የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 1ኛ ዙር የክለቦች ዳሰሳ – ኢትዮ ኤሌክትሪክ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመርያ ዙር ከተጠናቀቀ ቀናትን አስቆጥሯል፡፡ ሶከር ኢትዮጵያም የክለቦቹን ግማሽ የውድድር ዘመን ዳሰሳ በተከታታይ እያቀረበች ትገኛለች፡፡ ዮናታን ሙሉጌታ እና ሚልኪያስ አበራ በዚህ ፅሁፍ አንደኛውን ዙር 11ኛ ደረጃ ይዞ ያጠናቀቀው ኢትዮ ኤሌክትሪክን እንዲህ ባለ መልኩ ዳሰውታል፡፡


የመጀመሪያ ዙር ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጉዞ

ከሊጉ መጀመር በፊት የአዲስ አበባ ዋንጫ ውድድርን አሸንፎ የነበረው የሁለት ጊዜ የሊጉ ዋንጫ ባለቤት ዘንድሮ ለዋንጫው ከሚፎካከሩ ቡድኖች አንዱ ይሆናል የሚል ግምት ተሰጥቶት ነበር። ነገር ግን የኢትዮ ኤሌክትሪክ የመጀመሪያ ዙር ጉዞ በአቻ ውጤቶች የተሞላ ነበር። ቡድኑም አብዛኛውን ጊዜ በወራጅ ቀጠና ውስጥ ነበር ያሳለፈው ።

አመቱ ሲጀመር ወደ ጅማ በማቅናት ከጅማ አባ ቡና ጋር ያለግብ አቻ በመለያየት ውድድር አመቱን የጀመረው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በሳምንቱ ወደ ድሬደዋ አቅንቶ 2-1 ውጤት ተሸንፎ ነበር። ቀጥሎ የተደረጉትን ሶስት ጨዋታዎችም አዲስ አበባ ላይ በማድረግ ሁሉንም ጨዋታዎች በ 1-1 ውጤት ነበር የጨረሰው ። በመቀጠልም በስድስት እና ሰባተኛው ሳምንትም ሁለት ተከታታይ ሽንፈት የደረሰበት ኢትዮ ኤሌክትሪክ 11ኛው ሳምንት ላይ ወላይታ ድቻን በአዲስ አበባ ስታድየም አሸንፎ የውድድር ዘመኑን የመጀመሪያ ድል ከማስመዝገቡ በፊትም በነበሩት ሶስት ጨዋታዎች ማሳካት የቻላቸው ሶስት ነጥቦች ከሶስት የአቻ ውጤቶች የመጡ ነበሩ። ከወላይታ ድቻው ድል በኋላም በመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎች ሁለቱን አቻ በመውጣት እና በአንዱ በመሸነፍ በመጨረሻው ሳምንት ሀዋሳ ከተማን አስተናግዶ ድል በማድረግ 15 ነጥቦችን ሰብስቦ ከወርጅ ቀጠናው በጥቂቱ በመራቅ ነበር የአመቱን የውድድር አጋማሽ ያጠናቀቀው።


የቡድኑ ውጤት ከአምናው ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነፃፀር

ኢትዮ ኤሌክትሪክ አምናም እንደዘንድሮው ከወራጅ ቀጠናው በሁለት ደረጃዎች ከፍ ብሎ ነበር የመጀመሪያውን ዙር ያጠናቀቀው። ሆኖም ግን አምና ከ 13ቱ ጨዋታዎች 4ቱን ማሸነፍ ችሎ ነበር። በዚህ ረገድ የቡድኑ የማሸነፍ ንጻሬ ከ 30% ወደ 13% ወርዷል። በሌላ በኩል ኢትዮ ኤሌክትሪክ ዐምና በተመሳሳይ የውድድር ጊዜ የገባበት የጎል መጠን ከዘንድሮው ጋር እኩል ነው። ዘንድሮ ያደረጋቸው ጨዋታዎች ከአምናው በብዛት በሁለት ከፍ ስለሚሉም ቡድኑ ከአምናው በአማካይ ዝቅ ያለ የጎል መጠን አስተናግዷል። ያም ቢሆን ያገባቸው ግቦች መጠን 11 ብቻ መሆናቸውን ደግሞ ስንመለከት ከአምናው በአንድ ጎል ዝቅ ብሎ እናገኘዋለን። ይህም ቡድኑ በአማካይ በጨዋታ የሚያስቆጥረውን የግብ መጠን ከ0.92 ወደ 0.73 ቀንሶታል። ከሰበሰባቸው ነጥቦች አንፃር ስንመለከት ደግሞ ቡድኑ በአማካይ በአንድ ጨዋታ የሚሰበስበው ነጥብ ከ 1.2 ወደ 1 ዝቅ ብሏል ።


