” መጪው ጊዜ ለእኔም ለኤሌክትሪክም መልካም ይሆናል” ፍፁም ገብረማርያም 

በፕሪምየር ሊጉ ምርጥ ወቅታዊ አቋም ላይ ከሚገኙ ተጫዋቾች አንዱ ፍጹም ገብረማርያም ነው፡፡ በጥር ወር የሶከር ኢትዮጵያ ምርጥ ቡድን ውስጥ የተካተተ ሲሆን ባለፉት 6 ጨዋታዎች 5 ጎሎችን አስቆጥሯል፡፡

ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውድድር ከተገኙ ጥቂት የሊጉ ተጫዋቾች አንዱ የሆነው ፍጹም በወለጋ ዩኒቨርሲቲ በነበረው የ3 አመታት ቆይታ በ መቀለ ፣ ጎንደር እና ሀዋሳ በተስተናገዱት የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውድድሮች ላይ የዩኒቨርስቲውን ቡድን በአጥቂነት እየመራ በመጀመሪያው አመት 9 እንዲሁም በተቀሩት ሁለት አመታት በእያንዳዳቸው 12 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል።  በመቀለ እና  በጎንደር ኮከብ ግብ አግቢ እንዲሁም ቡድኑ እስከፍፃሜ በተጓዘበት  የሀዋሳው ውድድር ኮከብ ተጨዋች ሆኖ ለመመረጥም በቅቷል።

ከዚህ በተጨማሪም ከትምህርቱ ጎን ለጎን ለከተማው ዋና ቡድን ነቀምት ከተማ በመጫወት የእግር ኳስ ተጨዋችነትን በአማተርነት መጀመር ችሏል። በእነዚህ እንቅስቃሴዎቹ ትኩረትን የሳበው ተጫዋቹ በሚመረቅበት አመት 2002 ላይ በተለያዩ ክለቦች ሲፈለግ ቆይቶ በመጨረሻ ለሙገር ሲምንቶ ፊርማውን አኖረ ።

በሙገር ሲሚንቶ የሙሉ ጊዜ ኳስ ተጨዋች /professional player/ ሆኖም በ2003 ዓ.ም በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ መታየት ጀመረ ። በሙገር ቆይታውም በሁለት አመታት 30 ግቦችን በማስቆጠር የብዙዎችን ቀልብ መሳብ ችሏል፡፡

በ2005 ከተጨዋቹ ፈላጊ ክለቦች መሀከል አንዱ የነበረው ቅዱስ ጊዮርጊስ ተሳክቶለት አጥቂውን የቡድኑ አካል አደረገ። ከ 2005 – 2007 በቅዱስ ጊዮርጊስ የአፍሪካ ውድድሮችን ጨምሮ በተሳተፈባቸው ጨዋታዎች ላይም 33 ግቦችን ከመረብ አገናኝቷለል። በቅዱስ ጊዮርጊስ የመጨረሻው አመት ከጉዳት ጋር እየታገለ ጨርሶ አምና ኢትዮ ኤሌክትሪክን በነፃ ዝውውር በመቀላቀል 8 ግቦችን ሲያስቆጥር በዘንድሮው  ውድድር ደግሞ  7 ግቦችን  ከመረብ በማዋሀድ ለቡድኑ ከወራጅ ቀጠና መውጣት የበኩሉን አስተዋፅኦ አድርጓል። በዚህም ባሳለፍነው ወር ባሳየው እንቅስቃሴ የሶከር የኢትዮጵያ ምርጥ 11 ውስጥ መካተት ችሏል።

በስራ አክባሪነቱ እና በመልካም ባህሪው በተጫዋቾች እና ተመልካቾች ተወዳጅ የሆነው ፍፁም ገ/ማርያም ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረገው ቆይታ ስለወቅታዊ አቋሙ እና ስለ እግር ኳስ ህይወቱ ተናግሯህ፡፡

