የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዙር ግምገማ በሶዶ ተካሂዷል

የ2009 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሪፖርት ዛሬ በሶዶ ከተማ አበበ ዘለቀ ሆቴል ተካሂዷል፡፡ በግምገማው የ13 ክለብ ተወካዮች ሲገኙ የመከላከያ ፣ ደደቢት እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተወካዮች ሳይገኙ ቀርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን ፕሬዝደንት አቶ ጁነይዲ ባሻ በተገኙበት ግምገማ የአንደኛው የውድድር አፈፃፀም ሪፖርት የቀረበ ሲሆን ሪፖርቱ የውድድር ዓመቱን አጋማሽ ጠንካራ እና ደካማ ጎን ያላቸውን ለይቶ አስቀምጧል፡፡ ክለቦች ስለአንደኛው ዙር እና መታረም አለባቸው ያሏቸውን ችግሮችም አንስተዋል፡፡ ሚዛናዊ ያልሆኑ የዳኝነት ውሳኔዎች እና የታዛቢዎች ሪፖርት ደግሞ ሰፊውን ሰአት የወሰደ ጉዳይ ነበር፡፡

በውይይቱ የስምንት ክለብ ተወካዮች አስተያየታቸውን ሲገልፁ የሊግ ኮሚቴ፣ ዲስፕሊን ኮሚቴ፣ የፀጥታ ኮሚቴ፣ የዳኞች ኮሚቴ እና ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ተወካዮች ሪፖርት እና ከክለቦች ለተነሱ ጥያቄዎች መልስ ሰጥተው የኢትዮጵያ ዋንጫ (ጥሎ ማለፍ) ውድድር የዕጣ ማውጣት ስነ-ስርዓት በግምገማው መጨረሻ ተካሂዷል፡፡

በክለቦች በኩል እና በሚመለከታቸው ኮሚቴዎች በኩል የተሰጡት አንኳር አንኳር አስተያየቶች ይህንን ይመስላሉ፡፡ (ማስታወሻ፡ ስምንት ክለቦች ብቻ አስተያየታቸው ገልፀዋል)

አቶ አሰፋ (ወላይታ ድቻ)

“ውድድሩ ላይ የጨዋታ መቆራረጥ ባይኖርም አራት ቡድኖች ላይ መቆራረጦች ነበሩ፡፡ በሁለተኛው ሳምንት ከፋሲል ጋር የነበረን ጨዋታ የአውሮፕላን ትኬት ቆርጠን ልንጓዝ ስንል ጨዋታው መተላለፉ ተነግሮናል፡፡ ፌድሬሽኑ ይህንን ወጪ ሊያካክስ ይገባል፡፡ ነጥቦች እና የጨዋታ ውጤት የሚያስለውጥ ውሳኔዎች ነበሩ፡፡ የዳኝነት ውሳኔ ከቡዙ ነገሮች ጋር የተያያዘ ነው፡፡ 6 ነጥብ  በዳኝነት ስህተት አጥተናል፡፡ በኮሚሽነሮች በኩል ሚዛን አድርጎ ሪፖርት አለማቅረብ ችግር አለ፡፡ የፀጥታ ጉዳይ አሁንም ሊነሳ ይገባል በዚህ ላይ ኢትዮጵያ ቡና ሊመሰገን ይገባዋል፡፡”

 አቶ ገዛኸኝ (አዲስ አበባ ከተማ) 
“ሊግ ኮሜቴው በዲፓርትመን የተከፈለ ቢሀን ጥሩ ነው፡፡ አብዛኛውን ጨዋታ በራሳችን ስህተት ነው የተሸነፍነው በዳኛ፣ ሜዳ፣ በፌድሬሽን አይደለም፡፡ ግን አንዳንድ የዳኝነት ውሳኔዎች ዋጋ አስከፍለውኗል፡፡ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ የሚያቀርበው እና የሚፅፈው ሪፖርት አራት ዓመት ሙሉ ተመሳሳይ ነው፡፡ የዲስፕሊን መመሪያው ላይ ራሱ ችግር አለ፡፡ ትንሽ የሚመስሉ ግን አደጋ ያላቸው መመሪያዎች አሉ፡፡ ፌድሬሽን የድስፕሊን መመሪያውን ክለቦች በደንብ እንዲያውቁት አላደረገም፡፡ በክልል የሚደረጉ ጨዋታዎች ላይ ደጋፊዎች በጣም አክራሪ የሚሆኑት ነገር አለ፡፡ ይህ ኳስ ጨዋታ ነው ማሸነፍ፣ መሸነፍ እና አቻ መውጣት እንዳለ ቢገነዘቡ በጣም መልካም ነው፡፡ የፀጥታ ኮሚቴው አዲስ አበባ ላይ ብቻ ታጥሯል፡፡”

