የጨዋታ ሪፖርት | መከላከያ የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ጉዞውን በድል ጀምሯል 

መከላከያ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የመጀመሪያ ዙር ፍልሚያ ከካሜሩኑ ዮንግ ስፖርትስ አካዳሚ ጋር ያደረገውን ጨዋታ በ 1-0 ውጤት ማሸነፍ ችሏል፡፡

የቡድኖቹ የመጀመሪያው አጋማሽ ፍልሚያ በርከት ያሉ የግብ ሙከራዎችን እና ፈጣን እንቅስቃሴ የተመለከትንበት ነበር ። ሙከራዎቹም ገና ከጅምሩ ነበር መታየት የጀመሩት። በ2ኛው ደቂቃ ማራኪ ወርቁ ከመሀል ሜዳ ጥሩ ኳስ ደርሶት ሳይጠቀምበት የካሜሩናዊያኑ ግብ ጠባቂ ቀድሞ ደርሶ አውጥቶበታል። ዮንግ ስፖርቶችም በተመሳሳይ በቀኝ መስመር  በዲዮቤን አማካይነት ወዲያውኑ ጥቃት ቢሰነዝሩም አቤል ማሞ ከመስመር የመጣችውን ኳስ በቅልጥፍና ይዟታል። እነዚህ ሁለት ጥቃቶች ሁለቱም ቡድኖች ጨዋታውን አጥቅተው እና ወደፊት ገፍተው እንደሚጫወቱ ያመላከቱ ነበሩ ።

መከላከያዎች በ6ኛው እና በ8ኛው ደቂቃ ላይ በሳሙኤል ሳሊሶ እና በሚካኤል ደስታ ጥሩ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል። በተጨማሪም 12ኛው ደቂቃ ላይ የተሻ ግዛው ሳሙኤል ሳሊሶ ከመሀል ሜዳ ያሻገረለትን ኳስ ከሳጥን ውስጥ  በቀኝ መስመር የሞከረው እና ራሱ የተሻ ግዛው በ36ኛው ደቂቃ በቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ ሳሙኤል ታዬ ከግቡ አፋፍ ላይ ሞክሮ ግብ ጠባቂው የያዘበት ኳሶች በባለሜዳዎቹ በኩል በእጅጉ ለጎል የቀረቡ ሙከራዎች ነበሩ ። የግራ መስመር አማካዩ ሳሙኤል ሳሊሶም ከረጅም ርቀት ይሞክራቸው የነበሩ ኳሶችም ቡድኑ ከፈጠራቸው የግብ አጋጣሚዎች መሀል የሚጠቀሱ ነበሩ።

ጨዋታውን ሙሉ ለሙሉ በማጥቃት ላይ ተመስርተው በመጫወት አሸንፈው ለመመለስ ያሰቡት ዮንግ ስፖርት አካዳሚዎችም ምንም እንኳን እንደመከላከያዎች የጠሩ የግብ እድሎችን ባይፈጥሩም በተለያዩ አጋጣሚዎች ባለሜዳዎቹን መረበሻቸው ግን አልቀረም።  ከምበተለይ በ9ኛው ደቂቃ ላይ የፊት አጥቂው ፌስተስ አሳንጎ ከተከላካዮች በረጅሙ የተላከለትን ኳስ ተጠቅሞ ከ አቤል ጋር አንድ ለአንድ የተገናኘበት እና ሙከራው ወደውጪ የወጣበት ቡድኑ የጨዋታው ምርጡ ሙከራ ነበር። በ35ኛው እና 38ኛው ደቂቃ ላይም የመሀል አማካዩ ሪቻርድ ኢቦንጉ እና የእጥቂ አማካዩ ንዶንጎ ጋሌባ ከሳጥን ውጪ በቀጥታ የሞከሯቸው እና  አቤል ማሞ የያዛቸው ኳሶችም በእንግዳው ቡድን የተደረጉ ሌሎች ሙከራዎች ነበሩ።

