የፕሪምየር ሊግ 1ኛ ዙር የክለቦች ዳሰሳ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመርያ ዙር ከተጠናቀቀ ቀናትን አስቆጥሯል፡፡ ሶከር ኢትዮጵያም የክለቦቹን ግማሽ የውድድር ዘመን ዳሰሳ በተከታታይ ታቀርባለች፡፡ ዮናታን ሙሉጌታ እና ሚልኪያስ አበራ በዚህ ፅሁፍ አንደኛውን ዙር በመሪነት ያጠናቀቀው ቅዱስ ጊዮርጊስን እንዲህ ባለ መልኩ ዳሰውታል፡፡


የመጀመሪያ ዙር የቅዱስ ጊዮርጊስ ጉዞ

የቅዱስ ጊዮርጊስ የዘንድሮው የሊጉ ጅማሮ የሚያስደንቅ ነበር ። በመጀመሪያ ያደረጋቸውን ሶስት ጨዋታዎች በድል ማጠናቀቅ ብቻ ሳይሆን በሶስቱ ጨዋታዎች ስምንት ጎሎችንም አስቆጥሮ የውድድር ዘመኑን በከፍተኛ የበላይነት ሊያጠናቅቅ ይችላል የሚል ሰፊ ግምት ያስቸረውን ውጤት አስመዝግቦ ነበር።

ሆኖም ግን ክለቡ በቀጣይ ያደረጋቸው ሶስት ጨዋታዎች ውጤት የቀደመውን አስተያየት ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነበር። በእነዚህ ሶስት ጨዋታዎችም አንዱን በመሸነፍ በተቀሩት አቻ ወጥቶ ሁለት ነጥቦችን ብቻ ለማሳካት ተገዷል። ከዚህ ጊዜ አንስቶም የክለቡ ደጋፊዎች በቡድኑ ውጤት መውረድ እና በጨዋታ አቀራረቡም ላይ ደስተኛ አለመሆናቸውን ማሰማት የጀመሩበት ወቅት ነበር።

ያም ሆኖ ቡድኑ በቀጣይ ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች ሶስት አሸንፎ በአንዱ ብቻ ሽንፈት በመቅመስ ወደጥሩ አጀማመሩ የተመለሰ መሰለ። ከነዚህ ከታህሳስ ወር አጋማሽ እስከ ጥር ወር መጀመሪያ ከተደረጉ ጨዋታዎች ውስጥ ቡድኑ ታህሳስ 23 ቀን በኢትዮጵያ ቡና የተረታበት ጨዋታ መኖሩ የደጋፊዎቹን ደስታ ሙሉ እንዳይሆን ያደረገ ነበር። ከዚህ በተጨማሪም ቡድኑ በመቀጠል ከ11ኛ ሳምንት እስከ 14ኛ ሳምንት ባደረጋቸው ጨዋታዎች ኤሌክትሪክን ብቻ በአንድ ግብ በመርታት በቀሪዎቹ ጨዋታዎች በ 1-1 የአቻ ውጤት ከተጋጣሚዎቹ ጋር መለያየቱ የደጋፊዎቹን ጥያቄ ጠንክሮ እንዲመጣ እና ተቃውሞውም ከዋናው አሰልጣኝ ሌላ ወደ ሙሉ የአሰልጣኞች ቡድን እንዲመጣ ያስገደደ ነበር ።

ቡድኑ በዚህ ወቅት በአራቱ ጨዋታዎች ማስቆጠር የቻለውም አራት ግቦችን ብቻ ነበር። ቢሆንም በደረጃው ሰንጠረዥ አናት ተፎካካሪ የሆኑት ቡድኖችም ያስመዘግቡ የነበሩት ውጤት እንደ ቅዱስ ጊዮርግስ ሁሉ ዝቀተኛ የነበረ በመሆኑ ቡድኑ የከፋ የደረጃ መንሸራተት አልገጠመውም ነበር። በዙሩ የመጨረሻ ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ሲገጥምም በሊጉ አናት ላይ በመሆን ነበር። በዚህ የ15ኛ ዙር ጨዋታም ቡድኑ 4 ግቦችን በማስቆጠር ጨዋታውን 4-1 በማጠናቀቅ የሊጉ አጋማሽ በአንደኝነት አገባዷል። ከዚህ ጨዋታ ውጤት በኋላም ደጋፊው በከፍተኛ ደስታ ውስጥ በመሆን ነበር የውድድሩን አጋማሽ ያጠናቀቀው።