አቶ ጠሃ (ሀዋሳ ከተማ)

“ሀዋሳ ከመከላከያ ከተጫወቱ በኃላ በተወሰነው ውሳኔ በጣም ነው ያዘንኩት፡፡ የክለብ ከክለብ ግንኙነት እንዲሻክሩ የሚያደርጉ ክለቦች አሉ፡፡ አንዳንዴ የምናደርጋቸው ነገሮች ለይምሰል ባይሆን ጥሩ ነው፡፡ 15 ቀን እረፍት አነስተኛ ነው ፤ ግዜው ቢራዘም ደስ ይለኛል፡፡ መጋቢት እንዲጀመር ምንአልባት የብሄራዊ ቡድን ጨዋታ ቢኖርም አራት ወር ሊጉን ለመጨረስ ይኖረናል፡፡”

ኢንጅነር ኢያሱ (አርባምንጭ ከተማ)

“ሪፖርቱ አዲስ አበባ ላይ ያለውን ያተኩራል፡፡ ይህ ነገር ወደ ክልልም መውጣት አለበት፡፡ አንዳንድ ዳኞች አንባገነን ለመሆን የሚፈልጉ አሉ፡፡ የውጪ ተጫዋች በጣም እየተበራከተ ነው፡፡ በዚሁ ከቀጠለ ለብሄራዊ ቡድናችን ግብ ጠባቂ ከውጪ ልናደርግ ነው?”

አቶ አንበሴ እና አቶ ግርማ (አዳማ ከተማ)

“የሊግ ፕሮግራም አወጣጡ ግልፅ አይደለም፡፡ ማነው ኮሚሽነሮችን የሚገመግመው? የነጥብ መቀራረብ ስላለ በሁለተኛው ዙር ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለብን፡፡

“ብቁ ያልሆኑ ዳኞች ችግር እየፈጠሩ ነው፡፡ ክለብን ለማዳከም የሚጥሩ አንዳንድ የተቃራኒ ክለብ አሰልጣኞች አሉ፡፡ ተጨዋች በማስኮብለል የተጫዋችን የእግርኳስ ህይወት የሚያሰናክሉ አሉ፡፡ ምርጥ ልጆች እኛው ጋር እያሉ የውጪ ተጫዋች እናበረታታለን፡፡ ይህ በጣም ሊሰማን ይገባል፡፡ በሃገራችን ልጆች እንጠቀም፡፡”

አቶ በላይ (ኢትዮጵያ ቡና)

“መረጃ እና ሪፖርት ልዩነት እንዳለው መታወቅ አለበት፡፡ ለአስተዳደራዊ ችግሮች እና የዳኝነት ችግሮች ቀልጣፋ እና ብቃት ያለው ውሳኔ ያለመስጠት ነገር ይታያል፡፡ የዳኞች አለመናበብ በጨዋታዎች ላይ በተደጋጋሚ ይታያል፡፡ በአካል ብቃት ደረጃ ዳኞቻችን የት ነው ያሉት፡፡ ርቀት ላይ ሁነው ውሳኔ ይወስናሉ፡፡ እኒህ ነገሮች ላይ መሰራት አለበት፡፡ የኮሚሽነር ጉዳይ በጣም አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል፡፡ በጨዋታ ወቅት በሞባይል ስልካቸው ጨዋታ የሚጫወቱ ኮሚሽነር አጋጥመውኛል፡፡ ይህ ነገር በጣም መፈተሸ አለበት፡፡ ለሚሰሩ ጉዳዮች ቁጥጥር እና ክትትል ቢደረግ፡፡”

አቶ መንግስቱ (ሲዳማ ቡና)

“በዳኝነት ዙሪያ አሁንም እየተጫጫህን ነው፡፡ በደጋፊው በኩል የምናየው ነገር አለ፡፡ ግልፅ የሆነ አሰራር ኖሮ የሁለተኛው ዙር መጀመር አለበት፡ ኮሚሽነሩ በአብዛኛው ዳኞችን በመሸፈን ላይ ይገኛል፡፡ አሁን ላይ የአንድ ነጥብ ዋጋ ከአንድ ሚሊየን ብር በላይ ነው፡፡ የኮሚሽነሮች ሪፖርት ቢሰጠን፡፡ የክልል ፖሊስ እና የፀጥታ አካላት የሚያቀናጅ መዋቅር ቢኖር ችግሮች ይፈታሉ፡፡ የዕረፍት ግዜን በተመለከተ ለልጆቹ በቂ የማገገሚያ ግዜ ቢሰጥ፡፡”

