ሀሪሰን ሄሱ በቤኒን የአመቱ ኮከብነት ሽልማት አሸናፊ ሆነ

የኢትዮጵያ ቡናው ግብ ጠባቂ ሃሪሰን ሄሱ የሀገሩ ቤኒን ትልቁ የእግርኳስ ድረገፅ የሆነው ቢጄ ፉት (BJFOOT) በየዓመቱ በሚያዘጋጀው እና በውድድር ዘመኑ ጥሩ እንቅስቃሴ ያሳዩ የቤኒን ዜጋ የሆኑ ተጫዋቾች በሚሸለሙበት ውድድር ተሸላሚ ሆኗል። ሃሪሰን ሽልማቱን ማሸነፍ የቻለው የዓመቱ ምርጥ በአፍሪካ ውስጥ የሚጫወት ቤኒናዊ ግብ ጠባቂ በሚለው የውድድር ምድብ ነው።

በድረገፁ ላይ በሰፈረው መረጃ መሠረት ሃሪሰን በፈረንጆቹ 2016 ለክለቡ ኢትዮጵያ ቡና ካደረጋቸው ጨዋታዎች ውስጥ በ17ቱ ግብ ሳይቆጠርበት መውጣቱ እንዲሁም በአመቱ ባሳየው ጥሩ እንቅስቃሴ በሽልማቱ የመጨረሻ ተመራጮች ውስጥ መግባት ችሎ የነበረ ሲሆን በቱኒዚያው ክለብ አፍሪካን የሚጫወተው ጃክዌስ ቤሳን እና የጋቦኑ ሴንተር ምቤሪ ሰፖርቲፍ ክለብ ግብ ጠባቂ የሆነው ጃማል ፋሳሲን በድምፅ በመብለጥ የዓመቱ ምርጥ በአፍሪካ ሊግ የሚጫወት ግብ ጠባቂ ተብሎ ተመርጧል። በውድድሩ የአንባቢያን ድምፅ 30% የድረገፁ አርታኢያን ድምፅ ደግሞ 70% ሲይዝ ሃሪስን አንባቢያኑን 20% እንዲሁም የድረገፁን ፀሀፊዎች 47% ድምፅ በድምሩ የ67% መራጮች ይሁንታን አግኝቶ ነው ማሸነፍ የቻለው። ተጫዋቹ በዚህ ሽልማት ሲያሸንፍም ሆነ በዕጩነት ሲቀርብ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ሀሪሰን የእግርኳስ ህይወቱን በሃገሩ ቤኒን ዳጄ ለሚባል ክለብ በመጫወት የጀመረ ሲሆን ኤኤስ ፖሊስ፣ ድራጎንስ ድ ኦውሜ እንዲሁም የኮንጎ ብራዛቪሉ ኤኤስ ቼሚኖትስ ሌሎች ሃሪስተን ተጫውቶ ያለፈባቸው ክለቦች ናቸው። በ2013ቱ የአልጄሪያው የአፍሪካ ወጣቶች ዋንጫ እና በተወሰኑ የወዳጅነት ጨዋታዎች ላይ የሀገሩን ማሊያ አድርጎ መጫወት የቻለው ሃሪስን ከ2008 ዓ.ም. መጀመሪያ አንስቶ ደግሞ ኢትዮጵያ ቡናን እያገለገለ ይገኛል።

Leave a Reply