የድቡኑ ውጤት ከአምናው ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነፃፀር

ቅዱስ ጊዮርጊስ ቻምፒዮን ሆኖ በጨረሰበት የ2008 የውድድር ዘመን የመጀመሪያ ዙር በ13 ጨዋታዎች እንደዘንድሮው ሁሉ 29 ነጥቦችን ሰብስቦ በአንደኝነት ነበር ያጠናቀቀው። ሆኖም ዘንድሮ የሊጉ ተሳታፊዎች ቁጥር በሁለት መጨመሩ ቡድኑ በጨዋታ በአማካይ ያስመዘገበውን ነጥብ ብዛት ከ2.2 ወደ 1.9 ዝቅ ያደርገዋል ። ከዚህ በተጨማሪም የቡድኑ የማሸነፍ ንፃሬ ከአምናው ጋር ሲነፃፀር ከ 69% ወደ 53% ቀንሷል። በሌላ በኩል ቡድኑ በየጨዋታው በአማካይ የሚያስቆጥረው እና የሚቆጠርበት የግብ መጠን በሁለቱም አመታት ተመሳሳይ ሆኗል ። በዚህም መሰረት ቅዱስ ጊዮርጊስ በሁለቱ አመታት የመጀመሪያው ግማሽ አመት ባደረጋቸው ጨዋታዎች በየጨዋታው በአማካይ 1.53 ግቦችን ሲያስቆጥር በአንፃሩ ደግሞ 0.46 ጎሎች ተቆጥረውበታል ።

የመጀመሪያው ዙር የቡድኑ አቀራረብ

በሆላንዳዊው አሰልጣኝ ማርት ኖይ የሚመራው የዘንድሮው ቅ/ጊዮርጊስ በዋነኝነት በ 4-3-3 የጨዋታ አቀራረብ ወደሜዳ ይገባል። መሀል ሜዳ ላይ በአንድ የተከላካይ አማካይ እና በሁለት የአጥቂ አማካዮች የሚጠቀም ሲሆን ሁለቱ የአጥቂ አማካዮች የተጋጣሚ ተጨዋቾን በራሳቸው ሜዳ ላይ ጫና የማሳደር እንዲሁም በሜዳው ስፋት እና ቁመት ሰፊ የሜዳ ክፍልን አካሎ የመጫወት ሚና ሲኖራቸው ይታያል ። ቡድኑ ውጤት ማስጠበቅ ሲፈልግ እና ጥቃት በሚሰነዘርበት አጋጣሚዎችም ይህ የመሀል ሜዳ የሶስትዮሽ ቅንጅት ይገለበጥና ከተከላካይ መስመሩ ፊት የሚኖሩትን የተከላካይ ባህሪ ያላቸውን ተጨዋቾች ቁጥር ወደ ሁለት ከፍ ያደርገዋል። በሌሎች አጋጣሚዎችም ቡድኑ ወደ 4 2 3-1 የሚጠጋ አጨዋወትን ሲተገብር ይስተዋላል ። በዚህ መሰረትም በቀደመው ቅርፅ የመስመር አጥቂ የየበሩት ተጨዋቸች የመስመር አማካይነት ሚና ይኖራቸዋል። የቅዱስ ጊዮርጊስ ዋነኛ የማጥቃት እማራጭ ከሁለቱ መስመሮች ያሚነሳ ሲሆን አልፎ አልፎም ከተከላከካይ መስመሩ እና ከጥልቅ አማካዮች በረጅሙ የሚላኩ ኳሶች ለቡድኑ ሌላ የማጥቂያ አማራጭ ሲሰጡት ይታያሉ።

ጠንካራ ጎን

የቅዱስ ጊዮርጊስ ዋነኛው ጠንካራ ጎኑ የማሸነፍ ስነልቦናው ነው። ላለፉት አመታት ክለቡ የገነባው የስኬት ታሪክ እንደሁልጊዜው ሁሉ ዘንድሮም በተጋጣሚዎቹ ላይ የአእምሮ የበላይነት ሲያጎናፅፈው እና በጨዋታ እንቅስቃሴ ቢበለጥም እንኳን ድል አድርጎ ከሜዳ ሲወጣ ይታያል። ከዚህ ጋር ተያይዞም የደጋፊዎቹ ሚና ሳይጠቀስ ሚታለፍ አይደለም። በተለይም በዚህ አመት በጀመሩት ዜማ እየተቀባበሉ በመደገፍ አዲስ ዘይቤ ለቡድናቸው ድጋፍን ሲሰጡ እና ቡድኑ ሜዳ ላይ በተዳከመባቸው ጊዚያት በተቃውሞ ወደነበረበት አቋም እንዲመለስ ቀጥተኛ አስተዋፅኦ ሲያደርጉ ታይቷል።