የመጀመሪያው ዙር የቡድኑ አቀራረብ

የብርሃኑ ባዩ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በአመኙ የ 4-4-2ን እና የ 4-3-3 ን የተጨዋቾች አደራደርን እየያፈራረቀ ተጠቅሟል። በተለይ በመጀመሪያዎቹ ጨዋታዎች ላይ 4-3-3ን በተደጋጋሚ ሲጠቀም ቆይቶ የፊት አጥቂው ሙሉአለም ጥላሁንን ጉዳት ተከትሎ ነበር ወደ 4-4-2 ቅርፅ የመጣው። በዚህ መሰረትም ከፊት በፍፁም ገ/ማርያም እና ኢብራሂም ፉፋኖ እየተመራ ከመጀመሪያው በተሻለ በቁጥር በርከት ያሉ ግቦችን ሲያስቆጥር ተመልክተነዋል። ሀዋሳ ከተማን 2-0 በረታበት ጨዋታ ግን ቡድኑ እንደመጀመሪያው ሁሉ በሶስት አጥቂዎች ነበር የተጠቀመው። ኢትዮ ኤሌክትሪክ በተከላካይ መስመሩ ላይ በጉዳት እና በቅጣት ምክንያት ብዙ የጥምረት ለውጦችን እያደረገም ነበር የመጀመሪያውን ግማሽ የውድድር አመት ያጠናቀቀው። በተለይ በመሀል ተከላካይ ቦታ ላይ አማካዩን አዲስ ነጋሽን ከሌሎቹ የተከላካይ መስመር ተሰላፊዎች ጋር በተለያዩ ጨዋታዎች ሲያጣምር ታይቷል። ኤሌክትሪክ ከተከላካይ መስመሩ ይልቅ በአማካይ ክፍል ላይ የተሻለ መረጋጋት ይታይበታል። የአማካይ መስመሩ ሰፊ የመጫወቻ ቦታ ነፃነት በሚሰጠው ዳዊት እስጢፋኖስ ዙሪያ የተገነባ ሲሆን በአመዛኙ አንድ የተከላካይ አማካይን ከሁለት ወይም ከሶስት የአጥቂ አማካዮች ጋር በማዋሀድ የተሰራ ነው ።


ጠንካራ ጎን

በዚህ አመት ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከሜዳው ውጪ በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ላይ የተሻለ ጥንካሬን አሳይቷል። በዚህ መሰረት ካደረጋቸው 5 ጨዋታዎች በአንዱ ብቻ በመሸነፍ በሌሎቹ አቻ ወጥቶ አራት ነጥቦችን ማሳካት ችሏል። ይህ ውጤት ከተሰበስበብው ነጥብ አንፃር ሲታይ ዝቅተኛ ቢመስልም ከቡድኑ ካለፉት አመታት ውጤት እና ከሜዳ ውጪ ከሚደረጉ ጨዋታዎች ጥንካሬ አንፃር ሲታይ እንደ አንድ በጎ ጎን እንዲወሰድ ግድ ይላል። ሌላው የመሀል ሜዳው ጥንካሬ ነው። ቡድኑ በብዛት ባደረጋቸው ጨዋታዎች ላይ የመሀል ሜዳውን የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ሲይዝ ይታያል። የመሀል ሜዳን የበላይነት መጎናፀፍ ሁልጊዜ ለድል ባይበቃም ስኬታማ የማጥቃት ዕቅድን ለመፍጠር ግን እንደ አንድ ትልቅ ግብዐት የሚታይ ነው። ኢትዮ ኤሌክትሪክ በሁለት አጥቂዎች ባደረጋቸው ጨዋታዎች ላይም ሁለቱ አጥቂዎች ያሳዩት ጥምረት ሌላኛው ጠንካራ ጎኑ ነው። የኢብራሂም ፍፋኖ የአማካይ መስመሩን ከአጥቂው መስመር ጋር ለማገናኘት የሚጥርበት መንገድ ቡድኑ በሶስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ለሚኖረው የማጥቃት አጨዋወት የተሻለ እገዛን የሚሰጥ ነው። ቡድኑ ካገባቸው ጎሎች 63 % የሚሆኑትን ግቦች ያስቆጠረው የአጥቂው ፍፁም ገ/ማርያም የአጨራረስ ብቃት እስካሁን ሰባት ጎል የሆኑ ኳሶችን ካቀበለው ዳዊት እስጢፋኖስ ጋር የፈጠረውም ጥምረት የኢትዮ ኤሌክትሪክ ዋነኛ ጥንካሬዎች መሀል አንዱ ነው። አጠቃላይ ቡድኑ ያለው የተጨዋቾች ስብስብም ቢሆን ከጉዳት እና ቅጣት ነፃ መሆን ከቻለ ከሌሎቹ ክለቦች ጋር ሲነፃፀር ጠንካራ ሊባል የሚችል ነው ።


