ሶስተኛው ዙር የዳሽን-አርሰናል የታዳጊዎች እግርኳስ አሰልጣኝነት ስልጠና ተሰጥቷል

ዳሽን ቢራ አዘጋጅነት በአዲስ አበባ ለሁለት ቀናት የተሰጠው የታዳጊ እግርኳስ አሰልጣኞች ስልጠና ዓርብ ተጠናቋል፡፡ 

የዳሽን ቢራ አጋር የሆነው የእንግሊዙ ክለብ አርሰናል የታዳጊ ተጫዋቾች ሁለት አሰልጣኞችን በመላክ ለ32 ሰልጣኞች ስልጠና ተሰጥቷል አድርጓል።

የአርሰናል እግርኳስ ማሰልጠኛ አካዳሚ ሃላፊ የሆነው ሳይመን ማክማነስ እና ካርለን ኤድጋር ስልጠናው የሰጡ እንግሊዛዊያን ናቸው፡፡ በሁለት ቀናት ስልጠና ሰልጣኞች የንድፈ ሃሳብ እና የተግባር ትምህርቶችን እንዲቀስሙ መደረጉን የዳሽን ቢራ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዴቭሊን ሄንስወርዝ በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ገልፀዋል፡፡ የተግባር ትምህርቱ ሲኤምሲ አከባቢ በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የልምምድ ሜዳ ተደርጓል፡፡ ዳሽን እንደዚህ ዓይነት ያሉ ስልጠናዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የዳሽን ቢራ የገበያ ዋና ሃላፊ ሪታ ፀሃይ ተናግራለች፡፡

ስልጠናው ከሰጡት አሰልጣኞች መካከል አንዱ የሆነው ካርለን ኤድጋር ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጠው አስተያየት የታዳጊዎች ስልጠና አራት መሰረታዊ ነገሮችን መያዙን ተናግሯል፡፡ “የአፍሪካ አሰልጣኞችን ተመልክተን ጥሩ አቅም እንዳለ ተመልክተናል በእድገት ደረጃ፡፡ እዚህ ላይ የምንመለከተው አንድ ታዳጊ ተጫዋች በታክቲክ፣ ቴክኒክ፣ በተክለ ሰውነት፣ በአዕምሮ እና ማህበራዊ በሆኑ ነገሮች ላይ ማሳደግ ነው፡፡ በታዳጊ ስልጠና ላይ የተሰማሩ ሰዎችን የምናበረታታው እኒህን ነገሮች እንዲሰሩ ነው፡፡ ይህ የታዳጊ አሰለጣጠን ዘዴ በዩናይትድ ኪንግደም በሚገኙ የእግርኳስ ትምህርት ቤቶች የሚሰጥ በመሆኑ ተመሳሳይ ነው፡፡”

አሰልጣኝ ኤድጋር ሲቀጥል የአፍሪካ እና አውሮፓ እግርኳስ መለያየቱ የታወቀ ቢሆንም በታዳጊ ስልጠና ላይ ተመሳሳይ እንደሆነ አስረድቷል፡፡ “ይህ ስልጠና ለእግርኳስ ነው የተዘጋጀው፡፡ የሁሉም እግርኳስ የየራሱ የሆነ ባህል በውስጡ ይኖረዋል፡፡ ይህ ተፈጥሯዊ ነው፡፡ መሰረታዊ በሚባሉ ጉዳዮች ላይ  እና በታዳጊ እግርኳስ ላይ ግን ቅድም የጠቀስኳቸው አራት ነገሮች ተመሳስለው ይታያሉ፡፡”

በስልጠናው ላይ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ቡድኖች፣ ከእግርኳስ ፌድሬሽን፣ ከክልል ስፖርት ኮሚሽኖች እና ከግል የታዳጊዎች እግርኳስ ፕሮጀክት የተወጣጡ አሰልጣኞች ተሳትፈዋል፡፡ በስልጠናው ማጠናቀቂ ላይ በበሻሌ ሆቴል የስልጠናው ተሳታፊዎች የምስክር ወረቀት ከዋና ስራ አስፈፃሚው ሄንስወርዝ እጅ ተቀብለዋል፡፡

Leave a Reply