ጨዋታው በእንዲህ አይነት ሁኔታ ቀጥሎ 41ኛው ደቂቃ ላይ የተሻ ግዛው ከቀኝ መስመር ያሻማውን የማዕዘን ምት የመሀል ተከላካዩ አዲሱ ተስፋዬ በግንባሩ በመግጨት የጨዋታውን ብቸኛ ጎል ማስቆጠር ችሏል። ከጎሏ መቆጠር በኋላም በዮንግ ስፖርቶች በኩል በተመሳሳይ መንገድ ሲያ ሳንጉ ከግራ መስመር ያሻማውን የማዕዘን ምት በመጠቀም የመሀል ተከላካዩ ኦሊቨር ቴቼንግ በግንባሩ ለማስቆጠር ቢሞክርም ኳሷ በግቡ አግዳሚ ወጥታለች።

ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው በተለየ ጨዋታው ተቀዛቅዞ የታየበት ነበር። በሚያስገርም ሁኔታ እስከመጨረሻው ድረስ በሙሉ ሀይላቸው ሲያጠቁ የነበሩት ዮንግ ስፖርቶች በኳስ ቁጥጥሩ የበላይነቱን ቢወስዱም ከመከላከያዎች የተከላካይ ክፍል ጀርባ ዘልቀው ለመግባት ከብዷቸው ታይቷል ። ከኋላ መስመር በረጅሙ ይላኩ የነበሩ ኳሶችንም በመጠቀም የግብ እድል ለመፍጠር ያደርጉ የነበሩት ጥረት አጥቂዎቻቸው በተደጋጋሚ ከጨዋታ ውጪ በመሆናቸው ሳቢያ ስኬታማ ሊሆንላቸው አልቻለም።

ያም ቢሆን በአብዛኛውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በላይኛው የሜዳ ክፍል ላይ ኳስን ተቆጣጥረው መጫወትን መምረጣቸው መከላከያዎችን ከራሳቸው ሜዳ በብዛት እንዳይወጡ በማድረጉ ባለሜዳው ቡድን ሊያደርስባቸው ሚችለውን ጫና በእጅጉ ቀንሶላቸዋል።

በመጀመሪያው አጋማሽ ከብዙ አማራጮች የግብ ዕድሎችን ሲፈጥሩ የነበሩት መከላከያዎችም በሁለተኛው 45  ላይ ከኋላ በረጅሙ ለአጥቂዎች በሚላኩ ኳሶች ላይ ጥገኛ ሆነው ታይተዋል። በሁለተኛው አጋማሽ መጀመሪያ ላይ  መከላከያዎች  በሁለት አጋጣሚዎች ያገኟቸውን የማዕዘን ምቶች ለመጠቀም ባደረጉት ጥረት ካሜሮናዊያኑን ጫና ውስጥ መክተት ችለው የነበረ ቢሆንም ተጨማሪ ጎል ማስቆጠር ግን አልቻሉም። በአብዛኛው ሰዐትም ቡድኑ የተወሰደበትን የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ተከትሎ ወደኋላ በማፈግፈግ ነበር ያሳለፈው ። ኳስ መንጠቅ በቻሉባቸው አጋጣሚዎችም ጥሩ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን አግኝተው የነበረ ቢሆንም በተጋጣሚያቸው ሜዳ ላይ መልሶ ማጥቃቱን ወደግብ ሊቀይር የሚችል የተጨዋች ቁጥር ብልጫ ስላልነበራቸው እና በረጅሙ ወደአጥቂዎቹ የሚላኩ ኳሶች የተመጠኑ ባለመሆናቸው ስኬታማ ሳይሆኑ ቀርተዋል። በተለይም ቴውድሮስ ታፈሰ እና ኦጉታ ኦዶክ ተቀይረው ወደሜዳ ከገቡ በኋላ ቡድኑ ውጤቱን አስጠብቆ ለመውጣት ያሰበ በሚመስል መልኩ ነበር የተጫወተው። በዚህም ምክንያት መከላከያዎች ከዮንግ ስፖርት ተከላካዮች ጀርባ ይታይ የነበረውን ሰፊ ርቀት መጠቀም ሳይችሉ ጨዋታው በአዲሱ ተስፋዬ ብቸኛ ግብ በ 1-0 አሸናፊነት አጠናቀዋል።

የሁለቱ ቡድኖች የመልስ ጨዋታ በቀጣዩ ሳምንት ይደረጋል።

Leave a Reply