግሞ የሲሸልስ ብሄራዊ ቡድን ከኢትዮጵያ ጋር ሲጫወት አይቻለው፡፡ የአጨዋወት ስርዓታቸውን እና ስለተጫዋቾቹን በተወሰነ መልኩ እንውቃለን፡፡ ከማዳጋስካር እና አንድ ከዩጋንዳ ተጫዋች እንዳላቸው ተነግሮኛል፡፡ በተጋጣሚያችን ላይ ትኩረታችንን ከመጠን ያለፈ መሆን የለበትም በእኔ አስተሳሰብ፡፡ በራሳችን እናምናለን፡፡ ጠንካራ የሆነ የአጨዋወት ዘይቤን ከተጫዋቾቼ ጋር እያዳበርኩ ነው፡፡ ስለዚህም ይህንን በሁለቱም ጨዋታዎች ለመተግበር እንፈልጋለን፡፡”

የምድብ ማጣሪያ ጉዞ

“ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመምጣቴ በፊት በቡርኪናፋሶ፣ ታንዛኒያ እና ሞዛምቢክ ሰርቻለው፡፡ ስለዚህም ከኢንተርናሽናል ጨዋታዎች የተማርኩት አንድ ነገር ምንድ ነው ከመጠን ያለፈ አርቀን ማሰብ እንደሌለብን ነው፡፡ በመጀመሪያ ሁለቱን ገጥሚያዎች እንያቸው ከዛ ቀጣዮቹን ጨዋታዎች መመልከት ይሽላል፡፡ እውነታውን ሁሌም ማየት ስላለብን በመጀመሪያ ከፊታችን ያሉትን ሁለት ጨዋታዎች እናሸንፍ፡፡”

Leave a Reply