” ለስኬት ከፍተኛ የሆነ ተነሳሽነት በውስጣችን አለ” አስቻለው ግርማ

በሀዋሳ ከተማ የአንድ የውድድር ዘመን ቆይታ አድርጎ ወደ ኢትዮጵያ ቡና የተመለሰው አስቻለው ግርማ በውድድር ዘመኑ መጀመርያ እንደ ኢትዮጵያ ቡና ሁሉ የተጠበቀውን ያህል መንቀሳቀስ ባይችልም ቀስ በቀስ ወደ ድንቅ አቋሙ ተመልሶ ኢትዮጵያ ቡና ደረጃውን እንዲያሻሽለል ረድቷል፡፡ በሶከር ኢትዮጵያ የሊጉ የጥር ወር ኮከብ ተብሎም ተመርጧል፡፡ አስቻለው ከዳንኤል መስፍን ጋር ስለ ወቅታዊ አቋሙ እና ሁለተኛው ዙር ያደረገውን ቆይታ እነሆ ብለናል፡፡

ህይወት በኢትዮጵያ ቡና ቤት እንዴት ነው?

ህብረታችን እና የቡድን መንፈሳችን በጣም ጥሩ ነው። ኢትዮዽያ ቡና ጠንካራ ቡድን ነው፡፡ ጥሩ የተጨዋች ስብስብ ያለውና  ለዋንጫ መጫወት የሚችል ትልቅ ቡድን ነው። በአጠቃላይ በኢትዮዽያ ቡና ቤት ደስ የሚል ጊዜ እያሳለፍኩ እገኛለው።

በመጀመርያዎቹ ሳምንታት ኢትዮጵያ ቡና ያስመዘገበው ውጤት ጥሩ አልነበረም፡፡  እንደ ተጫዋች የዚህ ውጤት መጥፋት ምክንያቱ ምድነው ትላለህ?

ቡድናችን እንዳለው የተጨዋች ጥራት ፣ ስብስብ ፣ በዝግጅት ወቅት የነበረን ስራ ፣ ሀዋሳ ላይ ተዘጋጅቶ በነበረው በደቡብ ካስትል ካፕ ላይ እንዳሳየነው ጥሩ እንቅስቃሴ እና ውጤት አንፃር ቡድናችን በፕሪምየር ሊጉ ጥሩ ውጤት እንደምናስመዘግብ ጠብቀን ነበር፡፡ በእግር ኳስ አንዳንዴ ያልጠበቅከው ነገር ይከሰታል ፤ ጥሩ ተጫውተህም ትሸነፋለህ፡፡ ለማሸነፍ ከነበረን ከፍተኛ ፍላጎት የተነሳ ጎል የማስቆጠር ችግሮች ነበሩብን፡፡ እነዚህ እና ሌሎች ምክንያቶች ተጨምሮበት አጀማመራችን ጥሩ አልሆነም፡፡ የመጀመርያ ጨዋታ ላይ በሰፋ ጎል መሸነፋችን ተፅዕኖ አድርጎብን ቶሎ ወደ ጨዋታ ለመመለስ ጊዜ ወስዶብናል እንጂ ቡድናችን ወደተሻለ ነገር እንደሚመጣ እርግጠኛ ነበረኩ ።

ኢትዮዽያ ቡና ከጥር ወር መጀመርያ አንስቶ ከፍተኛ የሆነ ማሻሻል በማሳየት በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ጋር ካሉ ቡድኖች ጋር ያለውን ልዩነት አጥብቧል፡፡ ያሳያችሁትን መሻሻል እንዴት ትገልፀዋለህ?

