ሳላዲን ሰኢድ ቅዱስ ጊዮርጊስ በቻምፒየንስ ሊጉ ረጅም ርቀት እንደሚጓዝ ያምናል

ሳላዲን ሰኢድ ወደ ቀድሞ አቋሙ እየተመለሰ መሆኑን በቅርብ ሳምንታት እያሳየን ይገኛል፡፡ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎችም 4 ጎሎች ማስቆጠር ችሏል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ሲሸልስ ተጉዞ ኮት ዲ ኦርን 2-0 ሲረታ የማሸነፍያ ግቦችን ያስቆጠረው ሳላዲን ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረገው ቆይታ ከሲሸልስ የሚፈልጉትን ይዘው እንደተመለሱ ተናግሯል፡፡

” ጨዋታው በጣም ጥሩ ነበር፡፡ ወደ ሲሸልስ ያቀናነው የማለፍ እድላችንን አስፍተን ለመመለስ ነበር፡፡ ፈጣሪ ብሎልን የምንፈልገውን ውጤት በጥንቃቄ ተጫውተን አሳክተን ተመልሰናል፡፡ ” ይላል፡፡ አክሎም ግቦች በማስቆጠሩ ደስተኛ መሆኑን ይገልጻል፡፡

” እግር ኳስ ጨዋታ የቡድን ስራ ነው፡፡ ሁሌም ቅድሚያ የምትሰጠው ቡድንህ ውጤታማ እንዲሆንና እንዲያሸንፍ ነው። በግልህ ደግሞ በማሸነፍ ውስጥ ጎል ማስቆጠርን ሁሉም ተጨዋች ያስባል፡፡ ቡድኔ በኔ ሁለት ጎል በማሸነፉ ደስተኛ ነኝ፡፡ ”

ቅዱስ ጊዮርጊስ በድል መመለሱን ተከትሎ ሀዋሳ ላይ የሚደረገው ጨዋታ ለፈረሰኞቹ ብዙም ከባድ የሚሆን አይመስልም፡፡ ነገር ግን ሳላዲን ለተጋጣሚያቸው ክብረ እንደሚሰጡ ይናገራል፡፡

” እኛ ምንጊዜም የክለባችንን ትልቅነት ጠብቀን ነው መሄድ የምንፈልገው፡፡ ያንን ለማድረግ ደግሞ ጨዋታዎችን መምረጥ የለብንም ፤ ለመልሱ ጨዋታም አሸንፈን መተናል ብለን አቅልለን የምንመለከትበት መንገድ የለም፡፡ የሚገባቸውን ክብር ሰጥተን ነው ወደ ሜዳ የምንገባው፡፡ ጨዋታውን ማሸነፍ በሊጉም ሆነ በኢንርናሽናል መድረክ  ላለብን ጉዞ ትልቅ መነሻሻ ስለሚሆን ጨዋታውን አቅልለን አንመለከትም። ” ሲል ለጨዋታው ቀላል ግምት እንደማይሰጡ ይገልጻል፡፡

ባለፉት አመታት እንደታየው የቅዱስ ጊዮርጊስ የአፍሪካ ውድድር ፈተና የሚጀምረው በአንደኛው ዙር ነው፡፡ ፈረሰኞቹ የሲሸልሱ ተጋጣሚያቸውን ከረቱ በቀጣይ የካሜሩኑ ቻምፒዮን ኤምኤስ ዴሉም  እና የኮንጎ ብራዛቪሉ ኤሲ ሊዮፓርድስን አሸናፊ ይገጥማሉ፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በሀገር ወስጥ እያሳየ ካለው ወጥ ያልሆነ አቋም አንጻር የአንደኛ ዙር ጨዋታው ፈታኝ እንደሚሆን ቢገመትም ሳላ ቡድናቸው ረጅም ርቀት የመጓዝ አቅም እንዳላቸው ያምናል፡፡

” ለእኔ ጊዮርጊስ በአፍሪካ መድረክ  ያለው ጥንካሬ አስገራሚ ነው፡፡ አንዳንዴ በሀገር ውስጥ ውድድሮች የአቋም መዋዠቅ  ይታይብናል፡፡ ይህ እንዲሆን ያደረገው የተለያዩ ምክንያቶች የነበሩ ቢሆንም በተለይ ጉዳቶች ቡድናችንን በተወሰነ መልኩ ረብሾታል፡፡ ያም ቢሆን አሁን ጥሩ ነገር አለ፡፡ እንደሚታወቀው የሀገር ውስጥና የውጭ ውድድር በጣም ልዩነት አለው ፤ የውጭ ጨዋታ ታክቲክ ላይ የተመሰረተ ነው ጊዮርጊስ ደግሞ በእንደዚህ  ያለ አጨዋወት የሚመጣ ቡድን ይቀለዋል፡፡ የመጫወቻ ስፔስ ታገኛለህ፡፡ ኢትዮዽያ ውስጥ እንደዚህ ያለ ነገር የለም ፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአፍሪካ መድረክ ረጅም ርቀት ለመጓዝ አቅም አለው፡፡ ጥሩ ውጤት እንደምናመጣም እናስባለን፡፡

በቅርብ አመታት በርካታ ጉዳቶች ያስተናገደው ሳላዲን ሰኢድ በቀድሞ አስፈሪ አቋሙ ላይ ለመገኘት ተቸግሯል፡፡ ሳላዲን ግን በዚህ አይስማማም፡፡ ጥሩ አቋም ግብ ከማስቆጠር ጋር ብቻ መያያዝ እንደሌለበት ያምናል፡፡

” እኛ ሀገር ላይ ብዙ ጊዜ ጎል ካላገባህ ከአቅም መውረድ እና ጥሩ ብቃት ላይ ካለመገኘት ጋር ይያያዛል። ሆኖም ብዙ ጨዋታዎች ላይ ጥሩ ተንቀሳቅሻለው፡፡ በርካታ የሚሆኑ የጎል የማግባት አጋጣሚዎችን ፈጥሬያለው ፤ አንዳንዴ ኳስ ባህሪው በጣም ይገርማል፡፡ የማልጠብቃቸው ክስተቶች ተፈጥረዋል ፤ በዚህም ትንሽ ግራ መጋባት ውስጥ ገብቼ ነበር፡፡ በርካታ ያገኘሁትን አጋጣሚ ወደ ጎልነት ብቀይር ኖሮ ሰዎች ወደዚህ ሀሳብ አይገቡም ነበር፡፡ ያው የእግር ኳስ አንዱ አካል በመሆኑ ትቀበለዋለህ።

“እኔ ምንግዜም በስራዬ ጠንካራ ሆኜ መገኘት ነው የምፈልገው፡፡ ልነግርህ የምፈልገው ነገር ከምንጊዜውም በላይ ጊዮርጊስ ውስጥ ተጨማሪ ልምምዶችን እየሰራው ራሴን ብቁ ለማድረግ እና እራሴን ትልቅ ቦታ ለማስቀመጥ ጠንክሬ እየሰራው ነው ፤ ማች ፊትነሴም ጥሩ ነው። አንዳንዴ ጉዳቶች ትንሽ ስራዬን አስቸጋሪ ቢያደርገውም ከዚህ የበለጠ ለክለቤ ጥሩ አገልግሎት መስጠት ነው የምፈልገው፡፡ ለብሔራዊ ቡድንም እንደዛው፡፡ በኔ በኩል ፊት ሆኖ በመገኘት ጎል ለማስቆጠር አቅሜን ለማሳደግ ከፈጣሪ ጋር እሰራለው። ”


1 Comment

Leave a Reply