ስለ እስካሁኑ የእግር ኳስ ህይወቱ እና ስላሳየው ዕድገት

” ባለፉት አመታት በሙገር ሲሚንቶ ፣ በቅዱስ ጊዮርጊስ እና አሁን ደግሞ በምወደው ክለብ  ኢትዮ ኤሌክትሪክ ውስጥ ባጠቃላይ ጥሩ ጊዜ አሳልፊያለው ብዬ በሙሉ ልብ መናገር እችላለው። በእነዚህ አመታት ያሳየሁት እድገት ፈጣን ነው ማለትም ይቻላል። ከዩኒቨርሲቲ በወጣው በ14 ወራት ውስጥ ነው ለብሄራዊ ቡድን የተጠራሁት። በክለቦቹ ውስጥም ስኬታማ ጊዜ ነው ያሳለፍኩት። በሙገር ሁለት ጥሩ አመታትን አሳልፌያለው ። በቅዱስ ጊዮርጊስም በአፍሪካ ውድድሮች ላይ ጭምር ጎሎችን ማስቆጠር ችያለው። በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው እና ማሪያኖ ባሬቶ ዘመንም ለቤሔራዊ ቡድን የመጫወት ዕድሉ ነበረኝ። ከዚህ ከዚህ አንፃር የስካሁኑ የእግር ኳስ ህይወት ጉዞዬ ጥሩ እና በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ለውጥ ያየሁበት ነው ማለት እችላለው። ”

በቅዱስ ጊዮርጊስ የመጨረሻ አመት እንዲሁም አምና ስላሳየው የአቋም መውረድ

” በቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ የመጨረሻ አመት ቆይታዬ ላይ በከፍተኛ የወገብ ጉዳት እሰቃይ ነበር። በወቅቱ የክለቡ ሌሎች የአጥቂ ክፍል ተስላፊዎችም ጉዳት ላይ ነበሩ። በዚህም ምክንያት ክፍተቱን የሚሞላ ሰው ባለመኖሩ ከህመም ሳላገግም በመድሀኒት እየተስለፍኩ እጫወት ነበር። በዚህም ምክንያት ጉዳቱ ሊባባስብኝ ችሏል። በአካል ብቃቴ ላይም ከፍተኛ ተፅዕኖ ነበረው። የበፊቱን ብቃቴንም ለማሳየት ተቸግሬ ነበር። ይህ ወቅት አስቸጋሪ ጊዜ ያሳለፍኩበት ጊዜ ነበር። ነገር ግን ትልቅ ትምህርት ሰጥቶኝ አልፏል። ከዛ ውጪ እስካሁን ያለኝ ነገር በጥቅሉ ጥሩ የሚባል አይነት ነው ። ”

የኢትዮ ኤሌክትሪክ የመጀመሪያ ዙር ጉዞ

” የዘንድሮው አመት የኤሌክትሪክ የተጨዋቾች ስብስብ ከምንጊዜውን የተሻለ ነው ብዬ አስባለው። ሁሉም የቡድኑ ተጨዋቾች ትልቅ አቅም ያላቸው ናቸው። ሆኖም ግን ላለፉት ሦስት እና አራት አመታት ቡድኑ ላለመውረድ መጫወቱ ከፍተኛ የስነልቦና ችግር ፈጥሯል። ይህም በመሆኑ ብዙ ጨዋታዎች ላይ መምራት እየቻልን ውጤት ማጠበቅ እንዳችል አድርጎናል። ከዛ ውጪ ቡድኑ እስካሁን ያስመዘገበው ውጤት የተጨዋች ስብስቡን እና ሜዳ ላይ የሚያሳየውን ብቃት አይገልፀውም። አብዛኞቹ ጨዋታዎች ላይም በጨዋታ የበላይነቱን ወስደን ነው የጨረስነው። ”

በተጨዋችነቱ ስለሚመርጠው የጨዋታ ቦታ

” ከልጅነቴ ጀምሮ ስጫወት የቆየውት በፊት አጥቂነት ነው። ወደቀኝም ወደግራም አልወጣም ነበር። በቅዱስ ጊዮርጊስ የሶስት አመት ቆይታዬ የነበሩ የተለያዩ የቡድኑ አሰልኞች በ 4-3-3 አጨዋወት ይጠቀሙ ነበር። በዚህ አጨዋወትም ለፊት አጥቂነት የሚኖረው ቦታ አንድ በመሆኑ ምክንያት ከቀኝ እና ከግራ እየተነሳው መጫወትን መልመድ ችያለው። ነገር ግን ለኔ የመጀመሪያ ምርጫዬ የፊት አጥቂ ሆኖ መጫወት ነው። ከመስመር እየተነሱ መጫወት ብዙ አይቸግረኝም ፤ ለምጄዋለው ማለት እችላለው። ለምርጫ ከቀረበልኝ ግን የመጨረሻ አጥቂ ሆኖ መጫወቱ ለኔ የተሻለ ነው። ”

