የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 1ኛ ዙር የክለቦች ዳሰሳ – አዲስ አበባ ከተማ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመርያ ዙር መጠናቀቅን አስመልክቶ ሶከር ኢትዮጵያ የክለቦቹን ግማሽ የውድድር ዘመን ዳሰሳ በተከታታይ በማቅረብ ላይ ትገኛለች፡፡ አብርሃም ገብረማርያም እና ሚልኪያስ አበራ በዚህ ፅሁፍ አንደኛውን ዙር በመጨረሻ ደረጃ ላይ ሆኖ ያጠናቀቀው አዲስ አበባ ከተማን እንዲህ ባለ መልኩ ዳሰውታል፡፡

የውድድር ዘመኑ ጉዞ

አዲስ አበባ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለመጀመርያ ጊዜ በመሳተፍ ላይ ይገኛል፡፡ የዋና ከተማው ክለብ በታሪክ የመጀመርያውን ድል እና ጎል በፍጥነት ነበር ያገኘው፡፡ በ1ኛው ሳምነንት ወደ ሀዋሳ አቅንቶ ሀዋሳ ከተማን በመርታት፡፡ አአ ከተማ በቀጣይ ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች የአቻ ውጤት ማስመዝገቡን ተከትሎ መልካም የውድድር ዘመን ጅማሮ ቢያደርግም ከዛ ወዲህ ነገሮች ለአዲስ አበባ አልጋ በአልጋ መሆን አልቻሉም፡፡ 8 ተከታታይ ጨዋታዎችን ተሸንፎ የደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌን ለመያዝ ተገዷል፡፡ በጥር ወር ደግሞ መሻሻል አሳይቶ ወላይታ ድቻን ከሜዳው ውጪ በመርታት ፣ ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ወልድያ ጋር  አቻ በመለያየት ቢያንስ ከሰንጠረዡ ወገብ ካሉ ቡድኖች ጋር ያለውን ልዩነት አጥብቦ በደረጃ ሰንጠረዡ መጨረሻ ደረጃ ላይ ተቀምጦ አንደኛውን ዙር አጠናቋል፡፡

የቡድኑ ውጤት ከአምናው ጋር ሲነጻጸር

አአ ከተማ አምና የነበረው ከፍተኛ ሊግ እንደመሆኑ የአምና እና የዘንድሮውን የቡድኑ አቋም ማነጻጸር አስቸጋሪ ነው፡፡ በከፍተኛ ሊጉ ተጋጣሚዎቹን በቀላሉ የሚረታው አዲስ አበባ ከተማ በፕሪምየር ሊጉ ይህንን ለመድገም መቸገሩ አስገራሚ አይሆንም፡፡

የቡድኑ የጨዋታ አቀራረብ

አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ሁሉም ጨዋታዎች ላይ ለማለት በሚያስችል ሁኔታ በግልጽ 4-1-3-2 የሜዳ ላይ አደራደር ተጠቅመዋል፡፡ የአሰልጣኝ ስዩም የጨዋታ አቀራረብ በግልፅ ሜዳ ላይ የሚታይና ለትንተና የማያስቸግር ነው፡፡ ከብቸኛው የተከላካይ አማካይ ፊት የሚገኙት 3 አማካዮች ወደ መሃል አጥብበው መጫወታቸውና ከኳስ ጋር ምቾች የሚሰማቸው ተጫዋቾችን መያዙ በየትኛውም ቡድን ላይ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት እንዲይዙ አድርጓቸዋል፡፡

ሁለቱ አጥቂዎች (በተለይ ኃይሌ) ከኳስ ውጪ ወደ መስመሮች በመውጣት ተጋጣሚ ማጥቃት ከኋላ እንዳይጀምር ሲጥሩ ይታያል፡፡ አማካይ መስመሩ ወደ መሀል አጥብቦ እንደመጫወቱ የመስመር ተከላካዮቹ በማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ የሚሳተፉበትን የመቀባበያ ማዕዘናት እና ነጻነት አስገኝቶላቸዋል፡፡

