ድሬዳዋ ከተማ 2 ጋናዊያን ሲያስፈርም 6 ተጫዋቾችን አሰናብቷል

ድሬዳዋ ከተማ የሁለት ጋናዊያን ተጫዋቾችን ዝውውር አጠናቋል፡፡ የተከላካይ አማካዩ ኢማኑኤል ላሬያ የሚባል ሲሆን በአጥቂ ስፍራ የሚጫወተው ደግሞ ሀምዛ መሀመድ ይሰኛል፡፡ ድሬዳዋ ከተማ ከሁለቱ ተጫዋቾች ጋር ከጃንዋሪ 31 በፊት የተስማማ በመሆኑ በሁለተኛው ዙር ይጠቀምባቸዋል፡፡

የአክራ ኸርትስ ኦፍ ኦክ ከ20 ዓመት በታች እና መጋቢ ክለብ በሆነው አውሮራ ክለብ ውስጥ መጫወት የጀመረው የ21 አመቱ ኢማኑኤል ከ3 ዓመታት በፊት ወደ ኸርትስ ኦፍ ኦክ ዋናው ቡድን አደገ። በ2014/15 እና በ2015/16 የውድድር ዓመታትም ለጋናው ታላቅ ክለብ ተጫውቷል።

ለኸርትስ ኦፍ ኦክ በብዛት በተከላካይ አማካይ ስፍራ ላይ የተጫወተው ኢማኑኤል ከኸርትስ ኦፍ ኦክ ጋር የነበረው ኮንትራት ሲያበቃ በገንዘብ ሊስማሙ ስላልቻሉ ቆይታውን አላራዘመም።

ኢማኑኤል ላሬያ

ሌላው ፈራሚ ሀምዛ መሀመድ (ከርዕሱ በላይ ነጭ ማልያ ለብሶ የሚታየው) በበርካታ የጋና ክለቦች የተጫወተ ልምድ ያለው አጥቂ ነው፡፡ መስቴአቴ ኢንቮስ በተሰኘ የወጣቶች ክለብ ውስጥ መጫወት የጀመረው ሀምዛ በጋና ፕሪምየር ሊግ ለሚጫወተው ሊበርቲ ፕሮፌሽናልስ ክለብ እ.ኤ.አ. በ2004 ፈረመ።

በኋላም በኸርትስ ኦፍ ላየንስ ከ2006-2007፣ በአሻንቴ ኮቶኮ ከ2007-2008፣ በሪል ቴማሌ ዩናይትድ ከ2009-2012፣ በቤሬኩም ቼልሲ ከ2012-2015፣ በመጨረሻም ከ2015-2016 በአክራ ኸርትስ ኦፍ ኦክ ተጫውቷል። በ2008 ለጋና ከ20 ዓመት በታች ቡድን ተጠርቶ 2 ጨዋታ አድርጎ 1 ግብ ማስቆጠርም ችሏል።

ደካማ የውድድር ዘመን እያሳለፈ የሚገኘው ድሬዳዋ ከተማ በሁለተኛው ዙር ተጠናክሮ ለመቅረብ ዝውውር ላይ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል፡፡ አድናን ቃሲምን ያስፈረመ ሲሆን ምስጋናው ወልደዮሃንስ ፣ ሮቤል ግርማ ፣ ተስፋዬ ኃይሶ ፣ አልሳሪ አልመሃዲ ፣ ኤርሚያስ በለጠ እና ሰሚር ነስሩ ደግሞ ከክለቡ ጋር የተለያዩ ተጫዋቾች ናቸው፡፡ አሰልጣኝ ዘላለም ባሰናበቷቸው ተጫዋቾች ምትክ ተጨማሪ ተጫዋቾች ለማስፈረም እየተንቀሳቀሱ መሆኑም ታውቋል፡፡ 

Leave a Reply