ስለዘንድሮው አቋሙ

” አመቱ ሲጀመር አካል ብቃቴ ልክ አልነበረም። በቀኝ ጡንቻዬ ላይም ደርሶ የነበረው ጉዳት አስቸግሮኝ ነበር። ህመም ሲሰማኝ ከማረፍ ይልቅ መድሀኒቶችን እየተጠቀምኩ ወደሜዳ መግባቴ በእጅጉ ጎድቶኛል። ይህም ቡድኑን በሙሉ አቅሜ እንዳላገለግል አድርጎኛል። በአመቱ መጀመሪያም በነዚህ ምክንያቶች ሳቢያ አቋሜ ይዋዥቅ ነበር። አሁን ላይ ግን በሂደት ወደ ጥሩ ነገር መጥቻለው ፤ በግማሽ አመትም 7 ጎሎችን አስቆጥሬያለው። የፍፁም ቅጣት ምት እና ሌሎችንም ዕድሎች ተጠቅሜ ቢሆን ኖሮ የጎሎቹ መጠን ከዚህም በላይ ከፍ ማለት ይችል ነበር። ”

ኢትዮ ኤሌክትሪክ በሁለተኛው ዙር

” በመጀመሪያው ዙር ከሜዳችን ውጪ ካደረግናቸው አምስት  ጨዋታዎች በአራቱ ነጥብ ተጋርተን መምጣት ችለናል። ባለፉት አመታት  ይህን ማሳካት ለክለቡ ከባድ ሆኖበት ነበር። ይህ ቡድኑ ላለው ጥንካሬ አንዱ ማሳያ ነው። በአጨዋወትም ወደፊት ገፍቶ ተጭኖ የሚጫወት ቡድን ነው። ዋናው የቡድኑ ችግር ካለፉት አመታት ጋር ተያይዞ ይመጣ  ስነልቦናዊ ድክመት ነው።  በሁለተኛውም ዙር በእርግጠኝነት ይሄ አይደገመም ብዬ ነው ማስበው። እንደቀደመው ጊዜ ባይሆንም ውበት ያለው እግር ኳስ የሚጫወት ውጤታማ ቡድን በሁለተኛው ዙር እንደምናሳይ አስባለው። ለዚህም የሀዋሳው ጨዋታ ፍንጭ ያሳየ ይመስለኛል። ”

ፍፁም ገ/ማርያም ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር በቀጣይ ጊዜያት

” መጪው ጊዜ ለእኔም ለኤሌክትሪክም መልካም ይሆናል ብዬ አስባለሁ። ከልጅነቴ ጀምሮ የክለቡ ደጋፊ ነበርኩ ፤ አሁንም ቡድኑን ከልቤ ነው የምወደው። ውጤት አጥቶ ላለመውረድ በተጫወተባቸው ጊዜያትም አብሬ እሸማቀቅ ነበር።  አሁን በምወደው ክለቤ እየተጫወትኩ እገኛለው በዚህም ደስተኛ ነኝ። በኤሌክትሪክ ገና ሁለት አመት ባይሞላኝም አምና 8 ግቦችን አስቆጥሪያለው ዘንድሮ ደግሞ 7 ደርሻለው በአጠቃላይ ከክለቡ ጋር ጥሩ የሆነ ጊዜም እያሳለፍኩ እገኛለው። አሁንም የተሻለ ጥረት አድርጌ ቡድኑን የተሻለ ቦታ ላይ ለማድረስ አልማለው። ”

በመጨረሻም…

” በቡድኑ ውስጥ አብረውኝ የሚጫወቱ ሁሉም ተጨዋቾች አሁን ላለውበት መልካም አቋም ላይ ለመገኘቴ ላደረጉልኝን ድጋፍ በጣም አመሰግናለሁ። በተለይም እንደ አዲስ ነጋሽ ያሉ የቡድኑን ሲኒየር ተጨዋቾች እና አጥቂው ሙሉአለም ጥላሁንን በሚያረገው ጥሩ እንቅስቃሴ ማመስገን ፈልጋለው። ወደቡድኑ ከመጣ ብኋላ ለመሀል ሜዳው ምሶሶ የሆነውን እና ብዙዎቹን ኳሶች አመቻችቶ ያቀበለኝን ዳዊት እስጢፋኖስንም ትልቅ ምስጋና ይገባዋል። ሁሌም ኳስ እሱ ጋር ሲሆን ለቡድኑ የራስ መተማመን ይጨምራል። በአሰልጣኝ ብርሁኑ ባዩ የሚመረው የአሰልጣኝ ቡድንም ክለቡ ላሳየው መሻሻል ትልቁን ድርሻ ይወስዳል። በመጨረሻም ይህን ዕድል ለሰጠኝ እና በሀገርውስጥ እግር ኳስ ላይ ብዙ እየለፋ የሚገኘውን ድረገፃችሁን ማመስገን እፈልጋለው ። ”

Leave a Reply