አሁን ላይ ቡድኑ ያለበት ሁኔታ ጥሩ ነው፡፡ በተከታታይ ጨዋታዎች አልተሸነፍንም፡፡ ይህን ማድረግ ከባድ ነው። ከሜዳ ውጭም እያሸነፍን ነጥብ እየተጋራን እየመጣን እንገኛለን ፤ ይህ ደግሞ በኢትዮዽያ ቡና አልተለመደም፡፡ ብዙ ጊዜ ከሜዳ ውጭ ለማሸነፍ እና ነጥብ ለመጋራት የሚቸገር ቡድን ነበር፡፡ አሁን ከሜዳ ውጭ ነጥብ ይዘን እየተመለስን መሆኑ ጥሩ ነው፡፡ ይህም የሆነው ደግሞ ያለን ህብረት ቡድናችን ውጤታማ እንዲሆንና ምን ማድረግ እንዳለብን መነጋገራችን አሁን ላለንበት ጥሩ ጉዞ ረድቶናል።

ለቡድኑ መሻሻል የአንተ በድንቅ አቋም ላይ መገኘት ትልቅ አስተዋፆ ነበረው…

ሁልጊዜ በርትተህ ከሰራህና ከለፋህ የስራህን ታገኛህ ፤ ካልሰራህ ሜዳ ውስጥ የምታሳየው ነገር አይኖርም። እውነት ለመናገር እኔ በግሌ ከቡድን አጋሮቼ ጋር በመሆን  ከምሰራው ልምምድ  በተጨማሪ  በግሌ ተጨማሪ የሆኑ ልምምዶችን  እሰራለው፡፡ ያ ለኔ የተሻለ ነገር ሜዳ ውስጥ እንዳሳይ አግዞኛል፡፡ ከጨዋታ ጨዋታ እያሸነፍን መምጣታችን ደግሞ በራስ መተማመናችንን በከፍተኛ ሁኔታ አሳድጎታል፡፡ በቀጣይም የተሻለ ነገር ለመስራት ከቡድን አጋሮቼ ጋር በመሆን ጥሩ ነገር ለማድረግ እጥራለው።

የደጋፊውን እገዛስ እንዴት ትገልፀዋለህ ?

እንድያውም ምንም ውጤት አላመጣንም ማለት ነው የሚቻለው። እንዳለን ስብስብ ያስመዘገብነው ውጤት ለኢትዮዽያ ቡና ደጋፊ አይገባውም፡፡ ከዚህ በላይ መሪ ሆነን መገኘት ነበረብን፡፡ እንደሚታወቀው  ቡና በኢትዮዽያ ክለቦች ታሪክ ቁጥር አንድ ደጋፊ ያለው ክለብ ነው። ውጤት ባላመጣንበት ወቅት እንኳን ከጎናችን አብረውን ነበሩ፡፡ እነሱ ማለት ለእኛ ጉልበታችንና ብርታታችን ናቸው፡፡ አሁን ያለውን ውጤት አስቀጥለን ለደጋፊው የሚገባውን ነገር ማድረግና ማስደሰት እንፈልጋለን ።

በሁለተኛው ዙር ከአንተ እና ከኢትዮዽያ ቡና ምን እንጠብቅ?

በሁለተኛው ዙር ነገሮች ቀላል አይሆኑም፡፡ ለዋንጫ የሚፎካከሩ ቡድኖች ይኖራሉ ፤ ላለመውረድ ደግሞ የሚታገሉ ቡድኖች ስለሚኖሩ ፉክክሩ ቀላል እንደማይሆን አስባለው። ስለ ነገ መናገር ቢከብድም እኔ በግሌም እንደ ቡድን በምንችለው አቅም የተሻለ ውጤት ለማግኘት በሚገባ እየተዘጋጀን እንገኛለን፡፡ ዘንድሮ ለደረጃ ሳይሆን ለዋንጫ ነው የምንጫወተው ይህን ማድረግ እንዳለብን ተነጋግረናል፡፡ ለስኬት ከፍተኛ የሆነ ተነሳሽነት በውስጣችን አለ፡፡ ይህን ለማሳካት ከደጋፊዎቻችን ጋር መሆን ሁላችንም በአንድነት  የምንጥር ይሆናል፡፡

Leave a Reply