አቶ ታፈሰ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)

“ሪፖርቱ ላይ መስተካከል ያለበት የቁጥር ግድፈት አለ፡፡ ፕሮግራሙ ላይ (በተለይ እኛን እና መከላከያን ይመለከታል) የኢንተርናሽናል ጨዋታዎችን ከግምት አላስገባም፡፡ በእድሜ የገፉ ኮሚሽነሮችን አማካሪ ብታደርጉ ይሻላል ፤ ምክንያቱም ሪፖርቶች ላይ ግድፈት እየታየ ነው፡፡”

አቶ አለሙ (ኢትዮ-ኤሌክትሪክ)

“የዳኝነት ችግር በጣም አለ፡፡ ከባንክ ጋር ስንጫወት የተወነብንን መጥቀስ በቂ ነው፡፡ የጨዋታ ኮሚሽነሮች ጨዋታ ከመጫወት ባለፈ በጨዋታ ወቅት ከቤተሰብ ጋር ስልክ የሚወሩ አሉ፡፡ ይህ ችግር ሊስተካከል ይገባል፡፡ የዳኛ እና ሊግ ኮሚቴ ግንኘነት ምን እንደሆነ ቢገለፅ፡፡ የጨዋታ ኮሚሽነር በሊግ ኮሚቴ ነው የሚመራው የዳኞች በዳኞች ኮሚቴ ነው የሚመራው ግንኙነታቸው ምን ላይ ነው፡፡”

የተሰጡ ምላሾች

አቶ ወንድምኩን (የኢ.እ.ፌ የፅህፈት ቤት ሃላፊ)

“ለጥያቄዎች በወቅቱ ምላሽ ሰጥተናል ከአንድ ጥያቄ በቀር፡፡ ከዚህ በኃላ ክብደት ያላቸው ጨዋታዎችን በምስል ለማስቀረት እንሞክራለን፡፡ ኮምንኬ በተሻለ መንገድ በሁለተኛው ዙር ለክለቦች ለማቅረብ እንሞክራለን፡፡”

አቶ ትግል (የዳኞች እና ታዛቢዎች ማህበር ፕሬዝደንት)

“ክለቦች ልታግዙን ይገባል፡፡ ለክለቦቻችሁ የምታሳዩትን ተቆርቋሪነት ለእኛም አሳዩን፡፡ ዳኛው በነፃነት እንዲሰራ ተዉት፡፡ ክለቦች በዳኝነት ጉዳይ ላይ የምትፅፉት ደብዳቤ እና የምታቀርቡት የምስል ማስረጃ በጣም የተለያየ ነው፡፡ ዳኞቻችን ውጪ ሃገር ሲያጫውቱ ችግር አይገጥማቸውም  ምክንያቱም ከጫና ነፃ ስለሆኑ ነው፡፡ ታዛቢዎችን በተመለከተ ጥሩ ስራ እየተሰራ ነው በምዘናው በኩል፡፡ ጨዋታ ይጫወታሉ የታባሉት ታዛቢ ቢገለፁልን ጥሩ ነው፡፡ ይህ ነገር በጣም አሳፋሪ ነው፡፡ ከቤተሰብ ጋር በጨዋታ ወቅት ያወራሉ የሚል እሳቤ እንደማህበር የለንም፡፡ ቢጫ በዛ ለተባለው ቢጫ የሚያሠጡ 7 የጥፋት አይነቶች አሉ፡፡ በቃ ተጫዋች ቢጫ የሚያሰጥ ጥፋት ከሰራ ቢጫ ያያል ይህ የተለመደ ነው፡፡”

 አቶ ሸረፋ (የዳኞች ኮሚቴ)