በቡድኑ የጨዋታ አቀራረብ ላይ ከሚታዩት ችግሮ መካከል ቡድኑ በአንድ የተከላካይ አማካይ የሚጫወት ከመሆኑ በተጨማሪ ሶስቱ አማካዮች በማጥቃት ላይ አመዝነው መጫወታቸው የተከላካይ አማካዩን ስራ ሲያበዛው ይስተዋላል፡፡ በበርካታ ጨዋታዎች ላይ የተሰለፈው ዘሪሁን ብርሃኑ ለተከላካዮች ቀርቦ የሚጫወት በመሆኑ ቡድኑ ሁለት ቦታ የተቆረጠ መልክ እንዲይዝ አድርጎታል፡፡ ይህም ቡድኑ ከመከላከል ወደ ማጥቃት የሚያደርገው ሽግግር አዝጋሚ እንዲሆን አስገድዶታል፡፡

ጠንካራ ጎን

የአዲስ አበባ ከተማ ጠንካራ ጎን በተጋጣሚዎቹ ላይ የሚወስደው የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ነው፡፡ ቡድኑ በአብዛኛው ኳስ የሚቀባበልባቸው ስፍራዎች አደጋ ለመፍጠር አመቺ ያልሆኑ ቦታዎች ላይ ቢሆንም በእንቅስቃሴ እንዳይበለጥ እና በተከላካዮች ላይ ጫና እንዳይፈጠርበት አግዞታል፡፡ ቡድኑ መጨረሻ ደረጃ ላይ ቢገኝም ከፍተኛ የግብ መጠን ያልተቆጠረበት ኳስ በቡድኑ ተጫዋቾች እግር ስር ለረጅም ደቂቃዎች በመቆየቱ ነው፡፡

አዲስ አበባ ወደ ክልል ተጉዞ ያስመዘገበው ውጤት (6 ነጥብ) አአ ላይ ካመዘገበው (4 ነጥብ) የበለጠ ነው፡፡ ስለዚህም የቡድኑ ዋንኛ ጠንካራ ጎኑ ከሜዳው ውጪ ውጤት የማስመዝገብ አቅሙ ነው፡፡ 

በርካታ በቴክኒክ የበለጸጉ ተጫዋቾችን መያዙ የቡድኑ ሌላው ጠንካራ ጎን ነው፡፡ በተለይም በአማካይ ክፍሉ የሚገኙት ተጫዋቾች ክህሎት እና የፕሪምየር ሊግ ልምድ ከጨዋታ ጨዋታ መጎልበት ቡድኑን በሁለተኛው ዙር ተጠቃሚ ሊያደርገው ይችላል፡፡

አሰልጣኝ ስዩም ከበደ በሚያምኑበት አጨዋወት መቀጠላቸው እና በተደጋጋሚ ሽንፈቶች ምክንያት አጨዋወታቸውን አለመቀየራቸው ወደ መጨረሻዎቹ ጨዋታዎች ላይ ቡድኑ መልካም እንቅስቃሴ እንዲያደርግ ረድቶታል፡፡ ተጫዋቾቹ ሊጉን እየተላመዱ በመምጣታቸውም በሁለተኛው ዙር የተሻለ ውጤት ሊያመጡ ይችላሉ፡፡

ደካማ ጎን

የቡድኑ ዋንኛ ደካማ ጎን የተጫዋቾች ጥራት ነው፡፡ ተጫዋቾቹ ክህሎታቸው እና እምቅ አቅማቸው መልካም ቢሆንም ልምድ የቦታ አያያዝ ፣ ግምት ፣ ውሳኔ አሰጣጥ እንዲሁም የአእምሮ ጥንካሬያቸው ከሌሎች ክለቦች አንጻር ዝቅተኛ ነው፡፡ የቡድኑ አመዛኝ ስብስብ የፕሪምየር ሊግ ልምድ የሌለው መሆኑ አአ ከተማ በሊጉ ላይ እንዲቸገር አድርጎታል፡፡ የግብ እድል ለመፍጠር የሚቸገሩ ሲሆን በቀላሉ ግብ ያስተናግዳሉ፡፡

የእንቅስቃሴ ተገማችነት የቡድኑ ሌላው ደካማ ጎን ነው፡፡ ቡድኑ ኳስን በዝግታ በመቀባበል ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ የሚያደርገው ጥረት ለተጋጣሚ ቡድኖች ሰፊ የማሰቢያ እና ክፍተት የመድፈኛ ጊዜ የሚሰጥ ነው፡፡ 2ኛ የጨዋታ እቅድ የሌለው መሆኑ ቡድኑ ክፍተት ሲያጣ እንዲቸገር አድርጎታል፡፡