የቡድኑ የተጨዋቾች ስብስብ ሌላው ጠንካራው ጎኑ ነው። አሁንም የቡድኑ ተጨዋቾች ጥራት ከሌሎቹ ክለበች ጋር ሲነፃፀር የተሻለ የሚባል ነው። ከተጠባባቂ ወንበር ላይ በመነሳትም ውጤት መቀየር የሚችሉ ተጨዋቾችን በመያዙ በተደጋጋሚ ተጠቃሚ ሲሆን ታይቷል።

በብዛት በሶስት አጥቂዎች የሚገባው ቅዱስ ጊዮርጊስ በንፅፅር ሲታይ የተሻለ የአጥቂ ክፍል አለው። ቡድኑ በመጀመሪያው ዙር 23 ግቦችን ሲያስቆጥር ሌላ ይህን ያህል የጎል ብዛት ያመዘገበ ቡድን የለም። ከእነዚህ ግቦችም ውስጥ 82% የሚሆኑት በአጥቂ ስፍራ ተጨዋቾች የተቆጠሩ ናቸው ። በተጨማሪም የመስመር አጥቂዎቹ የተጋጣሚን የመስመር ተከላካዮች የሚያፍኑበት እና የተገደበ የማጥቃት ተሳትፎ እንዲኖራቸው የሚያደርጉበት መንገድ እንደጠንካራ ጎን ሊጠቀስ የሚገባው ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞም የተከላካይ ክፍሉን ማንሳትም ተገቢ ነው። በመጀመሪያው ዙር ጥቂት ጎል ካስተናገዱ ሶስት ቡድኖች መሀል አንዱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነው። ይህም ለጠንካራ የተከላካይ መስመሩ አንዱ እና ዋነኛው ማስረጃ ነው።

ደካማ ጎን

የቅድስ ጊዮርጊስ ዋነኛ ደካማ ጎን የቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት ተገማችነት መሆኑ እና የመሀል ሜዳው ድክመት ነው። ቡድኑ በአብዛኛው መስመሮችን ብቻ ለማጥቃት መጠቀሙ በተጋጣሚዎቹ ዘንድ በቀላሉ እንዲተነበይ ሲያደርገው  ታይቷል። በተለይም እንደ ፋሲል ከተማ ፣ ሲዳማ ቡና እና አዳማ ከተማ ያሉ ቡድኖች ይህንን የቡድኑን ድክመት ሲጠቀሙበት ተስተውሏል።

ሌላው የአማካይ መስመሩ መሀል ሜዳ ላይ በቁጥር በዝተው እና ተጠጋግተው በሚጫወቱ ቡድኖች የበላይነት ሲወሰድበት መታየቱ ነው። በተለይም የመስመር አጥቂዎቹ በቂ እገዛ በማያገኙባቸው አጋጣሚዎች ይበልጥ ሲቸገር ይታያል። የአማካይ መስመሩ በሶስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ የሚያደርጋቸው ቅብብሎች ስኬታማነትም ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ነው ። በተደጋጋሚ በተጋጣሚ የተከላካይ እና የአማካይ መስመሮች የሚቋረጡት እነዚህ ኳሶች ቡድኑ ባሜዳው ቁመት በቀጥታ ለሚሰነዝረው ስኬታማ ጥቃት አናሳነትም አንዱ ምክንያት ነው።

ሌላው የቡድኑ ድክመት የተጨዋቾቹ የግል ብቃት በተናጠል የሚወሩዱባቸው አጋጣሚዎች መበርከት ነው። በመጀመሪያው ዙር በርካታ የቡድኑ ቁልፍ ተጨዋቾች ተደጋጋሚ ጉዳትን ሲያስተናግዱ ተስተውልሏል። ይህም እንደ አንድ የቡድኑ የጨዋታ መስመርም ሆነ አጠቃላይ እንደ ቡድን በተጨዋቾች መሀከል ሊኖር የሚገባውን ውህደት ሲረብሸው ማየት ተችሏል።