“አንዳንድ የዳኝነት ችግሮችን ዳኞች ብቻ ሳይሆኑ ክለቦችም ተጠያቂ ናቸው፡፡ አዎ የኮሚሽነሮች ሚዛናዊ ያልሆኑ ሪፕርቶች ችግር ሲፈጥሩ አስተውለናል፡፡ ለእግርኳሱ የማይጠቅሙ ሪፖርቶች ይቀርባሉ፡፡ ይህንን እናስተካክላለን፡፡ ሁሌም ዳኛ ክለቦች ለመጉዳት ወሳኔ አይሰጥም፡፡ ሰው ናቸው እና ስህተቶች ይፈጠራሉ፡፡ አንዳንድ ግዜ ውጤት ሲታጣ ተጫዋቾች ወደ ያልሆነ እንቅስቃሴ ይገባሉ፡፡ ዳኛው ይህንን ነገር በብልጠት ማለፍ አለበት፡፡ ለዳኞች ነፃነት እና ጥበቃ ስጡ፡፡ ነፃነት የሚነፍግ አሰልጣኝ እና የቡድን መሪ አለ፡፡”

አቶ ሰለሞን (የውድድር ስፍራዎች ማዘውተሪያ ዳይሬክተር)

“ታዛቢዎች የሚወሰኑት በብቃት ነው፡፡ ስልጠና ያስፈልጋል፡፡ በስልጠና ሰጥተን ብቃት የሌላቸውን ወደ ክልል አልፎም ወደ ወረዳ ማውረድ አለብን፡፡ ሁሌም ክለቦች ለምትጠይቁት ጥያቄ ህጉን የተከተለ መሆን አለበት፡፡ ፕሬግራም ላይ ሁሌም ችግሮችን ከማንሳት ይልቅ የመፍትሄ ሃሳብ ካላችሁ አቅርቡ፡፡ የዲፓርትመን ክፍፍል በተመለከተ ክፍፍል አድርገን ስራዎች በመሰራት ላይ እንገኛለን፡፡”

አቶ አበበ (የብሄራዊ ውድድሮች ኮሚቴ ሰብሳቢ)

“የፋሲል እና ድቻ ጨዋታ ላይ ኮማንድ ፖስቱ ችግር አለ ለሌላ ግዜ እንድናስተላልፍ በድንገት ስላሳወቀን ጨዋታው ተላልፏል፡፡ ችግሩ የክለቦቹ ወይም የፌድሬሽኑ ችግር ሳይሆን ሃገራዊ በመሆኑ ሊራዘም ችሏል፡፡ የድቻን ያወጣውን ወጪ ፌድሬሽኑ ይሸፍናል፡፡ ጨዋታ የሚጫወቱ ኮሚሽነር አሉ ብለን አናስብም፡፡ አቅማቸው የደከመ ወይም የጤና መታወክ የገጠመው ኮሚሽነር የለም፡፡ አንደለም በሊጉ ላይ በሱፐር ሊጉ ላይ እንደዚህ ዓይነት ኮሚሽነር የተመደበበት ሁኔታ የለም፡፡”

አቶ ጁነይዲ (የኢ.እ.ፌ. ፕሬዝደንት)

“የሊግ ፕሮግራሙ ሲወጣ ፌድሬሽኑ ቶሎ ብሎ የውድድር ዓመቱን መጨረስ ይፈልጋል፡፡ ግን የሃራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ሊጣጣም አልቻለም፡፡ መጀመሪያ ጥቅምት መጀመሪያ ጀምረን ግንቦት ለማጠናቀቅ ነበር ሃሳባችን ፤ እንቅፋቶች በመፈጠራቸው ይህ እቅድ እውን ሊሆን አልቻለም፡፡ መልስ አልተመለሰም ሲባል ጥያቄው ልክ ስላልነበረ ነው፡፡ አገልግሎት ሰጪ ነን እና ፈጣን የሆነ መልስ ለመስጠት እየሞከርን ነው፡፡ እግርኳሱ እየደከመ ነው ለሚለው ምንድነው መስፈርቱ፡፡ ከ17 ዓመት፣ 20 ዓመታ ባታች፣ ሴቶች ሊግ እና ከፍተኛ ሊግ እየተፈጠረ ባለበት ሁኔታ ይህ አስተያየት ተገቢ አይደለም፡፡”

2 Comments

  1. “በክልል የሚደረጉ ጨዋታዎች ላይ ደጋፊዎች በጣም አክራሪ የሚሆኑት ነገር አለ፡፡ ይህ ኳስ ጨዋታ ነው ማሸነፍ፣ መሸነፍ እና አቻ መውጣት እንዳለ ቢገነዘቡ በጣም መልካም ነው፡፡ የፀጥታ ኮሚቴው አዲስ አበባ ላይ ብቻ ታጥሯል፡፡”

  2. ለምታቀርባው ስፖርታዊ ዘገባዎች ከፍተኛ ምስጋና አለኝ

Leave a Reply