በጉዳት አስገዳጅነት ቋሚ ቡድን አለመኖሩ አስተዋጽኦ ቢያደርግም የተጫዋቾቹ ውህደት ደካማ ነው፡፡ በተከላካይ መስመር የሚገኙት ተጣማሪዎች አለመግባባት እና የአጥቂዎቹ ከአማካዮች ያላቸው የመናበብ ድክመት በግልጽ የሚታይ ነው፡፡ አጥቂዎቹ በቡድኑ እንቅስቃሴ ተስበው ከተቃራኒ የግብ ክልል በተደጋጋሚ ሲርቁና ኳስ የሚቀበሉበት ቦታ አደጋ ለመፍጠር የማያመች ሲሆን በተደጋጋሚ ይስተዋላል፡፡

አዲስ አበባ ከተማ ከሜዳ ውጪ ያለው አስተዳደራዊ ችግር በሜዳ ላይ ደካማ እንዲሆን ያደረገው ይመስላል፡፡ ከውድድር አመቱ መጀመር አንስቶ የደሞዝ ክፍያ ፣ የቁሳቁስ አለመሟላት ፣ ቃል የተገባ የሽልማት ገንዘብ አለመሰጠት ፣ የልምምድ ሜዳ የመቀየር ጥያቄ ፣ የዲሲፕሊን ጉዳዮች ፣ ከተጫዋች ጋር ውዝግብ ውስጥ የመግባት ፣ በሴቶች ቡድን ላይ የነበረው ውዝግብ እና የመሳሰሉት ተደማምረው ቡድኑ ህልውናውን የተፈታተነ የውድድር ዘመን እንዲያሳልፍ ተገዷል፡፡

በሁለተኛው ዙር ምን እንጠብቅ?

አዲስ አበባ ከተማ በ1ኛው ዙር የመጨረሻዎቹ ጥቂት ጨዋታዎች ባሳየው መሻሻል የሚቀጥል ከሆነ በሁለተኛው የውድድር ዘመን አጋማሽ የተሻለ ቡድን ልንመለከት እንችላለን፡፡ ከውጪ ሃገራት የፈረሙት አራት አዳዲስ ተጫዋቾች ከጉዳት ከሚመለሱ ተጫዋቾች ጋር ሲደመር አአ ከተማ በሁለተኛው ዙር ላይ ተስፋ እንዲጥል ሊያደርገው ይችላል፡፡ አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ከወራት በፊት ጀምረው ከጨዋታ በኋላ ከሚሰጧቸው አስተያየቶች የምንረዳው ቡድኑ ለ2ኛው ዙር ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን ነው፡፡

አሰልጣኝ ስዩም ከምዕራብ አፍሪካ ያመጧቸው ተጫዋቾች ለቡድኑ አማራጭ እቅድ ሊሰጡት ይችላሉ፡፡

የ1ኛ ዙር የቡድኑ ኮከብ ተጫዋች – ኃይሌ እሸቱ

ኃይሌ ከቡድን አጋሮቹ በተሻለ ወጥ አቋም ማሳየት ችሏል፡፡ በተለይም በጥር ወር ቡድኑ የተሻለ ጉዞ እንዲያደርግ የኃይሌ ሚና ከፍተኛ ነበር፡፡ የተጋጣሚ ተከላካዮች ላይ ጫና የሚያሳድር ፣ ከተጣማሪው ጋር የሚግባባ እና ታታሪ ነው፡፡ የግብ እድሎች በሚፈጠሩበት ወቅት ያለውን የቦታ አጠባበቅ ካሻሻለ በሁለተኛው ዙር ለቡድኑ በርካታ ግቦች ማበርከትም ይችላል፡፡

ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ያሳየ ተጫዋች – ጊት ጋት

ጊት የአዲስ አበባ ከተማ የተከላካይ ክፍል በጉዳት መሳሳቱን ተከትሎ ያገኘውን የመሰለፍ እድል በአግባቡ እየተጠቀመበት ይገኛል፡፡ ቁመተ መለሎው ወጣት ኢላማቸውን የጠበቁ ሸርተቴዎቹ እና አንድ ለአንድ ግንኙነቶች ላይ ያለው ጥንካሬ ድንቅ ነው፡፡ በሁለተኛው ዙር ቦታውን ለማስጠበቅ ከፍተኛ ፉክክር ቢገጥመውም በቀጣዮቹ ጊዜያት በሊጉ ከሚገኙ ምርጥ ተከላካዮች አንዱ የመሆን አቅም አለው፡፡

Leave a Reply