ምንም እንኳን ተጋጣሚዎቹ ክፍተቱን ተጥቅመው ውጤት ሲያሳጡት ባይስተዋልም ቡድኑ በመጫወቻ መስመሮች መሀል በተለይ በሽግግሮች ወቅት ሰፊ ክፍተቶችን ሲፈጥር ማየት ተችሏል ። ወደማጥቃትም ሆነ ወደመከላከል በሚደረጉ ሽግግሮች ላይ ቡድኑ በሁለት የሚከፈልባቸው እና በተጨዋቾች መሀከል ሊኖር የሚገባው ርቀት ያላግባብ ሚሰፋባቸው ጊዜያት ቀላል አይደሉም። በተከላካይ እና በአማካይ መስመሩ መሀከልም ሚፈጠረው ክፍተት ለተጋጣሚ የአጥቂ አማካዮች የመንቀሳቀሻ ሰፊ ቦታ የሚሰጥ ሚሆንበትም አጋጣሚዎች ይበዛሉ።

በሁለተኛው ዙር ምን ይጠበቃል ?

ቅዱስ ጊዮርጊስ የመጀመሪያውን ዙር ብዙ ነጥብ በመሰብሰብ ፣ ብዙ ግብ በማስቆጠር እና ጥቂት ጎሎችን በማስተናገድ የመጀመሪያውን ዙር አጠናቋል። ከክለቡ ትልቅነት እንዲሁም ካለፉት አመታት ታሪኩ እና ካለው የተጨዋች ስብስብ አንፃር ዘንድሮም ዋንጫውን የማንሳት እድሉ ከፍተኛ ነው። በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ላይ መወዳደሩ በሊጉ የሚኖረውን ትኩረት ካልቀነሰው እና ጉዳት ላይ ያሉ ተጨዋቾች በሙሉ አቅም ወደሜዳ ከተመለሱ ሁለተኛውንም ዙር የመጀመሪያውን ዙር ባጠናቀቀበት መልኩ ሊቀጥል ይችላል።

የቡድኑ የመጀመሪያ ዙር ኮከብ ተጨዋች

ምንተስኖት አዳነ

ምንተስኖትየመጀመሪያውን ዙር በብዛት በመሀል ተከላካይነት በመሰለፍ ተጫውቷል። በትክክለኛ ቦታው  በተከላካይ አማካይነትም የተጫወተባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ። ሆኖም በአብዛኞቹ ጨዋታዎች ተመጣጣኝ እና ወጥ አቋም ማሳየቱ ተጨዋቹን ከቡድኑ ስብስብ ውስጥ የመጀመሪያው ዙር ምርጥ አድርጎ ያስመርጠዋል። በሶከር ኢትዮጵያ የህዳር ወር ኮከብ ተጫዋች ተብሎ የተመረጠ ሲሆን ለ2 ጊዜያት በምርጥ ቡድን ውስጥ መካተት ችሏል፡፡

ተስፋ ሰጪ ተጨዋች አቡበከር ሳኒ

አቡበከር ወደ ዋናው ቡድን ከተቀላቀለ 3ኛ አመቱን ቢይዝም ወደ ኮከብነት መሸጋገርና በመደበኛ ተሰላፊነት ቡድኑ ላይ አዎንታዊ ተፅእኖ መፍጠር የጀመረው ዘንድሮ ነው፡፡ ሊጉ ከመጀመሩ በፊት በተደረገው የአዲስ አበባ ዋንጫ ላይ በኮከብ ግብ አግቢነት መጨረሱም የሚታወስ ነው።

በሊጉ የዘንድውጪ ተጨዋቹ በመስመር በኩል የሚያደርገው እንቅስቃሴ ለቡድኑ የማጥቂያ ዋና አማራጭ እያደረገው ይገኛል። በሁለተኛው ዙር እና በቀጣዩ የክለቡ ጉዞ መልካም አገልግሎት የሚያበረክትበት ዕድልም ከፍተኛ ነው።

1 Comment

  1. እጅግ ድንቅ ግሩም ስራ ሶከር ኢትዮጵያዎች በርቱ እናመሰግናለን።

Leave a Reply