ቻምፒየንስ ሊግ | ቅዱስ ጊዮርጊስ አንድ እግሩን ወደ 1ኛ ዙር አስገብቷል

በ2017ቱ የቶታል አፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ኢትዮጵያን በመወከል የሚሳተፈው የአምናው የሊጉ ሻምፒዮን ቅዱስ ጊዮርጊስ በቅድመ ማጣሪያው የመጀመሪያ ጨዋታ የሲሼልሱን ኮት ድ ኦር ከሜዳው ውጪ በሳላህዲን ሰዒድ ሁለት ግቦች ታግዞ 2 – 0 ማሸነፍ ችሏል።

በፕራስሊን ከተማ በሚገኘው አሚቲዬ ስታዲየም በተደረገው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ የግብ ሙከራ እና የጨዋታ እንቅስቃሴ ብልጫ የነበረው ሲሆን በጨዋታው 40ኛ ደቂቃ ላይም በሳላህዲን ሰዒድ አማካኝነት ግብ በማስቆጠር በመሪነት ወደ መልበሻ ክፍል ተመልሰዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ኮት ድ ኦር የተሻለ ለመንቀሳቀስ ቢሞክርም በ60ኛው ደቂቃ ሳላህዲን ሰዒድ ለራሱም ለቡድኑም ያስቆጠራት ሁለተኛ ግብ ቅዱስ ጊዮርጊስ የ2017 የቻምፒዮንስ ሊግ ጉዞውን በድል መጀመሩን አረጋግጣለች።

የመልሱ ጨዋታ በቀጣዩ ሳምንት እሁድ በሀዋሳ ኢንተርናሽናል ስታዲየም ሲደረግ ቅዱስ ጊዮርጊስ በቀላሉ አሸንፎ ወደሚቀጥለው ዙር ያልፋል ተብሎ ይጠበቃል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ኮት ድ ኦርን በመጣል ማለፍ የሚችል ከሆነም በማጣሪያው አንደኛ ዙር ከኮንጎው ኤሲ ሊዎፓርድስ እና ከካሜሮኑ ዩኤምኤስ ዴ ሉም አሸናፊ ጋር የሚገናኝ ይሆናል። የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌዴሬሽን የአህጉራዊ የክለብ ውድድሮችን ምድብ ወደ 4 በማሳደጉ እና 16 ቡድኖችም በመጨረሻው ውድድር ተሳታፊ በመሆናቸው ውድድሩ ከአንደኛው የማጣሪያ ዙር በኋላ በቀጥታ ወደ ምድብ ድልድል የሚያመራ ይሆናል።

Leave a Reply