ደካማ ጎን

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ውጤት የማስጠበቅ ከፍተኛ ችግር የታየበት ቡድን ነው። ቀድሞ ግብ ባስቆጠረባቸው ጨዋታዎች ላይ ግብ እያስተናገደ የተሸነፈባቸው እንዲሁም ነጥብ የጠላባቸው አጋጣሚዎች ይበረክታሉ። የዚህ ችግር ዋናኛ ምክንያት የክለቡ ያለፉት አመታት የወራጅ ቀጠና ታሪክን ተከትሎ የመጣው የተሸናፊነት ስነልቦና እንደሆነ በአሰልጣኙ እና በየጨዋቾች ዘንድ ሲገለፅ ይሰማል። በአንደኛው ዙርም ይህ ድክመት ኢትዮ ኤሌክትሪክን በርካታ ነጥቦች ሲያሳጣው ታይቷል። ምንም እንኳን ቡድኑ በመከላከሉ በኩል ያን ያህል ስኬታማ ነው ሊባል ባይችልም የመስመር ተከላካዮች የማጥቃት ተሳትፎ ግን የተዳከመ ሆኖ ታይቷል። ይህ የቡድኑ ችግር ምን አልባትም የአማካይ መስመሩ እና የመስመር አጥቂዎች የመከላከል ሀላፊነት ዝቀተኛ ከመሆኑ ጋር የተያያዘም ሊሆን ይችላል። በተለያየ ጊዜ የሚታየው የተጨዋቾች የተናጠል ብቃት መዋዠቅም ቡድኑ የተጋጣሚን ደካማ ጎን በመጠቀም ላይ ያተኮረ በመስመር ተከላካዮች በመስመር አጥቂዎች እና በመሀል አማካዮች የተናበበ እንቅስቃሴ ለማድረግ እንዳይችል አድርጎታል። ይህ ያልተናበበ አጨዋወትም ቡድኑ የሚኖረው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወደሶስተኛው የሜዳ ክፍል ድረስ ዘልቆ የሚገባ እንዳይሆን እና የመጨረሻ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር እንዳያግዝ አድርጎታል። የፊት መስመሩም ቢሆን በየጨዋታው ብዙ የሚባሉ እድሎችን ያገኛል ባይባልም የሚገኙትንም የግብ እድሎች ወደግብ በመቀየሩ በኩል ብዙ መሻሻል ይጠበቅበታል።


በሁለተኛው ዙር ምን ይጠበቃል?

ኢትዮ ኤሌክትሪክ አብዱል ፈታ ሰይዱ የተባለ ጋናዊ የመሀል ተከላካይ አስፈርሟል። ቡድኑ በመሀል ተከላካይ ቦታ ላይ ካለበት ችግር አንፃር ግዢው በቀሩት ጨዋታዎች ላይ ተመሳሳይ የመሀል ተከላካይ ጥምረት እንዲኖረው የሚረዳው ሊሆን ይችላል። ክለቡ ካለው የተጨዋቾች ስብስብ አንፃር በተለይ በስነልቦናው በኩል ያለበትን ችግር ከቀረፈ እና አዲሱ ፈራሚም እንደሚታሰበው ለኋላ ክፍሉ ጥንካሬን ከጨመረለት በሁለተኛው ዙር በሰንጠረዡ ወደላይ ከፍ የማለት ዕድልን ለማግኘት ሚከብደው አይሆንም። የአማካይ ክፍሉ የማጥቃት እና የመከላከል ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ እና የፊት አጥቂዎቹ የአጨራረስ ብቃት መሻሻል ማሳየት የሚችል ከሆነም ኢትዮ ኤሌክትሪክ ባለፉት አመታት ካስመዘገባቸው ውጤቶች የተሻለ ውጤት የማስመዝገብ ከፍተኛ ተስፋ አለው። ኤሌክትሪክ በሁለተኛው ዙር አመዛኙን ጨዋታ በአአ ስታድየም የሚያደርግ መሆኑ በርካታ ነጥብ እንዲሰበስብ ሊረዳው ይችላል፡፡

የቡድኑ የመጀመሪያ ዙር ኮከብ ተጨዋች – ዳዊት እስጢፋኖስ

ተጨዋቹ በሀገራችን ከሚገኙ ጥቂት የላቀ የቴክኒክ ብቃት ካላቸው አማካዮች መካከል አንዱ እና ዋነኛው ነው። በዘንድሮው የኢትዮ ኤሌክትሪክ የመጀመሪያ ዙር ጉዞም ለቡድኑ የመሀል ክፍል ዋነኛ የፈጠራ ምንጭ ሆኖ አገልግሏል። በ13 ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ በርካታ ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን ለአጥቂዎቹ ማድረስ ችሎ ሰባቱ ወደግብነት ተቀይረዋል። በተለይም ከፊት አጥቂው ፍፁም ገ/ማሪያም ጋር ያለው ጥምረት ለቡድኑ የሁለተኛ ዙር ጉዞ ስኬታማነት ተስፋን የሚያጭር ነው።

ተስፋ የሚጣልበት ተጫዋች – አቤል አክሊሉ

ኤሌክትሪክ በርካታ ተጫዋቾችናን ከታዳጊ እና ተስፋ ቡድኑ ቢያሳድግም በተሻለ ሁኔታ ወደ ሜዳ መግባት የቻለው አቤል አክሊሉ ብቻ ነው፡፡ አቤል የሚሰጠው የጨዋታ ጊዜ በቂ ባይሆንም በሁለተኛው ዙር እድል ካገኘ አቅሙን ማሳየት ይችላል፡፡

Leave a Reply